አንድ ሀገር የፕሬስ ነፃነት ሊኖረው የሚችለው የዳበረ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና በኢኖሚውና በማህበራዊ መስክም የበለፀገ ሲሆን ነው። እነዚህ ባልተሟሉበት ሁኔታ የፕሬስ ነፃነት ከእነዚህ ተነጥሎ ብቻውን ሊከበር አይችልም። በኢትዮጵያ በንጉሡ ዘመንም ሆነ በደርግ ሥርዓት እነዚህ ነገሮች ባለመኖራቸው የፕሬስ ነፃነት የሚታሰብ አልነበረም።
በተለይም በደርግ ዘመን ሀገሪቱ ስትከተለው የነበረው ርዕዮተ ዓለም ማርክሲዝም ሌኒንዝም ስለነበር የዚያ ርዕዮተ ዓለም የፕሬስ ፖሊስ ነበር ሲተገበር የቆየው። በመሆኑም በወቅቱ የነበረው የፕሬስ ሥራ ርዕዮተ ዓለሙን ማሰራጨት ስለ ነበር ፕሬሱ አንድ ወጥ የሆነ የማርክሲዝም ሌኒንዝም መስመርን በማራመድ ሲያገለግል ቆይቷል። ሌላ ምንም አማራጭ አልነበረም፤ አማራጭ አለመኖሩ በራሱ የፕሬስን ነፃነት የሚዘጋ ነበር።
አንፃራዊ በሆነ መንገድ የፕሬስ ነፃነት የተጀመረው በ1983 የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ በኋላ በኢህአዴግ አስተዳደር ዘመን ነው። በዚህ ወቅት የግሉ ዘርፍም በስፋት ሚዲያውን የተቀላቀለበት ወቅት ነበር።በዚያን ጊዜ የግል ጋዜጦችና መፅሔቶች መስፋፋትን
ተከትሎ ስለ ፕሬስ ነፃነት በስፋት መነገርም መተግበርም ጀምሮ ነበር። ነገር ግን በዚህም ዘመን ቢሆን የተወራውን ያህል አልተተገበረም። በወቅቱ የነበሩት የመገናኛ ብዙኃን የመንግሥትን ችግሮች ማውጣት ሲጀምሩና መንግሥትም በሕዝቡ ጥያቄ እየቀረበበት መፈተን ሲጀምር የነበረው የፕሬስ ነፃነት እያሽቆለቆለ መጣ። በተለይም የግል መፅሔቶችና ጋዜጦች ከኢህአዴግ ጋር የነበራቸው ትግል ይበልጥ እየተዳከመ መጥቶ
የግል ፕሬስ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ወደ መግባትና ወደመጥፋቱም ደረሰ። የገበያ መቀነስ፣ የህትመት ዋጋ መጨመርና ሌሎች ችግሮችም ተዳምረው በአንድ ወቅት 160 ይደርሱ ከነበሩት ጋዜጦችና መፅሔቶች በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ቀሩ። ጋዜጠኞቹም ግማሹ ሲሰደድ ቀሪው በተለያየ መስክ ሌላ ሥራ ውስጥ ተሰማራ።
በቀጣይ የፕሬስ ነፃነትን በሀገሪቱ ለማስፈን በመንግሥት በኩል ችግሮችን የሚያሳዩትን የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያመላክቱትን የሕዝብን ድምፅ የሚያሰሙትን የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙኃንን ከማፈንና ከማሳደድ ወደ ማበረታታና መደገፍ መዞር ይጠበቅበታል።
እንደ ሀገር ደግሞ የፕሬስ ነፃነትን ለማስፋፋት የሚሰራ ነፃና ገለልተኛ አካላት ያሉበት አንድ ብሔራዊ ኮሚቴ ወይንም ኮሚሽን ቢቋቋምና በአንድ ወገን የመገናኛ ብዙኃኑን መብት ለማስከበር ቢሰራ በሌላ በኩል ደግሞ ጋዜጠኞች የግለሰብን መብት ከማክበር ጀምሮ በሕግ አግባብና ሥነ ምግባር ተላብሰው እንዲሰሩ ቢያስተምር የዳበረ የፕሬስ ነፃነት ለመፍጠር ይረዳል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2011