ምርጫ 2012ን እንደሚካሄድ ታሳቢ አድርጎ እየሰራ ነው
የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ተጨማሪ ዝግጅትን ጠይቆታል
አዲስ አበባ፡– በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደውን ምርጫ 2012 ታሳቢ አድርጎ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ መጠየቂያ ደብዳቤ መግባቱንም ጠቅሶ፤ ለቦርዱ የመጀመሪያ ሥራው እንደመሆኑ ተጨማሪ ዝግጅትን እንደሚጠይቀው ገለጸ።
የምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ ቦርዱ በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው ቀጣዩን ምርጫ 2012 ለማስፈፀም ከጊዜ ጋር ትንቅንቅ ፈጥሮ በመስራት ላይ ይገኛል።የቦርዱ ሥልጣን በተቀመጠው ጊዜ መሠረት ምርጫ ማስፈፀም ነው።
«ባለን ጊዜ ውስጥ ከቦርዱ የሚጠበቁ ጉዳዮችን አከናውነን ምርጫውን እናስፈፅማለን ብለን ነው የምናምነው።» ያሉት አማካሪዋ፣ «የጊዜ እጥረት ሊያጋጥም ቢችልም በአሁኑ ወቅት በርካታ ሪፎርሞችን በአንድ ላይ ነው እያስኬድን ያለነው» ሲሉ ተናግረዋል።
አማካሪዋ እንደገለፁት፤ የጊዜው ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ መክተቱ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ተቋሙንም ጫና ያሳድርበታል።እንዲያም ሆኖ ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ ነው ሥራውን
በመስራት ላይ የሚገኘው።
«የተለያዩ አካላት የፀጥታ ችግር መኖሩን፣ የጊዜ እጥረት እንዳለና የሕዝብና የቤት ቆጠራም አለመደረጉን ሲያነሱ ይደመጣሉ» ያሉት ወይዘሪት ሶሊያና፣ «እኛ ግን በተቻለ መጠን ውጪያዊ ችግሮችን ሳይሆን በእኛ በኩል ማድረግ ያለብንን ሁሉ አድርገን ዝግጅታችንን እናጠናክራለን» ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ካልተሳካ ደግሞ ለመቼ ነው የሚያሳካው የሚለውም አብሮ የሚታይ ጉዳይ ነው።እንደ ተቋም በአሁኑ ወቅት ዋናው ትኩረት ይደረጋል አይደረግም የሚለውን ሳይሆን ምርጫው የተሻለ ሆኖ እንዲካሄድ መስራቱ ላይ ነው ትኩረት የሚያደርገው።
የቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ፣ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ደብዳቤ ለቦርዱ መግባቱን ጠቅሰው፤ ይህ ሕዝበ ውሳኔ ለቦርዱ የመጀመሪያ ሥራው እንደመሆኑ ተጨማሪ ዝግጅትን እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።
አማካሪዋ እንደተናገሩት፤ ቦርዱ በአሁኑ ወቅት የሪፎርም ሥራ እየሰራ ነው።እነዚህን ሥራዎች ሳይሰራ የሚያካሂደው ሥራ ባልተቀየረ ሕግና ተቋም የሚፈጸም ይሆንና ከበፊቱ የተሻለ ሊሆን አይችልም።ስለዚህም ቦርዱ ሥራ እንዲሰራ የሚፈለገው በፊት በነበረው ቁመና ላይ ሆኖ ነው ወይስ በተለወጠ መንገድ ነው የሚለውም አብሮ መጤን ይኖርበታል።
«የአዲስ አበባንና አገራዊውን ምርጫ ወይም ደግሞ ሕዝበ ውሳኔውን ቦርዱ ተዓማኒነት ባለው መልኩ እንዲሰራቸው ሪፎርሞቹን ማስፈፀሙ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው» ሲሉም ጠቅሰው፤ «ሕዝበ ውሳኔውን በተመለከተ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች አብረው ማየት ያለባቸው የተቀየረ ተቋም መኖሩ ጠቃሚ መሆኑን ነው» ብለዋል።
«የሕዝበ ውሳኔው ጥያቄ ለቦርዱ የመጀመሪያ ሥራው እንደመሆኑ ምንም ዓይነት ልምድ የለውም» በማለት ጠቁመው፤ ከዚህ በፊት የክልል እንሁን ጥያቄ በአገር አቀፍ ደረጃ ተነስቶ ወደቦርዱ አለመምጣቱን አስረድተዋል።ስለዚህም ከምርጫም በተለየ ተጨማሪ ዝግጅትን እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2011
በአስቴር ኤልያስ