የዘንድሮው 26ኛው የዓለም የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።የዘርፉ ባለሙያዎች ደግሞ በዓሉ በአገሪቱ የመከበሩ ምስጢር መሠረታዊ የሆኑ ለውጦች መካሄዳቸውና የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብት ማሻሻያ ፕሮግራሞች በመከናወናቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይኸው ጅማሬ ሳይስተጓጎል ቀጣይ እንዲሆን ይመክራሉ።
በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሚዲያ ብዝሃነትና ልማት ዳይሬክተር አቶ ታምራት ደጀኔ የፕሬስ ቀን በኢትዮጵያ መከበሩ በቀጥታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የለውጥ ሂደት ጋር ግንኙነት እንዳለው ይገልፃሉ።የሰዎች በነፃነት የመደራጀትና የመናገር መብቶች በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በተጨባጭ ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉንም ያመለክታሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤መፃፍና ሐሳብን በነፃነት ማንፀባረቅ ከሚገለፅባቸው መሣሪያዎች
መካከል አንዱ የሚዲያ ብዝሃነት በተለይ በግሉ ሚዲያ ምን ያህል ተስፋፍቷል የሚለው ነው።ከዚህ አኳያ በተለይ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ለግል ህትመቶች ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ ዶክተር ዐብይ ከመጡ ወዲህ ብቻ ግን ከ40 በላይ ለሚሆኑ የግል ህትመት ድርጅቶች ፈቃድ ተሰጥቶ ወደ ገበያ በመውጣት ሐሳባቸውን በነፃነት እያራመዱ ይገኛሉ።በዚህ ዓመት ብቻ ለስምንት የብሮድካስት ሚዲያ ፈቃድ የተሰጠበትና ሥራቸውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው።
«ኢሳትና ኦ.ኤም.ኤንን የመሳሰሉ ውጭ ሆነው የነፃ አውጪነትና የታጋይነት ሚና የነበራቸው ሚዲያዎች በአገር ውስጥ ቅርንጫፍ
እንዲንቀሳቀሱ መደረጉና ሌሎችም ጦማሪያን በነፃነት አገር ውስጥ ሐሳባቸውን እንዲያንፀባርቁ መደረጋቸው ጭምር ነው ቀኑ እዚህ ለመከበሩ ምክንያት የሆነው» በማለትም አቶ ታምራት ያክላሉ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የቴሌቪዥን ዘርፍ ኃላፊ አቶ አቤል አዳሙ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ጋዜጠኛ የሚታሰርባት አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ከለውጡ በኋላ ግን አንድም የታሰረ ጋዜጠኛ ባለመኖሩ ምክንያት በዓሉን የማክበር ዕድል እንድታገኝ ያስቻላት እንደሆነ ነው የሚገልፁት።
«ቀደም ሲል የነበረው እንግልት ቀርቶ ጋዜጠኞችም ሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም እንዲሁም ጦማሪያን ላይ የሚደርሰው ጥፋት በመቆሙ እውቅና ለመስጠትም ታስቦ ነው ኢትዮጵያ እንድታከብር የመደረጉ ምስጢር» በማለትም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
አቶ አቤል፣ «እንደ አለመታደል ሆኖ እንጂ የፕሬስ ቀንን በአፍሪካ ደረጃ ኢትዮጵያ እንድታከብር የሚያስችላት በርካታ ጉዳዮች አሏት።ቀደም ሲል እስራቱ፣ ማንገላታቱ፣ ነፃ አለማድረጉና የመሳሰሉት በመኖራቸው እንጂ የራሷ ፊደል ያላት ብቸኛዋ አገር ከመሆኗም በተጨማሪ አስቀድሞም ቢሆን በራሷ እጅ ፅሑፍ ጋዜጠኝነትን የጀመረች አገር ነች።ለአብነትም የመጀመሪያው አዕምሮ በመባል የሚታወቀውን ጋዜጣ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው የእጅ ፅሑፍ እየፃፉ ለአንባቢያን ማድረሳቸው ቀደም ሲል እንኳ የመረጃ ልውውጡ መኖሩን ነው የሚያመላክተው።በብራና ላይ ፊደል ቀርፃ ሰዎችን ማስተማር የጀመረች አገር ናትና ይህን የፕሬስ ቀን ማዘጋጀቱ ይገባታል» ብለዋል።
እንደ አቶ አቤል ገለጻ አፓርታይድን ለማስወገድ ኢትዮጵያ ጃን ሜዳ ላይ ቢሮ ከፍታበአጭር ሞገድ ከአዲስ አበባ ፀረ አፓርታይድ ንቅናቄዎችን የሚደግፉ መረጃዎች ሲተላለፉ ነበሩ።ዚምባቡዌን ነፃ ለማውጣትም አገሪቱ ብዙ ሰርታለች።አፍሪካ ውስጥ ላሉ የቅኝ አገዛዝ ትግሎች እንደመነሻ ሆናም ብዙ አገልግላለች።ይህን ያደረገች አገር ለፕሬሱ ትልቅ ሚና እንዳላት ሊነገርላትም ይገባል።በመሆኑም በተጠቀሱት ጉዳዮች በዓሉን ለማዘጋጀቱ ትመጥናች።
ዳይሬክተሩ አቶ ታምራት ቀደም ሲል የነበረውን የፕሬስ ነፃነት ሲገልፁ እንደተናገሩት፤ የሕግ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት አኳያ ኢትዮጵያ ችግር የለባትም።በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 29 እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁት ከየትኛውም የመረጃ ነፃነትን ለመደገፍ ከወጡ ሕግጋት የማይተናነስ የተሟላ ሊባል የሚችል ሕግ አላት።ይሁን እንጂ በተጨባጭ ሲታይ በአንድ ወይ በሌላ መልኩ ተገድቦ ነበር።
ለወረቀት ድጎማ አለመደረጉ፣ የቀለምና የህትመትም ዋጋ መጨመሩና መሰል ተግዳሮቶች ሲደራረብባቸው በርካታ ህትመቶች ከገበያ ወጥተዋል።ከብሮድካስቱም አኳያ እንዲሁ ቅድመ ሁኔታዎች ሰፊ ስለነበሩ በሚፈለገው ደረጃ መሄድ አልተቻለም።አንዳንድ ጋዜጠኞችን ደግሞ በሆነው ባልሆነው የማሰር ሁኔታዎች ነበሩ።እንዲያም ሆኖ መሰረቱ የተጣለው ባለፉት ዓመታት መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
አቶ አቤል ባለፉት ዓመታት በፕሬስ ነፃነቱ ዙሪያ ምንም ነገር አልነበረም ብሎ መናገር እንደማይቻል ይናገራሉ።በ1966 ዓ.ም አብዮቱ ሲጀመር ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ እንዲሁም ኢህአዴግ ከገባ በኋላ እስከ ምርጫ 97 ድረስ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ እንደነበር በማስታወስ በተለይ ምርጫ 97 ወቅትም ወደ 300 ያህል ጋዜጦችና መጽሔቶች የነበሩ ቢሆንም ከምርጫው በኋላ ግን ሚዲያውን ወደማፈን መገባቱን ያስረዳሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት መምህር ዶክተር ተሻገር ሽፈራው እንደሚናገሩት፤ ቀደም ሲል የነበረው ሁኔታ በኢትዮጵያ ብዙ ጋዜጠኞች የሚታሰሩበት፣ የሚሰደዱበት እንዲሁም ብዙ ጋዜጦች የሚዘጉበት፣ የሚታፈኑበት፣ መረጃ ለማግኘት እጅግ አስቸጋሪ የሆነበት ሁኔታ ነበር።
አቶ ታምራት እንደሚናገሩት፤ ነፃነቱ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።አገር አቀፍ የሚዲያ ፖሊሲና ኮሙኒኬሽኑ የሚመራበት ስትራቴጂና የመሳሰሉት ተግባራዊ መደረግ አለባቸው።ለሌላው ልማት እንደሚደረገው ሁሉ ልዩ ልዩ ድጋፎች ማለትም የግብር ቅነሳ፣ የቀለም ዋጋ ቅነሳ፣ የህትመት ዋጋ ቅነሳ እንዲሁም ማተሚያ ቤቶች እንዲስፋ ማድረግ፣ ጋዜጠኞች በፕሬስ ካውንስል እንዲደራጁ የማድረግ፣ ልዩ ልዩ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል።አልፎ ተርፎ በየዓመቱ አፈፃፀማቸው እየታየ ድጋፍና ሽልማት እንዲሁም እውቅና የመስጠት ሁኔታዎች መኖር አለባቸው።
ባለፉት ዓመታት ዳቦ ማግኘት ያልቻለ ብዙ ሕዝብ እያለ የሳተላይት ስርጭትን ለማስተጓጎል በብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሲደረግ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አቤል የሚዲያ ተቋማት ማነቆ የሆነባቸውን ነገሮች በማሻሻል እንዲሁም ሥልጠና በመስጠት መሰራት አለበት።የፓርቲ አቋም የሚያፀባርቅ ሚዲያ እንዳይኖር ማድረግም ያስፈልጋል።
ዶክተር ተሻገር በበኩላቸው፤ይህ አሁን የመጣው ነፃነት እንዳይስተጓጎል መደረግ ካለበት መካከል አንዱ መረጃ ለማግኘት ጋዜጠኞች መከልከል እንዳይኖርባቸው ማድረግ እንደሆነ ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት የመገናኛ ብዙኃን አብዛኞቹ በአክቲቪስቶች የሚመሩና በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ተፅዕኖ ስር ያሉ ናቸው።እንደ ሌላ ሚዲያ በማስታወቂያ ገቢ እየተዳደሩ አይደለም።ከፖለቲካ ቡድን ደጋፊዎች የባንክ አካውንት ከፍተው ገንዘብ እየሰበሰቡና ቴሌቶን እያካሄዱ የሚመሩ ናቸው። እነዚህ ከመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ውጪ ያሉ ስለሆኑ ይህ ሁኔታ የፕሬስ ነፃነትን በተወሰነ ደረጃ በራሱ በሚዲያውም የተጨቆነ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ዶክተር ተሻገር ገልጸዋል።
እንደ ዶክተሩ ገለፃ በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ተወስነው ያንን ሐሳብ ሕዝብ እንዲቀበል ግፊት የሚያደርጉ፤ ለምሳሌ የዜግነት ፖለቲካ ብቻ ወይንም የብሔር ፖለቲካ ነው የሚሻለው ብለው እሱ ላይ ብቻ ግፊት የሚያደርጉ አሉ።እነዚህ የፕሬስ ነፃነትን ችግር ውስጥ ይከታሉ።ስለዚህ የፕሬስ ነፃነት አልተገደበም የሚባለው ካለፈው ጋር ሲነፃፀር ነው እንጂ ከላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች አማካይነት ገደብ እንዳለው ሊታወቅ ይገባል።
መረጃዎች እንደሚገልፁት፤ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ያለው የሚዲያ ነፃነት ከ180 አገሮች መካከል 150ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጣት እንደነበር ይታወሳል።ዘንድሮ ግን 40 ደረጃዎችን በማሻሻል 110ኛ ላይ እንደምትገኝ ታውቋል።
ዶክተር ተሻገር እንዳሉት፤የፕሬስ ነፃነቱ ባይኖር አገሪቱ መረጃ መደበቅ ይመጣል፤ መረጃ ያላገኘ ሕዝብ ደግሞ ችግር ላይ ነው የሚወድቀው።ሐሳብን መግለፅ ውጥረት የመቀነስ አቅሙ ከፍተኛ ነው።ሐሳብ የሚታፈን ከሆነ ግን ልዩ ልዩ አስተሳሰብና ፍላጎት ያላቸው የፖለቲካ ቡድኖች ወደ ብጥብጥና ሁከት ይገባሉ።
ፕሬስ ዴሞክራሲን ከማረጋገጥ አኳያ በምንም መልኩ የማይተካ ሚና እንዳለው የሚናገሩት አቶ ታምራት ዴሞክራሲን አበለፅጋለሁ የሚል መንግሥት የፕሬሱን ነፃነት መጠበቅ አለበት።ይህ መብት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ዴሞክራሲን ማስፈን አይቻልም። የመፃፍና የመናገር ነፃነት የሚባሉት በተሟላ መልኩ ሊተገበሩ አይችሉም። ይህ ካልሆነ ደግሞ አገሪቱ ወደፊት የመቀጠል ሁኔታዋን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ይሆናል።»ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2011
በአስቴር ኤልያስ