ስለፍቅር እስከ መቃብር የሚወራበት አጋጣሚ በጣም ብዙ ነው አንድ ማንበብ የማይወድ ሰው ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር ምንድነው?›› ተብሎ ቢጠየቅ ‹‹የሀዲስ አለማየሁ መጽሐፍ›› ብሎ መመለሱ አይቀርም ፍቅር እስከ መቃብርን ምንም ማንበብ የማይችሉ እንኳን ቢያንስ በስም ያውቁታል ምክንያቱም የሚሰማበት አጋጣሚ ብዙ ስለሆነ
ምን እንደሆኑ ማብራራት አይችሉ ይሆናል እንጂ እረኞች እንኳን በዛብህና ሰብለ ወንጌል የሚባሉ እንዳሉ ያውቃሉ ከዚያ አለፍ ሲል ደግሞ ፊታውራሪ መሸሻና ጉዱ ካሳ የሚባሉ ሰዎች እንደነበሩ መጽሐፍ የማያነቡ ሁሉ ያውቃሉ እንዲያውም አሁን አሁን በዛብህና ሰብለወንጌል የሚባሉት በሕይወት የነበሩ ሰዎች የሚመስሏቸውም አሉ ይሄ ማለት የማያነቡና ልብወለድ መሆኑን የማያውቁ ሁሉ ስለፍቅር እስከ መቃብር ሰምተዋል ማለት ነው
ይህ የሆነው እንግዲህ በብዙ ምክንያት ነው አንደኛ ፍቅር እስከ መቃብር ከሰፈር ጨዋታ እስከ ትልልቅ መድረኮች ብዙ ተብሎለታል ከዚህም በላይ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ይደመጥ በነበረው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬዲዮ በ1990ዎቹ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተተርኳል ራሳቸው ሀዲስ አለማየሁ እንዳሉት ወጋየሁ ንጋቱ ለመጽሐፉ ሕይወት ሰጥቶታል በፍቅር እስከ መቃብር ውስጥ ያሉ ገጸ ባህሪያት በሕይወት ያሉ እስከሚመስለን ድረስ ውስጣችን ገብተዋል የወጋየሁ ንጋቱ ትረካ ለማያነቡት ሁሉ መጽሐፉን እንዲታወቅ አድርጎታል
የማንበብና መጻፍ ልምድ ወደላቸው ሰዎች ስንመጣ ደግሞ ፍቅር እስከ መቃብር በርካታ ውይይቶች፣ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎች ተደርገውበታል የቅድመ ምረቃም ሆነ የድህረ ምረቃ ምርምሮች ተሰርተውበታል በብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ዳሰሳ ተሰርቶበታል የሬዲዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ላይ የስነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ብዙ ብለውበታል ብዙ የመድረክ ውይይት ተደርጎበታል
ፍቅር እስከ መቃብር ስሙ የሚነሳው ለሱ ተብሎ በተዘጋ መድረክ ላይ ብቻ አይደለም በየትኛውም የስነ ጽሑፍ መድረክ ላይ፣ የመጻሕፍት ውይይት ላይ ፍቅር እስከ መቃብር ስሙ ይነሳል የልብወለድ መጽሐፍ ማነጻጸሪያም ይደረጋል በማስተማሪያ መጻሕፍት ውስጥም ይጠቀሳል ተማሪዎች ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ቢያንስ በስም ያውቁታል
ከእነዚህ ሁሉ ምክንያቶችም በላይ ደግሞ መጽሐፉ በራሱ ላነበበው ሁሉ አይረሴ ሆነ እዚህ ጋ የበዛብህና ሰብለወንጌል ፍቅር አለ፤ እዚያ ጋ የቦጋለ መብራቱና የውድነሽ በጣሙ ፍቅር አለ፤ አሁንም እዚያ ጋ የፊታውራሪ መሸሻ እና ወይዘሮ ጥሩአይነት ፍቅር አለ የካሳ ዳምጤ እና የእንቆጳ ፍቅር አለ የሁሉም ፍቅር የሚሄደው እስከ መቃብር ነው ይህም በሰዎች ልብ ውስጥ አይረሴ አድርጎታል
ወዲህ ደግሞ በዚያ ዘመን የማይታሰበውን፣ በዚያ ዘመን ተደፍሮ የማይነገረውን ካሳ ዳምጤ(ጉዱ ካሳ) ደፍሮ እየተናገረ የአንባቢን ቀልብ ያንጠለጥላል እነ አበጀ በለው በዚያ በፊውዳል ሥርዓት ውስጥ ‹‹እምቢ!›› ማለት በማይታሰብበት ዘመን ‹‹አንገብርም›› እያሉ ያምጻሉ የመብት ጥያቄ ያነሳሉ ፍቅር እስከ መቃብር ፍቅር ነው፤ ፖለቲካ ነው፣ ማህበራዊ ሕይወት ነው መጽሐፉ በፍቅር፣ በማህበራዊ ኑሮ እና በፖለቲካ ብዙ ሊባልለት የሚገባ ነው
ይህን መጽሐፍ በሁሉም ዘውግ መዳሰስም ሆነ መወያየት ይከብዳል በፍቅር፣ በማህበራዊ ኑሮም ሆነ በፖለቲካ ሥርዓቱ እየለዩ ሊያወያይ ይችላል ከስነ ጽሑፍ ቅርጽ አንጻር ደግሞ ሌላ ራሱን የቻለ መድረክ መሆን ይችላል
ዛሬ ፍቅር እስከ መቃብርንና በፍቅር እስከ መቃብር ላይ የተባሉ ነገሮችን ማስታወስ የፈለግነው ሰሞኑን ፍቅር እስከ መቃብር አጀንዳ ስለሆነ ነው አንጋፋው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ፍቅርስ እስከ መቃብርን ለብዙዎች አስተዋውቋል እነሆ አሁን ደግሞ ዘመኑ በሚፈቅደው የዕይታ ቴክኖሎጂ በድራማ መልክ ሊታይ ነው ይህንንም የሚያደርገው አንጋፋው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ነው ባለፉት ሳምንታት የተዋወቀ ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ ከባለሙያዎች ጋር ውይይት እየተደረገበት ነው
ድራማው ሲጀመር ምልከታችንን እና የባለሙያዎችን አስተያየቶች(ምናልባትም የመድረክ ውይይቶች ሊደረጉ ይችላሉ) እናያለን እስከዚያ ግን በተለያየ ጊዜ ስለፍቅር እስከ መቃብር በባለሙያዎች የተባሉትን እናስታውሳችሁ
በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ይደረግ በነበረው የመጻሕፍት ውይይት ላይ ሚዩዚክ ሜይ ዴይ ከአምስት ዓመታት በፊት (የካቲት 11 ቀን 2010 ዓ.ም) በፍቅር እስከ መቃብር ላይ ውይይት አድርጎ ነበር በውይይቱም የስነ ጽሑፍ ባለሙያና መምህር መሰረት አበጀ ‹‹የግፍ መርህ ዳፋ- የሀዲስ አለማየሁ ደወል(በፍቅር እስከ መቃብር)›› በሚል በመነሻ ሀሳብ አቅርበው ውይይት ተደርጓል አቅራቢው ትኩረት ያደረጉት መጽሐፉ በፊውዳሉ የአገዛዝ ሥርዓት ላይ ብቻ ባለው ይዘት ነው ይሄውም በፊት ፊታውራሪ መሸሻና በነዋሪው መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ማለት ነው
በመጽሐፉ ውስጥ ፊታውራሪ መሸሻ የገዥው መደብ ወኪል ናቸው እርሳቸው የፊውዳሉን ሥርዓት ሲወክሉ ከጭቁኑ ሕዝብ ጋር የነበረውን ግብግብ ያሳያል የጭቁኑ ሕዝብ ጥያቄም የነጻነትና የፍትህ ጥያቄ ነው ይህም የግፍ አሰራር ነጻነትን በማሳጣቱ የመጣ ብሶት ነው የነበረው ጭቆና የተፈጥሮ መብትን ሁሉ የሚጋፋ ነው
በበዛብህና በሰብለወንጌል ፍቅር እንኳን ስንሄድ ሁለቱ እንዳይገናኙ ያደርጋል ግፍ ሲበዛ አመጽን ያስነሳል በዛብህና ሰብለወንጌል ግፍ ሲበዛበቸው አምጸዋል፤ ተሰደዋል በዛብህ ከወላጆቹ ኋላቀር እምነት ጋር፤ ሰብለወንጌልም ከወላጆቿ ኋላቀር አስተሳሰብና ልማድ ጋር፤ ጉዱ ካሳ ከሥርዓቱ አሮጌ አስተሳሰብ ጋር ሲፋለሙ ያሳያል ይሁን እንጂ የተናጠል እንቅስቃሴያቸው ደግሞ አሸናፊ አያደርጋቸውም የጉዱ ካሳ፣ የበዛብህና የሰብለወንጌል መጨረሻ ነጻነትና ፍትህ እንደናፈቁ መቅረት ይሆናል
ሌላኛው አይነት አመጽ ሕዝባዊ የሆነው ነው ይሄውም በገበሬዎችና በገዥው መደብ መካከል የነበረው ማለት ነው ቅራኔው በጣም የቆየ ነበር ይህንንም እነ አበጀ በለው አሳይተዋል
ፊታውራሪ መሸሻ ከተለመደው ግብር በተጨማሪ ለዓመት በዓል መታያ እንዲቀርብላቸው ፈለጉ ገበሬዎቹ ለሰላም ሲሉ ያቀርቡላቸው ነበር ፍትሃዊ እንዳልሆነ እያወቀ፤ ነገር ግን ሀብትና ንብረቱ እንዳይጠፋ፣ ልጆቹ እንዳይበተኑበት ሲል ገበሬው በደሉን እያወቀ ይገብር ነበር በኋላ ፊታውራሪ መሸሻ ግፉን በጣም ሲያበዙት ገበሬው ተሰብስቦ መመካከር ጀመረ ‹‹ግዴታ የለብንምና አንከፍልም›› አሉ ከመካከላቸውም አበጀ በለውን መረጡ ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ ፊታውራሪ መሸሻ ፈተና የገጠማቸው እነ አበጀ በለው ዘመናዊ አስተሳሰብ የነበራቸው ሆኑ አበጀ በለው ፊታውራሪ መሸሻን በማረካቸው ጊዜ ‹‹ተዋግተህ እንኳን ብትይዘኝ አይቆጨኝም ነበር›› ሲሉት ‹‹ተዋግቼ መያዝ እችል ነበር፤ ግን እኔ ደም እንዲፈስ አልፈልግም›› ነው ያላቸው
‹‹ገበሬ እና ወይፈን እንዛዝላ ሲጥሉበት ነው›› ይሉ ነበር ፊታውራሪ መሸሻ ገበሬን ከከብት ጋር እያነጻጸሩ ማለት ነው ገበሬውን እንዲህ ሲንቁ ሲንቁ ነው ኋላ ጉድ የሰራቸው ፊታ ውራሪ መሸሻ ገበሬዎችን ለመያዝና ለመቅጣት ሲዘምቱባቸው ገበሬዎች ግን ይሸሹላቸው ነበር፤ ይህም ደም እንዳይፈስ በማሰብ ነው ፊታውራሪ ግን ይህን አልተረጎሙትም፤ ፈርተውኝ ነው የሚሸሹ ብለው ነው ያመኑት ከእርሳቸው ይልቅ ሕዝቡ ሰላም ይፈልግ ነበር ማለት ነው ከዘመኑ አስተሳሰብ ወጣ ያለ ዕይታ የነበረው ጉዱ ካሳ ‹‹ልጅ ናቸው፤ አያውቁትም›› እያለ ይሳለቅባቸው ነበር አበጀ በለው ደግሞ ‹‹ህጋዊ ሽፍታ›› ይላቸው ነበር
ፊታውራሪ መሸሻ በእኩልነት አያምኑም በዛብህን ‹‹የድሃ ልጅ›› እያሉ የባላባት ልጅ ባለመሆኑ በጣም ያሳንሱታል ልጃቸው ሰብለወንጌል ‹‹እርስዎ የድሃ ልጅ የሚሉትን እኔ እወደዋለሁ›› ስትላቸው ‹‹ያ መተተኛ የተበተበብሽ መተት ነው እንዲህ የሚያደርግሽ›› እያሉ ይቆጣሉ ምክንያቱም ራሳቸውን የተቀባ የባላባት ዘር አድርገው ስለሚያስቡ ሌላውን አሳንሰው ነው የሚያዩት
ፊታውራሪ መሸሻ እምነታቸውም የተምታታ ነው ዳዊት ይደግማሉ፣ ልጃቸውንም ያስተምራሉ፣ ጊዮርጊስን ያምናሉ፤ ያስቀድሳሉ ይሁን እንጂ ከባዕድ አምልኮ የተላቀቁ አይደሉም ዘመቻ ሲሄዱ ቀበሮ ካገኙ እንደ መጥፎ ዕድል ነው የሚቆጥሩት ጊዮርጊስን እያመኑ ያሰቡት ነገር ካልደረሰላቸው ደግሞ ‹‹ጊዮርጊስ ከዳኝ›› እያሉ ይወቅሱታል ፈረሳቸውን እንኳን ‹‹እንደ ጊዮርጊስ እንዳትከዳኝ›› ብለውታል
ፊታውራሪ መሸሻ ያንን ሁሉ ግፍ ይዘው መጨረሻ ላይ ግን ተሸንፈዋል ልጆቻቸው ተሰቃይተዋል፣ ራሳቸው ተሰቃይተዋል፣ ከብቶታቸውን ተዘርፈዋል የገዢው መደብ ወካይ ነበሩና የሥርዓቱን ውድቀት አሳይተዋል ፍትህ ለማግኘት ሲደክሙም አድካሚነቱን አይተዋል
የስነ ጽሑፍ ባለሙያና መምህሩ መሰረት አበጀ እንደሚሉት፤ ስነ ጽሑፍ መጻፍ ያለበት መሆን ስለሚገባው ቅንና በጎ ጉዳይ ነው ስለመከባበር ማሳየት አለበት መጥፎውን ነገር ብቻ መጻፍ ከገሃዱ ዓለም ከሚታየው የተለየ አይሆንም በአገራችን ግን የማንበብ እንጂ የመተርጎም ችግር እንዳለ ያሳያሉ ለዚህም አንድ ምሳሌ ይጠቅሳሉ በዓሉ ግርማ ‹‹የቀይ ኮከብ ጥሪ›› መጽሐፉ ላይ በጣም መመስገን ነበረበት፤ ግን ብዙም ሲመሰገንበት አይሰማም እንዲያውም የመንግስት ደጋፊ ተደርጎ ነበር የተወሰደው በቀይ ኮከብ ጥሪ ላይ ግን ደርግና ኢህአፓ መታረቅ እንዳለባቸው ነው ያሳየው ሌላ መንግስት ከሚመጣ ያለውን መንግስት ማረቅና ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ነው የገለጸው
ሂሩት ኢህአፓ ናት ደርቤ ደግሞ የአብዮት ጠባቂ ነው ሂሩት ተመታ ስትወድቅ ደርቤ አንስቶ ወደ ሆስፒታል ይወስዳታል የዚህም መልዕክት ኢህአፓና ደርግ እንዲታረቁ ነው
ፍቅር እስከ መቃብር ለውጥ ፈላጊነትን ያሳያል ግፍ መጨረሻው እንደማያምር ያሳያል ድርሰቱ በወቅቱ የነበረው የዘውዳዊ አገዛዝ የአንድ ብሔር የበላይነት የሚታይበት እንዳልሆነም ያሳያል የገዥው መደብ ወካይ ፊታውራሪ መሻሻ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ናቸው ፍዳ ሲያሳዩት የነበረው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪውንና የክርስትና እምነት ተከታዩን ነበር፤ የራሳቸው ወገን ላይ ነው ያን ሁሉ ግፍ ሲፈጽም የነበረው
ደራሲው ሀዲስ አለማየሁ በፊታውራሪ መሸሻ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን አገዛዝ ነው ያሳዩት እንግዲህ እዚህ ላይ ነበር ከመድረኩ ተሳታፊዎች አንድ ክርክር የተነሳው ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሀዲስ አለማየሁን ሸልመዋቸዋል ጥያቄ የሆነው ‹‹የእርሳቸው አገዛዝ የግፍ አገዛዝ መሆኑን እየተረከ እንዴት ሊሸልሙ ቻሉ?›› የሚለው ነው አንዳንዶቹ ‹‹ንጉሱ መጽሐፉን ሳያነቡት ይሆናል፤ ወይም አልገባቸውም ማለት ነው›› ብለዋል አንዳንዶቹ ደግሞ ‹‹የለም! እንዲህ ማለትማ ድፍረት ነው፤ እንዴት አያነቡትም? እንዴትስ አይገባቸውም? በቃ! ሥራው ድንቅ ስለሆነ ተደስተውበት ነው፤ እንዲያውም ንጉሡ በቤተ መንግሥት ውስጥ ከነበሯቸው መጻሕፍት አንዱ ፍቅር እስከ መቃብር ነበር›› ብለዋል
የስነ ጽሑፍ ባለሙያና መምህር መሰረት እንደሚሉት፤ በወቅቱ በስነ ጽሑፍ መዝነው ሽልማት የሚሰጡት የስነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ነበሩ ንጉሡም ያንን አይቃወሙም ቢያነቡትም ባያነቡትም የመጽሐፉን ታሪክ ያውቁታል መሪዎች በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም በየትኛውም ነገር አስረጂዎች አሏቸው ባለሙያዎች ይነግሯቸዋል ዳሩ ግን ንጉሡ ለምን ሀዲስ አለማየሁን እንደሸለሙ ተጠይቀው ‹‹እንደዚህ መሆኑን እኔ መቼ አውቄ›› ብለዋል በዚያ ላይ በወቅቱ የነበራቸው ጊዜ ያንን መጽሐፍ ለማጣጣም የሚያመች አልነበረም በፖለቲካ ሥራ ተጠምደው ነው የሚውሉት
ፍቅር እስከ መቃብር እውነትም የዘመኑን ዘውዳዊ አገዛዝ የተነበየ ነበር ማለት ነው የሥርዓቱ ወካይ ፊታውራሪ መሸሻ መጨረሻቸው እንዳላማረው ሁሉ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መጨረሻም አላማረም የነበረው የባላባትነት ዘመን አክትሟል በባላባትነት ያምኑ የነበሩት ንጉሱ በመጨረሻ በደርግ እጅ ገብተዋል ሥርዓታቸው መውደቅ ብቻ ሳይሆን እርሳቸውም ተሰቃይተዋል
በነገራችን ላይ የስነ ጽሑፍ ባለሙያና መምህር መሰረት ከተናገሩት ‹‹ትርጉም›› የሚባለው ነገር ልብ ሊባል ይገባል ብዙዎቻችን እናነባለን እንጂ አንተረጉምም ለዚህም ነው አረዳዳችን የተለያየ የሚሆነው እርግጥ ነው ቢተረጎምም ልዩነት ሊኖር ይችላል፤ የተለያየ አተረጓጎም ይኖራል
ለምሳሌ ፍቅር እስከ መቃብርን ያነበበ አንድ ወጣት፣ አንድ የሃይማኖት እና አንድ ፖለቲከኛ ስለመጽሐፉ ጭብጥ ብንጠይቅ የተለያየ አረዳድ ልናገኝ እንችላለን ምናልባትም ወጣቱ ስለ በዛብህና ሰብለወንጌል የፍቅር ጽናት፣ የሃይማኖት አባቱም ስለ እምነት፣ ፖለቲከኛውም በዘውዳዊ ሥርዓቱ ውስጥ የነበረውን አገዛዝ ሊነግሩን ይችላሉ መጽሐፉ ከዚህም በላይ ብዙ የሚያወያይ ነው
እነሆ አሁን ደግሞ በቴሌቭዥን ድራማ ሊመጣ ነው፤ ተጨማሪ ሀሳቦችና ዕይታዎች ይንሸራሸራሉ ዘመን ተሻጋሪ ሥራ እንዲህ ሕያው ይሆናል
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም