ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ እና በማህበራዊ መስኩ ከወንዶች እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል በየዓመቱ ይከበራል። ጾታዊ ጥቃትን ለማስቆምና የህግና የሰብዓዊ መብታቸውንና ነፃነታቸውን ለማስከበር ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ቆይቷል። ለዚሁ ዓላማ ትግል ያደረጉ ሴቶችን በመዘከር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ 1975 በይፋ ሲያከብረው ዓለማቀፋዊ ይዘቱ የተጠናከረው በዓሉ እ.ኤ.አ ከ1911 ጀምሮ እንደሆነ ይገለጻል።
ታዲያ ዘንድሮ ይህ በዓል በዓለም ለ110ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ47ኛ ጊዜ ይከበራል። ለምን ይከበራል ከተባለ ደግሞ ቀድሞ ዓላማን ማወቅ ከምንም በላይ ያስፈልጋል። በሴቶች ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ ስለዚሁ ዓላማ እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በዓሉ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተደረገ ትግልን መሰረት አድርጎ የተጀመረ ነው። መነሻው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1908 በኒውዮርክ ከተማ ነዋሪ የሆኑ 15 ሺህ ሴቶች ሲሆኑ፤ የተነሱበት አላማም የተሻሻለ የሥራ ሰዓትና የደመወዝ ክፍያን እንዲሁም የመምረጥ መብታቸው እንዲከበር መጠየቅን ያለመ ነው። አደባባይ በመውጣት ሀሳባቸውን አስተጋብተዋል።
ዓላማው ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ እና በማህበራዊ መስኩ እንዲሁም በጋራ የሀገር ግንባታ ላይ ከወንዶች እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ታሪካዊ ቀን ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበር የጀመረው በአውስትራሊያ፣ ዴንማርክ፣ ስዊድንና ጀርመን እ.ኤ.አ በ1911 ነው። ስያሜውን ያሰጠችውም በዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሀገን በተካሄደ ሁለተኛው የሴቶች ኮንፈረንስ የተገኘችው ክላራ ዜትኪን የተሰኘች ጀርመናዊት ሴት ነች። ይሄን ተከትሎም ቀኑ ዛሬ ድረስ በዓለም ላይ የሚገኙ ሴቶች ዘር፣ ቀለም ፣ቋንቋ ፣ሃይማኖት እንዲሁም መልካ-ምድራዊ ድንበር ሳይገድባቸው ሕብረት ፈጥረው ለነጻነታቸው፣ ለሰብዓዊ እኩልነታቸው፣ ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ በአንድነት እንዲያከብሩት ሆነዋል። ድምፃቸውን እያሰሙበትም ቀጥለዋል።
እንደ ሀገርም ባለፉት ዓመታት በዓሉን ይሄን መሰረት አድርጎ ነበር ሲከበር የቆየው ያሉት ወይዘሮ ሙና፤ በ2013 ዓ.ም ወሩን ሙሉ በተለያየ መርሃ ግብር በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቷል። ወሩን ሙሉ በተለየ ሁኔታ ለማክበር በፌዴራልም በክልሎችም የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል። ‹‹ወሩን ሙሉ ሲባል ወሩን ሙሉ ለሴቶች መብት ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል›› ማለት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ‹‹የሴቶችን መብት የሚያከብር ማህበረሰብ እንገንባ›› የሚል መሪ ሀሳብ በመያዝም ነበር የተከበረው። ጥሩ መነቃቃት የፈጠረ እንደነበርም ታይቷል በማለት ያስታውሳሉ።
መሪ ሀሳቡ ‹‹የሴቶችን መብት የሚያከብር ማህበረሰብ እንገንባ›› እንደመሆኑ ከምንም በላይ የማህበረሰቡን ለሴቶች ያለውን የተዛባ አመለካከት የሚቀይር ሥራ መሥራት አለብን የሚለውን የሚያመለክት ነው። ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በየደረጃው ሁሌ ስለ ሴቶች መብት እኩል እንዲናገር ማስቻል ይኖርብናል ብለን ሰርተናል ይላሉ።
‹‹ወሩን ሙሉ አልኩ እንጂ በዓሉ ዓመቱን ጠብቀን አንድ ቀን ብቻ የምናከብረው አለመሆኑ ግንዛቤ ሊያያዝበት እንደሚገባ መናገር እፈልጋለሁ›› ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ። እንዳከሉት በዓሉን እስከ አሁን በነበረው ሂደት ሁልጊዜ ቀኑን ጠብቀን አንድ ቀን ብቻ ነበር የምናከብረው። አሁን ላይ ቆም ተብሎ ሲታሰብ ታዲያ ለሴት ስለመብቷ አንድ ቀን ብቻ ማውራት ትክክል አይደለም። ዓመቱን ሙሉ ልናወራላትና ዓመቱን ሙሉ የሴቷን መብት እያከበርን መሄዳችንን ማረጋገጥ አለብን የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል። በዚህም በዓሉ መከበር ያለበት አግባብ ትኩረት ተችሮት ነው። ይህንንም እያስፈጸምን እንገኛለን።
እንደ ሚኒስቴር ዴኤታዋ ማብራርያ፤ አንዱን ወርም ቢሆን ትኩረተ እንዲሰጠው ተደረገ እንጂ ዓመቱን ሙሉ የሴቶችን መብት ማክበር አስፈላጊ ነው። ይሄ በየደረጃው ታሳቢ መደረግ አለበት። እንዴት ነው የሴቷን መብት እያከበርን ያለ ነው በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጆች ምን ያህል የሴቶችን መብት እያከበሩ ነው ያሉት፣ የሕግ ማዕቀፎች ምን ያህል እየተተገበሩ ነው? የሚለውን መፈተሽ፣ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግና ምላሽ ማግኘቱንም ማረጋገጥ ይገባል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ደረጃ በተለይ በኮቪድና የተለያዩ ግጭቶች በተፈጠሩበት ወቅት ሴቶችና ህፃናቶች የጥቃት ሰለባ የሆኑበት እንዳለ በመስክ ምልከታ የተደገፈ መረጃ ነበር። በቀጣይ ሴቶች ለእዚህ ዓይነቱ ድርጊት እንዳይጋለጡ መታደግ የሚያስችል ሥራ በስፋት ተከናውኗል። ይሄ ሲሰራ ከጾታዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ ታክስ ፎርስ ነበር። ይሄ ሴቶች፣ ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ፣ ጤና ተቀናጅተው ሲሰሩት የቆዩት ነበር። በተጨማሪም ይሄን መሰረት አድርጎ እንደ ተቋም ጾታዊ ጥቃትን ከመከላከል አኳያ ‹ብሔራዊ የጾታዊ ጥቃት ወንጀል› የመረጃ ስርዓት እየተዘረጋ የነበረበት እንደነበርም ያወሳሉ። ለዚህ የሰነድ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። በቀጣይ ከሚመለከታቸው የተቋማት ኃላፊዎች ጋር ተፈራርሞ ወደ ሥራ የመግባቱ ጉዳይ ለመተግበር ዝግጅት ተደርጎም ነበር። እንደውም ይሄ ሥራ ትልቅና እንደ ሀገር የመጀመሪያውም ነበር። ዋናው ዓላማው ጥቃት አድራሾች መረጃቸው በትክክል እንዲያዝ ማስቻል ሲሆን ይሄ ወንጀልን ከመከላከል አኳያ ሕብረተሰቡንም ለማስተማር በእጅጉ የሚረዳ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። አጥቂዎች ዳግም ጥቃት እንዳይፈፅሙ ለማድረግም አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ ታሳቢ ተደርጎ ነው ወደ ሥራ ተገብቶ የነበረው።
በዚህ በ2013 ዓ.ም ከጾታዊ ጥቃት መከላከል ጋር ተያይዞ ትልቁ ችግር መረጃ የነበረ ሲሆን ተግባሩ እንደ አንድ የመረጃ ምንጭ በመጠቀም ወንጀሉን መከላከል እንደሚያስችልም ታምኖበት ነበር።
የጥቃቱ ወንጀል መንስኤ ምንድነው ከተባለ የመጀመሪያው በህብረተሰብ ውስጥ ለሴቶች ያለ የተዛባና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአመለካከት ችግር፣ የወንዶች የበላይነት መስፈን፣ አንዳንድ ሴቶች ለራሳቸው ያላቸው አመለካከት ዝቅ ማለት ወይም በራስ መተማመን መጥፋት፣ የሕግ አተገባበርና የአፈፃፀም ችግር ነው። ሌላውና ራሱን የቻለ መንስኤ በ1985 የወጣው የሴቶች ፖሊሲ ነው። ይሄ ማለት ህገ መንግስቱና የሴቶች ፖሊሲ አይጣጣሙም ማለት ነው።ፖሊሲው ብዙ ነገሮች ይጎሉታል።
እንደ ተቋም ጉድለቱን የመሙላቱ ሥራ ተጀምሯል ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፤ በድጋሚ እየተከለሰ ያለበት ሁኔታ አለ። አቅጣጫ የማስቀመጥና ክፍተቱን የመፈተሸ፣ የወጡ ህጎችንም እንዴት ነው ተግባራዊ እየሆኑ ያሉት በማለት በደንብ ተዟዙሮ ማየት ያሻል። አሁን ያለው ዓለም የወንዶች የበላይነት ያለበት ነው። ከዚህ አንፃር አንዳንድ የወንድ ሀሳብን ሴቶች የሚጋሩበት ሁኔታ ስለሚታይ እዚህ ላይ በሚገባ መሥራት ያስፈልጋል።
እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንሁን ስንል የመብትም ጉዳይ ነው። የመብት ጥያቄያችን በዚህ ደረጃ ነው ወይ የሚታየው የሚለው ሥራ ይፈልጋል። በመሆኑም አስተሳሰብ ላይ በየደረጃው መሥራት ይጠይቃል። በዚህ በኩል ሁሉም መገናኛ ብዙሃን ሊሰሩበት ይገባል። ሴቶች በአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ደረጃ መምጣት አለባቸው የሚለው ከመብትም አኳያ መታየት አለበት።
‹‹ወንዶች ሰጪ እኛ ተቀባይ መሆን የለብንም የሚል ዕምነት አለኝ።›› የሚሉት ወይዘሮ ሙና፤ ይህ ጉዳይ መብታችን ነው! ዕድሉን ብናመቻችላቸው፣ ብንደግፋቸው ብናበቃቸው በእርግጠኝነት ነገ የሀገር መሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሴቶች ማየት እንችላለን። በዚህ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። ሆኖም ደጋግሞ ወደ ታች እያወረድን ስንሄድ ዝቅ እያለ የሚሄድበትን በሚገባ ማየት ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ።
ወረዳ ላይ በአስፈፃሚነት ያሉ ሴቶች 25 ነጥብ 9 ናቸው። በፌዴራል ደረጃ ያለው 50 በመቶ የሴቶች ተሳትፎ እንዳይቀንስ ሥራዎችን ተቀናጅቶ መሥራት ይፈልጋል። በስተኋላ ላይ ቀድመን ያልዘራነውን ማጨድ ስለማንችል ዛሬ ሴቶችን ማብቃት፣ ዕድሎችን ማመቻቸት ይገባል። ሴቶች ሁኔታዎች ስላላመቻቸንላቸውና ዕድል ስላልሰጠናቸው ነው እንጂ ይችላሉ። አሁን ላይ እጅግ ጠንካራ ነገ ሀገር መምራት የምትችል ሴት እያየን ነው። በቀጣይም በዚህ ደረጃ ውጤት የሚያመጣ ሥራ መሥራት አለብን ሲሉ አሳስበዋል።
በዚህ ዙሪያ እንደ ተቋም ያቀድናቸው ዕቅዶች አሉ። በተለይ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ያሉ ታዳጊ ሴቶች አርአያ የሚሆናቸው ይፈልጋሉ። ከዚህ አንፃር የተጀመረ መርሐ ግብር አለ። በቀጣይ ሰፍቶ የሚሄድበት ሁኔታም ተመቻችቷል ብለዋል።
የሴቶች ጥያቄ የመብት ጥያቄ ነው፣ የተሳትፎ ጥያቄ ነው፣ የተጠቃሚነት ጥያቄ ነው። ጥያቄዎቹን ነጣጥለን ማየት የለብንም። የመብት ጥያቄ ስለመለስን ሌላው አብሮ ተመልሷል ተብሎ የሚተው አይደለም። የሴቶች እኩልነት መብት ጥያቄን ካረጋገጥን ሀብት ምንጮች ላይ መጠቀም መብት ያገኛሉ። ኢኮኖሚያቸውንም ያሳድጋሉ። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የማህበራዊ ችግሮቻቸውን እየፈቱ ይሄዳሉ። በመሆኑም የሴቶችን ጥያቄ ነጣጥለን መመለስ የለብንም ይላሉ።
የሴቶችን ጥያቄ አስተሳስሮ ካልተመለሰ ክፍተት ስለሚፈጠር የማህበራዊ ተጠቃሚነቷን በመመለሳችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷ ተመለሰ ማለት አይቻልም። የመብት ጥያቄዋም እንዲሁ ተመለሰ ማለት አይቻልም። በመሆኑም እነዚህን ሳንነጣጥል አብረን አስተሳስረን ልንመልስ ይገባል። ይሄን ለማድረግ በሴቶች መዋቅር የሚሰራው እንደተጠበቀ ሆኖ በየደረጃው ያለው አመራር በያለበት ለሴቷ ጠብ የሚል ነገር መሥራት አለበት። የሚደነቁ ጅምሮች ቢኖሩም አሁን ድረስ ሴቶች በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚያዊውም ሆነ በማህበራዊ መስኩ ተጠቃሚ ነን የሚል የለም። በመሆኑም ጅምሮቹን አጠናክረን ክፍተቶቹን ሞልተን ለመጪው ትውልድ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንችላለን። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ በየደረጃው ያለውን አካላት ትብብር ይፈልጋል ባይ ናቸው።
በምሳሌነት የሚያነሱት ደግሞ የወንዶች አጋርነትን ነው። አሁንም የሴቶች ጥቃት አልቆመም። በመሆኑም ከምን ጊዜውም በላይ የወንዶች አጋርነት እጅግ ያስፈልጋል። ችግሩን ከምንጩ ልናደርቀው ከሆነ ወንዶችን ማሳተፍ የበለጠ ጠቃሚ ነው። ሰጪና ተቀባይ ዓይነት ሳይሆን እኩል ዕድል ሊፈጠርልን እንደሚገባ መረዳት አለባቸው። የጋራ ሀገር እስካለን ድረስ በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ እኩል መሳተፍ እንዳለብን ማወቅ አለባቸው።
ሴቶች ደካማ ስለሆን ሳይሆን ከታች ይዘን የመጣናቸው ችግሮችና ድርብ ኃላፊነቶች አሉብን። ሴቷና ወንዱ በቤት ውስጥ እኩል አይደለንም። እኛ የቢሮም ሥራ እንሰራለን። እቤትም ስንገባ ልጆችና ቤተሰብ ከመንከባከብ ጀምሮ የቤት ውስጥ ሥራ ይጠብቀናል። የገጠር ሴቶች አብዛኛውን ጊዚያቸውን የሚያሳልፉት በቤት ውስጥ ሥራ ነው። በዚህ ላይ የተደረጉ አንዳንድ ጥናቶች ሲያይዋቸው የኢትዮጵያ ሴቶች ስንት ሰዓት ነው የሚሰሩት? ይላሉ። በመሆኑም ወንዱ በቤት ውስጥ ይሄን ጫናዋን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን እንድትጠቀም በማድረግ ሊያግዛት ይገባል።
ሴቶች በዚህ ውስጥ አልፈው ነው ከፍተኛ ስልጣን ላይ ሆነው ሀገራቸውን እየመሩ የሚገኙት። መምራት ታች ከቤተሰብ ከማስተዳደር እንደመጀመሩ እየተለማመድነው ነው የመጣነው። በግሌ ሴቶችን ወደ አመራርነት የሚያመጣ መንግስት ወይም መሪ እጅግ የገባው ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ወንዶች ታማኝ አይደሉም እያልኩ ሳይሆን ሴት የበለጠ ታማኝ ነች። አንድ የቤት ሥራ ከተሰጣት የቤት ሥራው ሳይበላሽ ከግብ እንዲደርስ ትጥራለች። ይሄ ምን ያህል ኃላፊነት የሚሰማት እንደሆነች ነው የሚያሳየው። ከዚህ አንፃር ለሴቶች የወንድ አጋርነት ያስፈልጋል ሲሉም ያብራራሉ። አዎ ወንድ ያለ ሴት እንደማይቆም ሁሉ ሴትም ያለወንድ ውጤታማ ልትሆን አትችልም። ስለሆነም አጋርነታቸውን በስፋት ሊያሳዩዋት ይገባል በማለት ሀሳባችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም