ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ወራሪ ሰራዊት ላይ ያስመዘገበችው አንጸባራቂው የዓድዋ ድል ዛሬ፣ የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም፣ 127 ዓመት ሞላው። ታላቁ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ያደረገና ኢትዮጵያና ድሏ የጭቁኖች የነፃነት ምልክትና መሰረት ሆነው እንዲታዩ ያስቻለ እንዲሁም መላውን ዓለም ያስገረመ ደማቅ ታሪክ በመሆኑ ተደጋግሞ ሊዘከርና ሊዘመርለት ይገባል።
የዓድዋ ድል ለጥቁሮች፣ በተለይም ለአፍሪካውያን፣ የነፃነት ትግል ስለነበረው ፋይዳ ተናግረው የማይጠግቡት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ታቦ ምቤኪ ‹‹የዓድዋ ድል ለትናንት ድሎቻችን ብቻም ሳይሆን ልናሳካቸው ላሰብናቸው አፍሪካዊ እቅዶቻችን ስኬት ታላቅ ስንቅ የሚሆነን አኩሪ ድል ነው›› በማለት በተደጋጋሚ ይናገራሉ፤ ይህን የሚናገሩት ደግሞ የድሉ መታሰቢያ መከበር ከድሉ መንፈስና ዓላማ ለመነጩት አፍሪካዊ እቅዶች ስኬት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው በማመን ነው።
የዓድዋን ድል ስናስብ ጥያቄ የሚያጭሩ ብዙ ጉዳዮች አሉ። የዓድዋ ድል ትርጉሙና በረከቶቹ ብዙ ናቸው፤ ከእነዚህም መካከል ዓድዋና ያለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ጉዞ፣ የዓድዋ ድል አከባበር እና ተያያዥ ጉዳዮች የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው።
የዓድዋ ድል ያስገኛቸውን በረከቶች በሚገባ እንዳላወቅናቸውና እንዳልተጠቀምንባቸው በፅኑ ከሚያምኑና ከሚሞግቱ ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ። ሃሳቤን ለማስረዳት በቅድሚያ ድሉ ካስገኛቸው በረከቶች መካከል ጥቂቶቹን በማስረጃ አስደግፌ ላቅርብ።
በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር በወራሪው የኢጣሊያ መንግሥት ጦር ላይ ያስመዘገበው ድል በዓይነቱ የተለየ ስለነበር መላውን ዓለም ያስገረመ፣ ያስደነቀና ያስደነገጠ ክስተት ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል። ይህ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ዓለም ጭቁኖች የነፃነት ተስፋን የፈነጠቀና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ያደረገ፤ በአንፃሩ ለወራሪው ጦር ደግሞ ሁለገብ ውድመትንና ውርደትን ያስከተለ ድል ነው።
የዓድዋ ድል የአፍሪካ የፀረ-ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎች ምልክት መሆን የቻለ ወሳኝ ታሪካዊ ክዋኔ ነው። ጦርነቱና ድሉ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ በጋራ ተሰልፈው ዓለምን ያስደነቀ ገድል መፈፀማቸውን ለመላው ዓለም ያሳዩበት በመሆኑ ጭቁን ሕዝቦች ለነፃነታቸው በጋራ ሆነው መታገል እንደሚገባቸው ትምህርት የሰጠ ታላቅ ክስተት ነው። የድሉ ትሩፋቶች ለጭቁን ሕዝቦች የነፃነት ትግል ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆነዋል፤ የነፃነት ትግሎቹም ፍሬያማ ይሆኑ ዘንድ የስኬት መንገድን ጠርገዋል።
የዓድዋ ድል በአፍሪካ፣ በካሪቢያንና በእስያ የተካሄዱ የነፃነት ትግሎች እንዲጀመሩና ስኬታማ እንዲሆኑ የጎላ ሚና ነበረው። ይህ ሚናውም በበርካታ የአገራት መሪዎች፣ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች ተመስክሮለታል። ከአህመድ ሴኮ ቱሬ እስከ ኔልሰን ማንዴላ፣ ከክዋሜ ንክሩሁማ እስከ ታቦ ምቤኪ፣ ከዊልያም ኤድዋርድ ዱ ቦይስ እስከ ማርክስ ጋርቬይ፣ ከስቬን ሩቤንሰን እስከ ማሞ ሙጬ፣ ከዶናልድ ናታን ሌቪን እስከ አየለ በከሪ፣ ከቨርጂኒያ ሊ ጃኮብስ እስከ ሮበርት ኔስታ ማርሌይ (ቦብ) … በርካታ የአገራት መሪዎች፣ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች ስለዓድዋ ድል አንፀባራቂነትና በዓድዋ ስለደመቁት ኢትዮጵያውያን ጀግንነት ተናግረዋል፤ ጽፈዋል፤ አዚመዋል፤ ዘፍነዋል!
ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ አገራቸውና ቤታቸው የሚቆጥሯት የአፍሪካ የነፃነት መሪዎች (ኔልሰን ማንዴላ፣ ሮበርት ሙጋቤ እና ሌሎችም) የነፃነት ትግላቸውን ባደረጉባቸው ጊዜያትም ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው የተለያዩ ድጋፎችን አግኝተዋል። እንግዲህ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ እንደነፃነት ምልክት መቆጠሯ በወሬና በንድፈ ሃሳብ የተገለፀ ብቻ ሳይሆን በተግባር የታዬና የተረጋገጠ መሆኑን ነው። የዚህ ሁሉ ምንጭ ደግሞ የዓድዋ ድል ነው። የአብዛኞቹ የዓለም የጭቁኖች የነፃነት ትግሎች መነሻና የስኬት ምንጭ የዓድዋ ድል እንደሆነ አይካድም።
የዓድዋ ድል በተለያዩ የዓለም አገሮች ለተደረጉ የነፃነት ትግሎች መነቃቂያ ከመሆን ባሻገር አገራት ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላ በጭቁኖች ለተቋቋሙ ተቋማት መመስረትም ሚናው የጎላ ነው። ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (Organization of African Unity – OAU) የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት (African Union – AU) ነው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (Organization of African Unity) መመስረት የዓድዋ ድል ውጤት ነው። የድርጅቱን ምስረታ፣ ዋና መስሪያ ቤቱ አዲስ አበባ ላይ የመሆኑንና የአፍሪካ አገራትም በዚህ የመስማማታቸውን ነገር ከዓድዋ ድል ውጭ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፤ አይቻልምም።
ለድርጅቱ መመስረት ምክንያት የሆነው የፓን አፍሪካ ንቅናቄ (Pan-Africanism) የተጠናከረውም በዓድዋ ድል ነው። ምንም እንኳ የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ከዓድዋ ጦርነት ቀድሞ የተጀመረ ቢሆንም፣ በዓድዋ የተገኘው ድል ግን የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጎታል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዓድዋ ድል ውጤት መሆኑ የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን የነፃነት ትግሎችና ከትግሎቹ መጠናቀቅ በኋላ የተመሰረቱ ተቋማት የዓድዋ ድል ደማቅ አሻራ እንዳረፈባቸው ጠቋሚ ምስክር ነው።
የዓድዋ ድል የትብብርንና የአንድነትን ውጤታማነት እንዲሁም ለነፃነት መስዋዕትነት መክፈል ታላቅ ክብር እንደሆነ ያሳየ፣ የነጮች የበላይነት ማክተም እንደሚችልም የጠቆመና መንገድ የከፈተ አንፀባራቂ ክስተትም ነው። ይህን ክብርና መንገድ በጀግንነትና በመስዋዕትነት በታጀበ ተግባር ያሳዩትና የመሩት ኢትዮጵያውያን ደግሞ የጭቁኖች መመኪያ መሆናቸውን አስመስክረዋል።
ጥቁሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ የዓድዋ ድል ትዝታና ስሜት ነበር። ጭቁኖች ኢትዮጵያን የነፃነት ምልክትና የጥቁሮች ሁለተኛ ቤት አድርገው ነው የሚመለከቷት። ‹‹ኢትዮጵያ አገራችን ናት›› ብለው ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት እንቅስቃሴ ሲያደርጉም ነበር። በተለይ ጃማይካዊው የፖለቲካ አክቲቪስትና የመብት ተሟጋች ማርክስ ጋርቬይ በንግግሩም ሆነ በጽሑፉ ላይ ሁሉ ‹‹በባርነት ተይዛችሁ በዘር አድልኦ በሽታ በተጠናወተው ኅብረተሰብ ውስጥ የምትኖሩ ጥቁር አፍሪካውያን በሙሉ ወደ አገራችሁ ወደ አፍሪካ፣ የነፃነት አገር ወደ ሆነችው አገራችሁ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ፊታችሁን ወደ ኢትዮጵያ መልሱ፤ ወደ ጥንት ርስታችሁ አፍሪካ ተመለሱ፤ ዘውዱን የደፋውን ጥቁር ንጉሥ ተመልከቱ፤ እርሱ አዳኛችን ነው›› እያለ መጥቀሱ ኢትዮጵያ የጭቁኖች ተስፋና መመኪያ ተደርጋ መቆጠሯን ያመለክታል።
በድሉ ማግሥት ታላላቅ የአውሮፓ መንግሥታት ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነት መስርተዋል። ከድሉ በፊት ‹‹ኢትዮጵያውያን ኋላ ቀሮች ናቸው›› ብለው ያስቡ የነበሩ አካላት ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነት መስርተው የምጣኔ ሀብትና ወታደራዊ ግንኙነት ለመፍጠር ፍላጎት አሳይተዋል። የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ዋና ከተማ (አዲስ አበባ) የብዙ አውሮፓውያን መንግሥታት ኤምባሲዎች መቀመጫ እንድትሆን እድል ፈጥሯል።
ድሉ ለምጣኔ ሀብታዊ እድገት (ለከተማ እድገት መነቃቃት፣ ለመሰረተ ልማቶች መገንባትና ለሥራ እድል መፈጠር) ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations)ን ጨምሮ የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መስራች አባል እንድትሆን ድሉ ከፍተኛ ሚና ነበረው። በአጠቃላይ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እውቅና እንደታገኝ አስችሏታል።
ከዓድዋ ድል 40 ዓመታት በኋላ የፋሺስት ኢጣሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ሲፈፅም፣ የኢትዮጵያ መወረር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በተለይም በጥቁሮችና በጭቁኖች ዘንድ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገው ከወረራው 40 ዓመታት ቀደም ብሎ የተመዘገበው አንፀባራቂው የዓድዋ ድል ነው። የድሉ ውጤት ኢትዮጵያ በመላው ዓለም እንድትታወቅ ስላደረጋት ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመው ወረራ ኢፍትሐዊና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የጣሰ ተግባር እንደሆነ የሚሰብኩ ድምፆች በመላው ዓለም ተስተጋብተዋል። የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም ለሚገኙ ጭቁኖች ያበረከተው አስተዋፅኦ በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
እስቲ ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትን የዓድዋ ድል ያስገኛቸውን በጎ ውጤቶች (መልካም አጋጣሚዎች) ይዘን፣ ‹‹ድሉ ያስገኛቸውን ትሩፋቶች በሚገባ መንዝረን ተጠቅመንባቸዋል? በድሉ የተገኙ ውጤቶችን በማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች የበለፀገችና ጠንካራ የሆነች አገርን ለመገንባትስ ተጠቅመንባቸዋል?›› የሚለውን ጥያቄ እንፈትሽው።
የዓድዋ ድል ውጤቶችን እያሰብን የኢትዮጵያን ያለፉትን ዓመታት (በተለይ 50 ዓመታት) ጉዞ ስንቃኝ ‹‹ለመሆኑ ኢትዮጵያ/ ኢትዮጵያውያንና የዓድዋ ድል ይተዋወቃሉ?›› ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። አገሪቱ በድህነት፣ በግጭት፣ በጽንፈኝነትና በጦርነት ጎዳናዎች ላይ ደጋግማ የመመላለሷ አሳዛኝ እውነት፣ የዓድዋ ድል ያስገኘላትን በረከቶች መዘንጋቷንና አለመጠቀሟን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ብዙ ሰው ‹‹ … የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ጥቁሩ የኢትዮጵያ ሰራዊት ነጩን የኢጣሊያ ሰራዊት ድል አድርጎ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ከመገዛት ነፃ አወጣት፤ … ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ብቸኛ አገር ሆነች፤ … አባቶቻችን በከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት ተከብረን ኖርን፤ …›› በማለት የዓድዋ ድል አልፋና ኦሜጋ ትርጉም አገርን ከወራሪ ኃይል መጠበቅ ብቻ እንደሆነና ከዚህ የተሻገረ ዓላማ እንዳልነበረው አድርጎ ያወራል/ይፅፋል። እውነታው ግን የዓድዋ ድል አገርን ከጠላት ወረራ ከመጠበቅ ያለፈ ዓላማና ትርጉም አለው።
በእርግጥ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን ከወራሪ ኃይል ጠብቆ የማቆየት አኩሪ ታሪክ መሆኑ ባይካድም፣ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ከወራሪው የኢጣሊያ ጦር ጋር የተፋለሙት ኢትዮጵያን ከወቅቱ ወራሪ ኃይል ለመጠበቅ (ዳር ድንበሯን ለማስከበር) ብቻ ሳይሆን፣ ወራሪው ኃይል ውሎ አድሮ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት በመገንዘብ ያን ጥፋት በእንጭጩ ለመቅጨት ጭምር እንደሆነ መዘንጋትም አይገባም።
ስለዚህ የዓድዋ ድል የመጀመሪያው ውጤት (አበርክቶ) ኢትዮጵያን ከወራሪ ኃይል ጠብቆ ማቆየት ሲሆን ዘላቂው ውጤት ደግሞ ድሉ ያስገኘውን መልካም ፍሬ መንዝሮ ማኅበረሰባዊ ንቃት ያዳበረች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ ልዩነቶችን አስማምታ አንድነቷን የጠበቀች በአጠቃላይ ኃያል የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠርና መገንባት ነበር። ይህን ዘላቂ ውጤት ማሳካት የነበረባቸው ደግሞ ድሉን ካስገኘው ትውልድ ቀጥሎ የመጡት ትውልዶች ነበሩ። በሚያሳዝንና ሁኔታ እነዚህ ትውልዶች ግን ያን ማድረግ አልቻሉም/አልቻልንም። ለዚህ ቀላሉ ማረጋገጫ ደግሞ ኢትዮጵያ ባለፉት 50 (በተለይ 30) ዓመታት ያሳለፈችበት ሁኔታ ነው።
የዓድዋ ድል ምን ማለት እንደሆነ በቀላል ምሳሌ በማስደገፍ እንመልከት። ዚምባብዌና ደቡብ አፍሪካ፣ በተለይ ከመሬትና ሌሎች ሀብቶች ባለቤትነት ጋር በተያያዘ፣ ቅኝ ግዛት ካመጣባቸው ጣጣ ዛሬም ድረስ ሊላቀቁ አልቻሉም። የዚምባብዌው ሮበርት ሙጋቤ መሬትን ከቅኝ ገዢዎቹ ነጮች ነጥቀው ለጥቁሮች መስጠታቸው አገሪቱ ዛሬም ድረስ ልትወጣው ያልቻለችው ከባድ የማዕቀብ አዘቅት ውስጥ ከቷታል። ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ጊዜ እየጠበቀ በሚያገረሽ የመጤ ጠል (Xenophobia) እሳቤ እየተፈተነች ነው።
በአንፃሩ የኢትዮጵያው ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ግን መሬትን የመንግስት የሚያደርገውን አዋጅ ለማወጅ ሲነሱ የገጠማቸው ያደረ የቅኝ ግዛት ጥያቄ/ጫና አልነበረም። [እዚህ ላይ ከታሪክ ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑ ጥቂት ጥራዝ ነጠቆች ኢትዮጵያውያን ባላባቶችንና የመሬት ከበርቴዎችን እንደቅኝ ገዢ የመቁጠራቸው አስቂኝ ጩኸት ከተረትነትና ከቀልድ ያለፈ ትርጉም እንደሌለው ማስታወስ ያስፈልጋል።] ይህም አዋጁን በቀላሉ ለማወጅና ለመተግበር ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። ዓድዋ ማለት እንዲህ ነው/ነበር!
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ነፃነት፣ ክብርና አንድነት ሲሉ በዓድዋና በሌሎች ስፍራዎች ለማመን የሚከብዱ ከባድ ተጋድሎዎችን አድርገው ነፃ አገር ለ‹‹ተተኪው ትውልድ›› ቢያስረክቡም፣ ‹‹ተተኪው በተለይ የአሁኑ ትውልድ›› (በተለይ ልኂቃኑ) ያን ታሪክ ማወቅ አልፈለገም፤ ይባስ ብሎ በብሔርና በሃይማኖት ተከፋፍሎ አገር ለማፍረስ ታጥቆ ሲሰራ ኖረ /አሁንም ይህንኑ የሚሰሩ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ/… ። በዚህም የሰማዕታቱ መስዋእትነት ባከነ፤ ተረሳ።
ታላቁ የዓድዋ ድልም የዚህ አሳዛኝ እጣ ፈንታ ሰለባ ከመሆን አልዳነም። አሁን መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም፣ ‹‹ድሉ የእኛ ብቻ ነው … ድሉ የእነርሱ ነው፤ እኛን አይመለከተንም፤ … እገሌ ለድሉ አስተዋፅዖ አልነበረውም … ›› የሚሉ ረብ የለሽ ጭቅጭቆች በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ በዘር፣ በሃይማኖትና በአመለካከት ሳይከፋፈሉ ዓድዋ ላይ ጠላትን ድል ያደረጉ ልጆች እናት መሆኗን ማሰብና ከዓድዋ ድል በኋላ ባፈራቻቸው ‹‹ልጆቿ›› ምክንያት በአስከፊ የጽንፈኝነት ፖለቲካ ስትታመስ መመልከት እጅግ አሳዛኝና አስገራሚ ተቃርኖ ነው።
በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሰሞን ‹‹ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል … ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን … በቅኝ ግዛት አልተገዛንም … ›› የሚሉ ገለፃዎችን መስማት የተለመደ ነው፤ አሁንም እየሰማን ያለነው ይህንኑ ነው። መገናኛ ብዙኃን ትኩረታቸው በእነዚህ ገለፃዎች የታጀቡ ዜናዎችና ዝግጅቶች ላይ ይሆናል። ይልቅስ በመገናኛ ብዙኃን መነገርና መፃፍ ያለበት ‹‹ከዓድዋ ድል በኋላ የነበሩት ትውልዶች፣ በተለይ የአሁኑ ትውልድ፣ የዓድዋ ድል በረከቶችን ተጠቅሞ ብሄር ግጭና ከልመና የተፋታች ኃያል አገር መገንባት ያልቻለው ለምንድን ነው? የአያት- ቅድመ አያቶቹን ውለታ የበላበት ምክንያትስ ምን ይሆን?›› የሚሉት ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው።
የዓድዋ ድል ያስገኘልንን በረከቶች መንዝረን ተጠቅመንባቸው ቢሆን ኖሮ … ዛሬ በዓባይ ወንዛችን ላይ በምንገነባው ግድባችን ምክንያት ‹‹ጥቅሜ ተነካ›› የሚሉ አካላትና የእነርሱ ወዳጆች ጫና ሊያደርጉብን እንዲሁም ታሪካዊና ሕጋዊ መብታችንን በአደባባይ ሊነጥቁን አይሞክሩም ነበር። [በነገራችን ላይ የዓድዋ ድል በዓባይ ወንዛችን ላይ እየገነባነው እንዳለው ዓይነት ግዙፍ የልማት ስራዎችን እንድንሰራ ስንቅ የሆነ ድል ነበር] … የዓድዋን በረከቶች ብናውቃቸውና ብንጠቀምባቸው ኖሮ በጽንፈኝነት ፖለቲካ የምትታመስ፣ ሚሊዮኖች በችግር የሚሰቃዩባትና የሚፈናቀሉባት …. አገር አትኖረንም ነበር! ለመሆኑ ዓድዋን ማባከናችን የሚቆጨን መቼ ነው?
በየዓመቱ የካቲት 23 በመጣ ቁጥር ስለዓድዋ ድል የተቀነቀኑ ዘፈኖችን እንሰማለን። በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የዓድዋን ተራሮች ደጋግመን ማየት እንዲሁም የዳግማዊ አፄ ምኒልክንና የጦር አበጋዞቻቸውን ጀግነት መስማትም ለምደናል። ነገር ግን የቀደምት አባቶቻችንንና እናቶቻችንን ታሪክ ከመስማት ባለፈ፣ ‹‹ታሪካቸውን ለበጎ ተጠቅመንበታል?›› ብሎ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ‹‹ይህ ትወልድ ለታላቁ የዓድዋ ድል ይመጥናል?›› ተብሎ ሊጠየቅና ሊመረመር ይገባል።
በየዓመቱ የካቲት 23 ሲደርስ ‹‹በአባቶቻችን ጀግንነት እኮራለሁ፤ … ምኒልክ አባቴ፤ ጣይቱ እናቴ … ›› እያሉ ማውራትና መዝፈን ብቻውን ዋጋ የለውም። ቀደምት ኢትዮጵያውያን ባስገኙት ድል መኩራትና ድሉን መዘከር ጥሩ ቢሆንም የድሉን ትሩፋቶች ሳይጠቀሙ፣ ድሀ (ደካማ የሆነች) አገር ይዞ በድሉ ‹‹መኩራት››ና ድሉን ‹‹መዘከር›› ትርጉም የለሽ ድካም ነው። በዓድዋ ለመኩራት ዓድዋን ማወቅና መጠቀም ይገባል!
የዓድዋ ድል በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች ጠንካራና ኃያል አገር ለመገንባት የሚያስችል እምቅ አቅም ያለው ድል መሆኑን መረዳትና መቀበል ያስፈልጋል። የዓድዋን ድል ያስገኘልንን በረከቶች አውቆ እየመነዘሩ መጠቀምና ማኅበረሰባዊ ንቃት ያዳበረች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ ልዩነቶችን አስማምታ አንድነቷን የጠበቀች ኃያል ኢትዮጵያን መፍጠር (መገንባት) የድሉን ትርጉም የማወቅ ንቃት ነው። ይህን በመተግበር ኢትዮጵያን ለታላቁ የዓድዋ ድል የምትመጥን ታላቅ አገር ማድረግ ይገባል!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም