ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ። ሳምንቱ እንዴት ነበር? ይህ ሳምንት የአፍሪካ ኩራት የጥቁር ሕዝቦች ድል የሆነው የዓድዋ ድል የተከበረበት ሳምንት ስለነበር ብዙ የሀገራችሁን የድል ታሪክ የተማራችሁበት እንደነበር እገምታለሁ። እናንተም ልክ እንደ ጥንት አባቶቻችን ሀገራችሁን የምታኮሩ እንቁ እንደምትሆኑ አምናለሁ። ምክንያቱም ጎበዝና ተሰጥዖ ያለው ተማሪ ሁሌም ለሃገሩ ኩራት መሆኑ አይቀርም። ልጆችዬ ዛሬ ያዘጋጃችሁት ጽሑፍ ወላጆቻችሁ ሊያነቡት የሚገባ ጽሑፍ ነው። ወላጆቻችሁ ይህንን ጽሑፍ ካነበቡ በኋላ በትምህርታችሁ ዙሪያ ለናንተ የሚጠቅም ነገር ስለሚያደርጉ እንዲያነቡ ጋብዟቸው እሺ።
ትምህርት ለሰው ልጆች የአዕምሮ እድገት እና የማገናዘብ አቅም መጎልበት እጅግ ወሳኝ መሆኑ በተለያየ ጊዜ ሲነገር እንሰማለን። በእውቀት ያልተገነባና ምክንያታዊነትን ያልተላበሰ አዕምሮ ከሌሎች መግባባት ይቸግረዋል፤ አለፍ ሲልም ሀገር ሊጎዳ የሚችል ጠንቅ ይሆናል። የዛሬ ችግሮቻችንም ከዚህ እውነት የሚመዘዙ እንደሆኑ ማስተዋል አያዳግትም፡፤ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን ከሁሉ በፊት ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል።
ልጆች ሀገር ይረከባሉ ተብለው የሚጠበቁ የነገ ተስፋና ለብዙዎችን የብርሃን ጮራ የሚፈነጥቁ የንፁሕ አዕምሮ ባለቤት ናቸው። ይህ ንፁሕ አዕምሮ ደግሞ ከነጭ ወረቀት ጋር ተመሳሳይነት አለው፤ ነጭ ወረቀት በብዕራችን የፃፍንበትን ሁሉ ይቀበልና አጉልቶ ያሳየናል። ልጆችም እንዲሁ ያሳየናቸውን ያስተማርናቸውን እና የነገርናቸውን አጉልተው ያንፀባርቃሉ። ስለዚህ በእነዚህ ንፁሕ ሕፃናት አዕምሮ ላይ የምንፅፈውን ነገር በጥንቃቄ ማጤን ይኖርብናል።
ወላጆች እንደወላጅ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ልጆች ይዘው የሚወለዱት ንፁሕ አዕምሮ ሁሉን ተቀባይ እንደመሆኑ የሚበጃቸውን መጥኖ ማቀበልና በትምህርታቸው ላይ ትኩረት ሰጥተው ዓላማ ያላቸው ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ብዙ ጊዜ ቤተሰብ የሀገር መሠረት ነው ሲባል እንሰማለን። ይህንን አባባል ከአባባልነቱ አለፍ ብለን ምን ማለት ነው የሚለውን ስንመረምር ግን አይታይም። ቤተሰብ ወደፊት ሀገርን የሚያስተዳድር መሪ፣ ለሀገሩ ዘብ የሚቆም ወታደር፣ ሕዝብን በቅንነት የሚያገለግል ባለሙያ የሚወጣበት ትልቅ ተቋም ነው።
ልጆች እንዲህ ዓይነት ተቋም ሆነው እንዲገነቡ ለማድረግ ደግሞ ቤተሰብ ዛሬ ላይ የሚሠራው የቤት ሥራ ትልቁን ስፍራ ይይዛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልጆች ለትምህርት ያላቸው አመለካከት እየቀነሰ፤ ትኩረት ሰጥተው ዓላማ አስቀምጠው ትምህርታቸውን ለመከታተል ያላቸው ፍላጎት እየተቀዛቀዘ መጥቷል። ከዚያም አለፍ ሲል ያላቸው በራስ መተማመን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠፋ በሌሎች ላይ ተደግፈው የሚጓዙ ራሳቸውን ችለው የማይቆሙ ጥገኞች ወደመሆኑ እየተሻገሩ እንመለከታለን።
ለዚህም የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውጤት አንዱ ማሳያ ነው። እንደሀገር በአጠቃላይ ፈተናውን ለመውሰድ የተመዘገቡ ተማሪዎች ብዛት 985 ሺህ 354 ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ፈተናውን የወሰዱት 896 ሺህ 520 ተማሪዎች ናቸው። 50 በመቶና ከዚያ በላይ በማምጣት ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ለመግባት የሚያስችላቸውን ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ብዛት ግን 29 ሺህ 936 ነው። ከነዚህ ውስጥ 22 ሺህ 936ቱ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ 6 ሺህ 973 ተማሪዎች ደግሞ የማኅበረሰብ ሳይንስ ተማሪዎች ናቸው።
ሙሉ የቀን ትምህርት የሚያስተምሩ 2ሺ959 ትምህርት ቤቶች በፈተናው የተካተቱ ሲሆን ከነዚህ መካከል አንድ ሺህ 798 ትምህርት ቤቶች በአማካይ አንድ ተማሪ ለማሳለፍ ችለዋል። የተቀሩት አንድ ሺህ 161 ትምህርት ቤቶች ግን ምንም ተማሪዎችን ማሳላፍ ያልቻሉ ትምህርት ቤቶች ናቸው።
የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ብሔራዊ ፈተና ከዚህ ቀደም ይሰጥ ከነበረበት የፈተና ሥርዓት በተለየ መልኩ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ቅጥር ግቢ በመግባት የፈተናው ጊዜ እስኪጠናቀቅ እዚያው እንዲቆዩ መደረጉና ፈተናው በዩኒቨርሲቲ መምህራን መሰጠቱ ይታወሳል። ይህም በየግዜው የሚነሳውን የፈተና ስርቆትና የኩረጃ ችግሮችን ከማስቀረት አንፃር ከፍተኛ ለውጦች የተገኙበት ነበር። ነገር ግን ይህ ሃሳብ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ሲገለፅ ብዙ ተማሪዎች አንስተውት የነበረው የተቃውሞ ሀሳብ ልጆች ምን ያህል በራስ መተማመን እንዳነሳቸውና ኩረጃን መሠረታቸው አድርገው እንደሚያስቡ የሚያሳይ ነው።
በሀገራችን ያለው የትምህርት ጥራት ደረጃ፣ ለተማሪዎች የተሟላና ምቹ ትምህርት ቤቶችና የመማሪያ ክፍሎች እንዲሁም ተማሪዎችን ማዕከል ያደረገ የመማር ማስተማር ሥርዓት አለመኖር ልጆች ለትምህርት ያላቸው አመለካከትና ትኩረት ሰጥቶ አለመማር እንዳለ ሆኖ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሠጡት ትኩረት ድጋፍም ከዚህ በማይተናነስ መልኩ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ልጆች ምን ያህል ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው እየተማሩ ነው መከታተልና ተገቢውን ደጋፍ መስጠት አስፈላጊ ነው። ከቤት ዩኒፎርም ለብሶ ከመውጣት ባሻገር ምን ያህል በትምህርታቸው ውጤታማ እየሆኑ ነው የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል። ልጆች በማንም ላይ ጥገኛ ሳይሆኑ ራሳቸውን ችለው ለፈተና እንዲቀርቡ ስነልቦናቸውን ማዳበር ትልቁ የወላጆች ኃላፊነት ነው።
የነገዋን ኢትዮጵያን በእውቀት ጎልብተው እንዲረከቡ ልጆች መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም ወላጅ የራሱን ግዴታ ሊወጣ ይገባል። ከዚያ ባሻገር በብዙ ፈተና ውስጥ አልፈን የምናሳድጋቸውን ልጆች ልፋታችን ከመሬት ወድቆ እንዳይቀርና በዕውቀት የዳበረ አዕምሮ ይዘው የሚያድጉ እንዲሆኑ ክትትልና ቁጥጥር ባይለያቸው መልካም ነው እያልኩ የዛሬ ጽሑፌን በዙሁ አበቃሁ መልካም ሳምንት።
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም