አውሮፓውያን በፈረንጆቹ 1884 እና 1885 በጀርመን በርሊንግ ከተማ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ከፋፍለው በቅኝ ግዛት ለመቀራመት የአህጉሪቷን ካርታ ዘርግተው ዕጣ ተጣጣሉ። ሕልማቸው ሰምሮም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የአፍሪካ ሀገራትን በቅኝ ግዛት ሥር አዋሉ። ኢትዮጵያን ለመውረር ቀይ ባሕርን አቋርጦ የመጣው የጣሊያን ወራሪ ጦር ግን ያልጠበቀው ዱብዳ ገጠመው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአራቱም ማዕዘን ቀፎው እንደተነካ ንብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ በ1888 ዓ.ም የካቲት 23 ቀን (ከ1895 እስከ 1896 እ.ኤ.አ.) ዓድዋ ላይ የጣሊያንን ጦር ገጥሞ ድል ያደረገበት 127ኛው የዓድዋ ድል በዓል እነሆ ዘንድሮ “አንድነት፣ ጀግንነት እና ጽናት!” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ በደማቅ ሥነሥርዓት ተከብሯል፤ ከኢትዮጵያም አልፎ በአውሮፓና በአሜሪካ አደባባይ በዓሉ ተከብሯል።
ይህን የመላው የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ቀንዲልና የትግል ዓርማ የሆነውን የዓድዋ ድል በዓል በየዓመቱ ታሪኩን በመዘከር በኩል ብዙ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ድሉ ግን ከዚህም ባለፈ መልኩ መዘከር ይኖርበታል፡፡ ብዙ ሊዘክሩት የሚገባቸው ተግባሮች መከናወን ይኖርባቸዋል ሲባልም ቆይቷል፤ ይህን ተከትሎም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግዙፍ ሙዚየም እየገነባ ነው፡፡ በትግራይ ክልል በዓድዋ ከተማም የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሰቲ ለመገንባት የተጀማመሩ ሥራዎች እንደነበሩም ይታወቃል፡፡
ድሉን ለተለያዩ ምጣኔ ሀብታዊ ዓላማዎች ማዋል እንደሚቻልም እየተገለጸ ነው፡፡ በተለይ ለቱሪዝም ዘርፉ በማዋል ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል በተለያዩ ወገኖች ይጠቆማል፡፡
የቱሪዝም ከፍተኛ ባለሙያና ተመራማሪው አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) እንደሚሉት ፤ የዓድዋ ድል ታሪካዊ ዳራን ስንመለከት በዓሉ የመላው የጥቁር ሕዝብ የድል በዓል ነው። ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ጦር ዓድዋ ላይ ገጥመው ድል ያደረጉት የአፍሪካ ሀገሮች በሙሉ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ውስጥ እያሉ ነበር። ይህ ድል ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች “ለካ ጥቁሮች በነጮች ላይ ድል መቀዳጀት ይችላሉ” የሚለውን ግንዛቤ ወስደው ለነጻነታቸው ለመታገልና ነጻነታቸውን ለማወጅ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሮላቸዋል፤ በርም ከፍቶላቸዋል። በዚህም የአፍሪካ ሀገሮች ኢትዮጵያን የነፃነታቸው ዓርማ አድርገው ስለሚቆጥሯት ከ29 በላይ ሀገራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በተለያየ መልኩ ብሔራዊ ዓርማቸው አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
በመሆኑም ይህን የመላ የጥቁር ሕዝብ የድል በዓል በየዓመቱ ታሪኩን ዘክሮ ከማለፍ ባለፈ እሴት ተጨምሮበት ለሀገርና ለሕዝብ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ እንዲሰጥ ማድረግ የሚቻልባቸው ፈርጀ ብዙ መንገዶች አሉ ። ከነዚህ መካከል የዓድዋ ድል በዓልን እንዲሁም ድሉ የተገኘበት ቦታን ለቱሪስት መስሕብነት በማዋል ከዘርፉ ከፍተኛ ገቢ ማግኝት፣ በዚህም ማኅበረሰቡንም መጠቀም ይቻላል።
ለዚህም ጦርነቱ የተካሄደበት ወይም ድሉ የተገኝበት ቦታ ዓድዋ ነው። በዚህ ቦታ ላይ በዓመት አንድ ጊዜ በዓሉን ከመዘከር ባለፈ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች ዓመቱን ሙሉ በቦታው ተገኝተው እንዲጎበኙ ቦታውን ማልማት ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ሲሳይ፣ ቦታውን የቱሪስት መስሕብ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ማግኝት ይቻላል ይላሉ።
እንደ ዶክተር አያሌው ገለጻ፤ ሌላው የጦርነቱ የታሪክ አካል የሆኑ መልክዓ ምድሮችን፣ ከፍተኛ የጦር አመራሮች የተሰዉባቸውን ቦታዎች፣ ወ.ዘ.ተ ታሪኩን መሠረት አድርጎ በማልማት የቱሪስት መስሕብ ማድረግ ይቻላል። ለአብነት የውጫሌ ስምምነት የት ተካሄደ? ስምምነቱ እንዴት ፈረሰ? ጄኔራል አልቤርቶኒ የተማረከበት እና ጄኔራል ዳቦርሜዳ የተገደለበት ቦታ የት ነበር? እንዲሁም ሶሎዳ፣ አባ ገሪማ፣ ኪዳነምሕረት፣ ራዕይዩ የሚባሉ ጦርነት የተካሄደባቸው ተራራዎች ላይ ምን ምን ታሪክ በቦታው እንደተሠራ? በሚገልጽ መልኩ በማልማት የቱሪስት ሳይት ማዘጋጀት ይቻላል። በተለይ እነዚህ ቦታዎች የእግር ጉዞ አድርገው ለሚጎበኙ ጎብኝዎች ተመራጭና ሳቢ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ ያኔ ምንም ዓይነት የመገናኛ ወይም የመረጃ መለዋወጫ ቴክኖሎጂ በሌለበት በአጭር ጊዜ ውስጥ “እንዴት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የክተት አዋጁን ተቀብለው ወረኢሉ ከተው ጠላትን ሊመክቱ ቻሉ” የሚለው በራሱ አንድ የቱሪስት መስሕብ የሚሆን ታሪክ ነው። ስለዚህ መጀመሪያ አምባላጌ ላይ የተደረገው ጦርነት ምን ይመስል ነበር? ከአምባ ላጌ ቀጥሎ ጦርነቱ ወደ መቀሌ እንዴት አመራ? ከመቀሌስ እንዴት ወደ ዓድዋ ጦርነቱ አምርቶ መቋጫ አገኝ? የኢትዮጵያ ጦር የዓድዋ ተራራን በምን መልኩ እንደተገን ተጠቅሞ ድል ሊያደርግ ቻለ? የሚሉትን በሙሉ የጦርነቱን ታሪክ የሚተርክ የቱሪስት መምሪያ መጽሐፍ (Tourist guide book) ቢዘጋጅ ታሪኩ የሀገር ውስጥንም የውጭውንም ጎብኚ የሚመስጥ ይሆናል። በዚህም ራሳቸውን ጣሊያኖችንም መሳብ ይቻላል። የሌላውንም ዓለም ቀልብ ይገዛል።
በዚህም “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ ድሉ የተገኝበት ቦታ፣ የጦርነቱ አካል የሆኑ ታሪካዊ ቦታዎችን እና መልክዓ ምድሮችን ጎብኚዎች ለመጎብኝት ወደ ቦታው ሲያቀኑ እግረ መንገዳቸውን በአካባቢው ያሉ ሌሎች የቱሪስት መስሕብ ቦታዎችን ይጎበኛሉ። ይህም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ኢኮኖሚ መነቃቃት ትልቅ ፋይዳ የሚኖረው ከመሆኑ በዘለለ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል።
ከዚህ አኳያ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሑራን ጦርነቱ ከተካሄደባቸው የዓድዋ ተራራዎች አንዱ የሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻ ቦታ እንዲሆን ለማስቻል ጥናት አካሂደው ነበር። ታሪካዊ ዳራውን መሠረት ያደረገ ደረጃውን የጠበቀ የቱሪስት መምሪያ ተዘጋጅቶ ለአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ለአስጎብኚዎች እንዲሁም ለቄሶች ጭምር ስልጠና ተሰጥቶ ነበር። በዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ “ቦታው የቱሪስት መዳረሻ ሊሆንልን ነው” ብሎ ደስ ብሎት በጣም ተስፋ አድርጎ ነበር።
ጥናቱ ግን ወደ ተግባር ሳይቀየር ቀርቷል ያሉት ዶክተር አያሌው፣ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደውን ጥናት መሠረት በማድረግ ቦታውን አልምቶ ወደ ቱሪስት መዳረሻነት በመቀየር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ወደሚያስገኝ መንገድ መቀየር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ከኅዳር አጋማሽ እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያለበት ወቅት መሆኑን የሚናገሩት የቱሪዝም ባለሙያው፤ እነዚህ ወራት በተለይ በምዕራቡ የዓለም ክፍል በጣም ቀዝቃዛና በረዷማ ወቅት ናቸው። በዚህ ወቅት ምዕራባውያን ከዚህ የአየር ንብረት ለመራቅ ሞቃታማ የአየር ንብረት ወዳላቸው ሀገሮች ለጉብኝት ይጎርፋሉ። በዚህ ወቅት ለጎብኚዎች ተመራጭ ከሆኑ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ በግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት ሲሉ ያብራራሉ።
ምክንያቱ ደግሞ በነዚህ ወራት የአየር ንብረቷ ተስማሚ ከመሆኑ ባለፈ እንደ ገና እና ጥምቀት ያሉ ኃይማኖታዊና የአደባባይ በዓላት የሚከበርበት ወቅት በመሆኑ ነው ያሉት ዶክተር አያሌው፣ ስለዚህ በዚህ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የውጭ ጎብኚ ወደ ሀገሪቱ ይገባል። በአንጻሩ በዩ.ኒ.ስ.ኮ በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል በዓል የሚከበረው መስከረም ወር ላይ ነው። ይህ ወር በምዕራባውያን ዘንድ ሞቃታማና ተስማሚ የአየር ንብረት ያለበት ወቅት ስለሆነ እምብዛም የውጭ ጎብኚዎች በበዓሉ አይታደሙም። ስለዚህ ከኅዳር አጋማሽ ጀምሮ ታኅሣሥ፣ ጥርና የካቲት ወራት በሀገሪቱ ከፍተኛ የጎብኚዎች ፍሰት ያለበት ወቅት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
በመሆኑም የዓድዋ ድል በዓል የሚከበረው ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያለበት ወቅት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ስለዚህ እንደ መስቀል፣ ጥምቀት፣ ኢሬቻ፣ ጨምበላላ ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ የአደባባይ በዓላት ሁሉ የዓድዋ ድል በዓልን በተመሳሳይ መልኩ በማክበር የቱሪስት መስሕብ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ማመቻቸት እንዳለባቸው ሲሉ ያመለክታሉ። ምክንያቱም የውጭ ጎብኚዎች ለገናና ለጥምቀት በዓላት ወደ ሀገሪቱ በከፍተኛ መጠን የሚገቡበት ወቅት ስለሆነ ቱሪስቶቹ በቀላሉ የቆይታ ጊዜያቸውን አራዝመው የዓድዋ ድል በዓልን እንዲታደሙና የዓድዋ የቱሪስት መስሕብ ስፍራዎችን እንዲጎበኝ ማድረግ ይቻላል ይላሉ።
የዓድዋ ድል በዓልን የቱሪስት መስሕብ ለማድረግ ከዚህ ቀደም እዚህ ግባ የሚባል ሥራ እንዳልተሠራም ጠቅሰው፣ ስለዚህ ድሉን በየዓመቱ ከመዘከር ባለፈ የቱሪስት መስሕብ ለማድረግ የበዓሉ አከባበርና የማስተዋወቅ ሥራው ምን መምሰል እንዳለበት? ለወደፊቱ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሌላው ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ አንጻር “እንዴት የዓድዋ ድል በዓልን ለቱሪስት መስሕብነት ማዋል ይቻላል” በሚለው ላይ የቱሪዝም ባለሙያው ዶክተር አያሌው እንዳብራሩት፤ ምዕራባውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት ተቆጣጥረው የባሪያ ንግድ ሲያጧጡፉ በነበረበት ወቅ ጋናን የባሪያ ንግድ አስኳል አድርገው ገበያውን ያጧጡፉት ነበር። ጋና ይህን ጥቁር ጠባሳዋን “Root of Slave Tread” በሚል ለቱሪስት መስሕብነት እያዋለችው ትገኛለች። ይህም ጋናዎች “አሁን ያሉት የምዕራባውያን ዜጎች አባቶቻቸው የባሪያ ንግድ ይፈጽሙበት የነበረውን ቦታ በመጎብኘት ለተበዳዩ የጥቁር ሕዝብ በቱሪዝሙ መካስ አለበት” ብለው የፈጠሩት የቱሪዝም መስሕብ ነው። በዚህም ጋና ይህ ሥፍራዋ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የምታገኝበት አንዱ ምንጯ ነው።
ስለዚህ ጋና ጥቁር ጠባሳዋን ወደ ገቢ ምንጭነት መቀየር ችላለች። ነገር ግን ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ቀንዲልና የትግል ዓርማ የሆነውን የዓድዋ ድል በዓልን ከመዘከር ባለፈ ፋይዳ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በሚያስገኝ መልኩ አልቀየረችውም። ስለዚህ ከጋና እንዲሁም ከሌሎች ሀገሮች ልምድ በመቅሰም ይህን ታላቅ የመላ ጥቁር ሕዝብ የድል በዓል ለቱሪዝም መስሕብነት ማዋል የሚቻልበት ዘርፈብዙ እድሎች አሉ ሲሉ ይጠቁማሉ።
የመጀመሪያው ልክ እንደጋና አሁን ያለውን የጣሊያን ትውልድ በወንድማማችነት መንፈስ ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ በመጋበዝ ትናንት አያት ቅድመ አያቶቻቸው የወደቁበትን ቦታ እንዲጎበኙ እና በዓሉን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንዲያከብሩ በማድረግ የቱሪስት ፍሰቱን ከማሳደግ ባለፈ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ማድረግ እንደሚቻል ዶክተር አያሌው አመልክተዋል። በዓሉን ከሀገሪቱ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ዐውድ ጋር በተስማማ መልኩ በየዓመቱ በማዘጋጀት በቱሪስት ተመራጭ የሆነ መስሕብ ማድረግ እንደሚቻልም ይጠቁማሉ። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተገነባ እንዳለው የዓድዋ ሙዚየም ያሉ ፕሮጀክቶች ነገ ላይ በከፍተኛ መጠን የሀገሪቱን የቱሪስት ፍሰት የሚጨምሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ስለዚህ መሰል ፕሮጀክቶችን ማስፋት ያስፈልጋል ይላሉ።
በአጠቃላይ በዓሉ ከኢትዮጵያ አልፎ በአውሮፓና በአሜሪካ አደባባይ በድምቀት መከበሩ በዓሉን በስፋት ለዓለም ሕዝብ በማስተዋወቅ የቱሪስት መስሕብ ለማድረግ ትልቅ እድል ይፈጥራል። በመሆኑም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዓሉን ሲያከብሩ የጀግኖች አባቶቻቸውን የጦር ሜዳ አልባሳት ለብሰው ባሕላቸውን ከማሳየት ባለፈ በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ስትራቴጂ ነድፈው ድሉን ለዓለም ማኅበረሰብ በማስተዋወቅ ለበዓሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ ወደ እናት ሀገራቸው እንዲመጣ ማድረግ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።
በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን በማስተባበር ያለምንም ወጪ እነርሱን ተጠቅሞ በዓሉን በከፍተኛ ሁኔታ የማስተዋወቅ ዘመቻ ማከናወን እንደሚቻል አመልክተው፣ ስለዚህ “በእጅ የያዙት ወርቅ …” እንዲሉ “ዓድዋ በእጃችን ያለ ነገር ግን ያልተጠቀምንበት ጭስ አልባው የኢንዱስትሪ ወርቅ ነው። ይህን በእጃችን ያለ ወርቅ እሴት ጨምሮ በማልማት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሀገር ማግኘት” እንደሚቻል የቱሪዝም ባለሙያው ይናገራሉ።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም