በአገራችን የአውዳት መምጣትን ተከትሎ የመወያያ አጀንዳነቱን ስፍራ የሚረከበው የገበያና ግብይት ጉዳይ ነው። የበዓሉን ልዩ ባህርይና የማህበረ-ባህላዊ አውዱን መሰረት የሚያደርገውን የሸማቾች ፍላጎት ተንተርሶ የሀገራችን ገበያና ውሎ ይደምቃል። በተለይ አዲስ አበባንና ሌሎች ከተሞቻችንን ትክ ብሎ ለተመለከተ ሰው እያየ ያለው መለስተኛ ቴአትር ቢጤ ቢመስለው አይደንቅም። ከፋብሪካ ውጤቶች እስከ ባህላዊ፣ ከሰንጋ እስከ ዶሮና እንቁላል፣ ከአልባሳት እስከ ጌጣጌጦች ወዘተ ከመደብር አልፎ እስከ አውራ መንገዶች ሁሉ የገበያ ማእከላት የሚሆኑት ለዚሁ ለአውዳመትና በአውዳመት ገበያ ወቅት ነው።
መጪውን ፋሲካ ተከትሎ እያስተዋልን ያለነውም ይህንኑ ነው። በከተማዋ ከነባሮቹ ጉሊቶች ባለፈ ድንኳኖች ተደኩነዋል፣ መደብሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ አሸብርቀው ደንበኞቻቸውን እያስተናገዱ ነው፤ «የ . . . % ታላቅ ቅናሽ አድርገናል» ማስታወቂያዎች ጊዜያቸው አሁንና አሁን ብቻ ይመስል ባሸበረቀ መልኩ በተገኙት ክፍት ቦታዎች ላይ ሁሉ ተለጥፈው «አንብቡኝ፣ አንብቡኝ፤ ግቡናም ግዙ» እያሉ ነው። ዝርዝሩ ብዙ ነው።
ፒያሳ አካባቢ ካገኘናቸው ሸማቾች አንዱ አቶ ባንጃው ተሰማ ይባላሉ። እድሜያቸው ወደ 60ዎቹ እየተጠጋ ሲሆን፣ የብዙ ዓመት የበዓልና ግብይት ልምድ አላቸው። ለልጆቻቸው ጫማ ገዝተው ሲወጡ ነው ያገኘናቸው። «እንዴት ነው የታላቅ ቅናሹ ነገር?» አልናቸው፤ «ተጠቃሚ እየሆኑ ነው?» ስንልም አከልንበት። መልሳቸው ፈገግታ ነበር፤ ከዛም «እዚህ የወጣ ዋጋ ሲወርድ የማይታይበት አገር ነው ታላቅ
ቅናሽ የሚደረገው? እኔ ለልጆቼ መግዛት ስላለብኝ ገዛሁ እንጂ ቅናሽ የምትለውን ነገር ተወው» አሉኝ፡፡ አመስግኜ ተለያየን።
መርካቶ ለህፃናት ልብሶችን ሲገዙ ያገኘናቸው እናትም የሰጡን መልስ ከዚህ የተለየ አይደለም። መልሳቸው አጭር ነው፤«ቅናሽ የሚሉት አውቀው እላይ ያወጡትና መልሰው ዋጋው ላይ ነው የሚያስቀምጡት። ስንገዛ እኮ ነው የኖርነው፤ እናውቀዋለን።» ከዚህ የተለየና «ቅናሹ ልክ ነው፤ ተጠቃሚ አድርጎኛል» የሚል መልስ ያላገኘን በመሆኑ በዚሁ እንለፈውና ወደ «ቀናሾቹ» እንሂድ።
ስፍራው ከስድስት ኪሎ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ ዳር ሲሆን፣ መደብሩ ሁለገብ የሚሉት አይነት ነው። በ«15% ታላቅ ቅናሽ» ተሽቆጥቁጧል። ወደውስጥ ዘልቀን አስተናጋጇን ስለገበያው ሁኔታ ጠየቅናት፡፡ ምንም እንደማይል ከነገረችን በኋላ «ይሀ ቅናሽ ትክክለኛ ስለመሆኑ የሚጠራጠሩ አሉና አንቺ ምን ትያለሽ?» አልናት። እሷ ተቀጣሪ ሠራተኛ እንጂ ባለቤት እንዳልሆነች ነግራን እውነተኛ ሊሆን እንደሚችል ከመገመት ባለፈ ሌላ ልትል እንደማትችል ነግራን ተለያየን።
መነን አካባቢ (በተለምዶ አርከበ ሱቅ) የሚባሉት ውስጥ የሚሸጥና «ታላቅ ቅናሽ» ወደ ለጠፈ ሰው ጎራ አልን፤ በአጋጣሚ የንግዱ ባለቤት ነው፡፡ ከብዙ ውይይት በኋላ እውነትም ቅናሽ ማድረጉን አረጋጦልን ተለያየን፡፡
ኢኮኖሚያዊ ፍትሃዊነት፣ እኩል ተጠቃሚነት ያለው የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ሥርዓት ከሚለካባቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ የግብይት ሥርዓት ነው። እንደሚታወቀው ሸማች ገንዘብ ይዞ ወደ ሸመታ የሚሄደው ለፍቶ፣ ጥሮና ግሮ ያገኘውን ገንዘብ ነው። በመሆኑም ይህንን ገንዘቡን ዝም ብሎ ሊበትነው አይፈልግም፤ መሆንም አይገባውም። የግብይት ፍልስፍና እንደሚያስተምረው በሁለቱ ወገኖች መካከል ሥርዓታዊ ግብይት የግድ ያስፈልጋል።
ይህ በልፋት የተገኘ ገንዘብ የሸማቹን የመግዛት አቅም የሚያሳድግ መሆን አለበት፡፡ በሌላ አባባል የሸማቹ ገንዘብ ተገቢውን ዋጋ ማግኘትና ለሸማቹም ተገቢውን ጥቅምና አገልግሎት መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም ነው ሸማች አባካኝ የወጪ ልምድን በማስወገድ ገንዘቡ ትክክለኛ ዋጋ እንዲኖረው የማድረግ ግንዛቤን (ባለሙያዎች «እሴት» ይሉታል) ማዳበር አለበት የሚባለው፡፡
ሸማች የንግድ እቃ ወይም የአገልግሎት ዋጋ የጥራት ደረጃ እና አጠቃቀም እንዲሁም ከሚሰጡት ጠቀሜታ አንፃር ከሌሎች ተወዳዳሪ የንግድ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ጋር የሚገዛውን እቃም ሆነ ሸቀጥ የማወዳደር ባህል ሊያዳብር ይገባል እየተባለ በባለ ሙያዎች መመከሩም ያለ ምክንያት አይደለም።
የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የተገኘ ሰነድ «ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ስምንት የሸማቾች መብቶች» በማለት ያስቀመጣቸው ነጥቦች ያሉ ሲሆን፤ እነሱም:- 1. መሠረታዊ ፍላጎት የማሟላት፣ 2. የደህንነት መብት፣ 3. መረጃ የማግኘት መብት፣ 4. አማረጦ የመግዛት መብት፣ 5. የውክልና መብት፣ 6. የመክሰስ መብት፣ 7. ትምህርት የማግኘት መብት እና 8. በጤናማ አካባቢ የመኖር መብት መሆናቸውን ዘርዝሯል።
በአገራችንም በአዋጅ ቁጥር 813/2006 መሰረት ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ብሎ ከለያቸውና ነጋዴዎች መፈፀም ከሌለባቸው ተግባራት ውስጥ ስለ ዋጋ ሐሰተኛና አሳሳች መረጃ አለማስተላለፍ ግልፅ ክልከላ አለ፡፡ ሸማቹ ስለሚገበያየው ዕቃ ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብትን አጎናፅፎታል፡፡ ነገር ግን በታላቅ ቅናሽ ስም የሚደረጉ የተሳሳቱ ማስታወቂያዎች የሸማቹን ህብረተሰብ መብት የሚጥሱ ናቸው፡፡
ስለዋጋ ቅናሽ ሐሰተኛና ትክክለኛ መረጃ መስጠት የተከለከለ ድርጊት መሆኑ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ ይህን ተላልፎ የተገኘ ሻጭም ቀጥታ የወንጀል ተጠያቂነት አለበት፡፡ በዚህም ከአምስት እስከ 10 በመቶ ዓመታዊ የሽያጭ ገቢውን በገንዘብ ሊቀጣና ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ሊቀጣ ይችላል፡፡
ድርጊቱ ሲፈፀም ባለሥልጣኑ ቅሬታዎች ተቀብሎ ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣን ቢሰጠውም መርምሮ የመክሰስ ሥልጣን በአቅራቢያው ያለው የፖሊስ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ቅናሽ ሳይኖር እንዳለ አድርጎ ማቅረብ፣ በአንዳንድ መደብሮች ቅናሽ የተደረገው በውስን ምርቶች ላይ ሆኖ በሁሉም ላይ እንዳለ ማስመሰል የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ያገለገሉ ዕቃዎችን እንደ አዲስ አድርጎ በታላቅ ቅናሽ ማቅረብ አዋጁን የሚፃረሩ ተግባራት ሲከናወኑ ይስተዋላሉ፡፡ ባለሥልጣኑም በመገናኛ ብዙኃን የሚነገሩትን ማጣራት ያደርግባቸዋል፡፡ እንደ ችግሩም የማገድና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡
በአጠቃላይ ቀንሻለሁ ባይ የንግድስ ተቋማትና በኩባንያዎች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እና መሠረታዊ የሸማች መብቶች እንዳይጣስ ድምፃቸውን ማሰማት ይጠበቅባቸዋል ተብለው የሚታመኑት የሸማቾች ማህበራት ናቸው። ሸማቾችም ማህበራትን ከማቋቋምና ከማደራጀት አኳያ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። ማህበራቱም ከመንግሥት ጎን በመሆን የሸማቹን ህብረተሰብ መብት ከማስጠበቅ እና ህጋዊ የግብይት ሥርዓትን ከማስፈን አኳያ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2011
በግርማ መንግሥቴ