በጠዋት የሚጀምረው ኳኳታ እንደወፎቹ ዝማሬ ከእንቅልፋ ማልዶ ይቀሰቅሳታል። ለማኝ ምን ሲያደርግ….. በሚባልበት ሰዓት ተነስትው በውደቀት የሚገቡት የሱማሌ ተራ ሰፈር ነዋሪዎች እንቅልፍ ያላቸው አይመስሉም። ነጋዴው፣ ሠራተኛው፣ ሌባና ቀማኛውም እኩል በሱማሌ ተራ መንገዶች ይርመሰመሳሉ። ሱነሜ አሕመድም ማልዶ ከቤቱ የወጣውን ሰው ለመመገብ እስከ እኩለ ሌሊት ያዘጋጀችውን ሳንቡሳና ፓስቲ ይዛ በመንገዱ ዳር ትቆማለች።
ያፈላችውን ሻይና ቡና በፔርሙዝ ይዛ፤በመጥበሻ ላይ በሚፈላ ዘይት ውስጥ ለመጥበስ ያዘጋጀችውን የሳንቡሳና የፓስቲ ሊጥ እያድቦለቦለች በፈገግታ አላፊ አግዳሚውን ትጋብዛለች። ማለዳ ላይ ቁርስ ለሚፈልገው ሰው በሙሉ ቁርስ አብልታ ስትጨርስ ደግሞ ለምሳ የሚሆኗትን ፈጣን ምግቦች ማዘጋጀት ትጀምራለች።
እርጥብ ፤ ዳቦ በአትክልትና ሌሎች ፈጣን በሱማሌ ተራ ጥድፊያ ውስጥ የሚሠሩትን ሠራተኞች መግቦ ወደ ሥራ የሚያስገባ ምግብን ታዘጋጃለች። ሰዓቱ እንደተጠናቀቀ ወደ የቤቱ ሊገባ የተዘጋጀው ሠራተኛ አፉ ላይ ጣል እያደረገ የሚያልፋቸወን ምግቦች እየሠራች ሙሉ ቀን በትጋት ታሳልፋለች። የእለቱ ሥራ ሲያበቃ ደግሞ ቤቷ ገብታ ለነገ የሚሆነውን ስታዘጋጅ እስከ እኩለ ሌሊት ታመሻለች። በዚህ ሁሉ ጥረት ውስጥ ነገን የተሻለ ለማድረግ ሕልሟን ሰንቃ የምትሠራው ሱነሜ አንድም ቀን የከፋ ነገር ይገጥመኛል ብላ አስባ አታውቅም ነበር።
የሱኔሜ የሕይወት ጅማሬ
ከተወለደችበት ስልጤ አካባቢ አክስቷን ተከትላ አዲስ አበባ የገባችው በልጅነቷ ነበር። ከአክስቷ ጋር ስትኖርም ሥራ ከመሥራት ባለፈ ለትምህርትና ለሌላ ነገር ምንም ጊዜ አልነበራትም። እድሜዋ እየጨመረ ሲሄድ ዓረብ ሀገር ሄዳ የተወሰነ ጥሪት ለመያዝ ትታትር ጀመር። ለሁለት ዓመታት ብቻ እንደሠራች ያሳደገቻት አክስቷ በጠና መታመሟን ሰምታ ወደ ሀገር ቤት ተመለሰች።
አክስቷ ምንም ልጅ ያልነበራት በመሆኑ እሷው አስታማ ሕይወቷ ሲያልፍ በወገ ማዕረግ ሸኝታለች። በመቀጠል የያዘቻትን ጥሪት በመያዘ አክሰቷ ትሠራው የነበረውን ሥራ በመሥራት ሕይወቷን ለመቀየር ትታትር ጀመር።
ከዓረብ ሀገር ስትመለስ የተለያዩ እንደ ቴሌቪዥን፤ ጂፓዝ ቴፕ እና የመሳሰሉ ኤሌክትሮኒክሶችን ጨምሮ በርካታ ነገ የትዳር ሕይወት ውስጥ ስገባ ያገለግለኛል ያለቻቸውን እቃዎች ይዛ ተመለሰች። በርካታ ብርድ ልብሶች እና ያልጋ ልብሶች ቢኖሯትም ነገ የተሻለ ነገር ላይ ስሆን እለብሳቸዋለሁ ብላ በአሮጌው የአክስቷ አልጋ ላይ አሮጌ ብርድ ልብሷን ለብሳ ትተኛ ነበር።
ምንም አይነት ምቾት ሳትፈልግ ነገን ውብ ለማድረግ የምትታትረው ይህች ወጣት ሳይሠሩ የሚያድሩ፤ የሰውን በመቀማት የሚደሰቱ ግለሰቦች ዓይን ውስጥ ገባች። ሥራዋ ላይ ትኩረት አድርጋ የምትታትረው ሱነሜ አንድም ቀን ሰው እየተከታተለኝ ነው ብላ አስባ አታውቅም ነበር።
ዘወትር ከሥራ ወደ ቤት ከቤት ወደ ሥራ እንጂ ቀና ብላ ማንንም አታይም ነበር። በብዛት ብቻዋን ገባ ወጣ ማለቷ ክፋት በልባቸው ሰንቀው ለሚከታተሏት ወጣቶች የልብ ልብ እየሰጣቸው ነው። በየቀኑ ብቻዋን ያውም በጥድፊያ ወጣ ገባ የምትለዋን ወጣት አጥምዶ ለመጣል ምቹ ጊዜን መጠበቅ ጀመሩ።
ቀማኞቹ
ቀማኞቹ ወንድወሰን ተስፋዬና በረከት በዛብህ ይባላሉ። በሱማሌ ተራ አካባቢ የመኪና አካል በመስረቅ የሚተዳደሩ ወጣቶች ናቸው። ከመኪና እስፖኪዮ እስከ ዝናብ መጥረጊያ ባስ ሲልም ጎማ እስከ መፍታት መኪናዋን ሙሉ ለሙሉ እስከማረድ የሚደርሱ ዓይነት ዓይን ያወጡ የሰው ንብረትን ፍለጋ የሚቅበዘበዙ ሌቦች ነበሩ።
ለሚሠሩት እኩይ ሥራ እንዲያመቻቸው ሦስት በመሆን እዛው ሱማሌ ተራ አካበቢ ተከራይተው ይኖሩ ነበር። በሂደት ከሰፈሩ ሰው ጋር መላመድ የአካባቢውንም ሰው የእለት ከእለት እንቀስቃሴ በመመልከት ከመኪና መለዋወጫ ስርቆት በተጨማሪ ኪስ ማውለቁንም ተያያዙት።
በዚህ መካከል ሱነሜ ዓረብ ሀገር ደርሳ እንደመጣችና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ይዛ መምጣቷን ሰሙ። ይሄን ጊዜ ይህች ወጣት ከማን ጋር እንደምትኖር፤ በስስት ያስቀመጠቻቸው ንብረቶቿ ምን ምን እንደሆኑ ማጥናት ጀመሩ። በአካባቢውም ሲያንዣብቡ ለራሷ መጠቀም ሰስታ ነገዬን ውብ አደርግባቸዋለሁ በማለት ከሻንጣና ከበርሜል ያላወጣቻቸው በስደት ያፈራችውን ንብረት ለመቀማት ቀን ቆረጡ።
የጥፋት ቀጠሮ
የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ፒያሳ ሱማሌ ተራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው። ወንድወሰንና በረከት ከሌላ አንድ ግብረ አበራቸው ጋር በመሆን ሱነሜ ቤቷ ገብታ ለነገ የሚሆናትን የምግብ ግብዓት አዘጋጅታ እስክትጨርስ አድፍጠው ይጠብቁ ጀመር። አንዱ ግብረ አበራቸው ደጅ እንዲቆም ካስጠነቀቁት በኋላ የዕለት ሥራዋን አጠናቃ ወደ መኝታዋ ለመሄድ እየተዘጋጀች የነበረችው ወጣት ላይ ፈጣን ጥቃት ያደርሳሉ። በሩ ገርበብ ብሎ መከፈቱንና አካባቢው ጭር ማለቱን የተመለከቱት ቀማኞቹ በሩን በሰፊው ከፍተው እንዳትጮህ ያዟት።
እነዚህ የክፋት መልዕክተኞች ሱነሜ አሕመድ ተከራይታ ከምትኖርበት የመኖሪያ ቤት ውስጥ በመግባት በላቧ ያፈራችውን ንብረት ለመውሰድ ወንደሰን አፏን በሻርፕ ጨርቅ አፍኖ ሲይዛት፣ በረከት ደግሞ በካርቶን ማሰሪያ ፕላስቲክ ገመድ የወጣቷን ሁለቱን እግሮች እና ታፋዋን እንዲሁም ሁለቱን እጆችዋ ወደ ኋላ በማድረግ በሻርፕ አስሮ ሕይወቷን እንዲያልፍ አደረገ። ባላሰበችው አጋጣሚ ጥቃት የደረሰባት ወጣት የእርዳታ ጥሪ ሳታሰማ እስከ ወዲያኛው አሸለበች።
ሕይወቷ ማለፉን ያረጋገጡት ቀማኞች በቤቱ ውስጥ የነበሩትን የሟች ንብረት የሆኑትን 32 ኢንች ቴሌቪዥን እና ሞባይል ከነሲም ካርዱ እንዲሁም ሌሎች ንብረቶችን ወስደው ከአካባቢው ሊሰወሩ ሲሉ አንድ የዓይን እማኝ ይመለከታቸዋል።
አይቷቸው ይጮሃል፤ በተሰማው ድምፅ መሠረት የፀጥታ ኃይሎች በቦታው ቢደርሱም ጩኸቱን የሰሙት ቀማኞች በፍጥነት ከቦታው በመሰወራቸው ሳያገኟቸው ይቀራሉ። የተፈጠረውን ለመመልከት ግን ወደ ወጣቷ መኖሪያ ቤት የገቡት ፖሊሶች በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቷ ያለፈውን ሴት ተመለከቱ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ በቦታው ሲደርስ ወጣቷ ሕይወቷ አልፎ ንብረቷ ተዘርፎ ይመለከታል። ይህን የተመለከቱት የፀጥታ ኃይሎች ምርመራቸውን ይጀምራሉ። የድረሱልኝ ጥሪ ያሰማው የዓይን እማኝ በሰጠው ምልክት መሠረት ቀማኞቹ ወንደሰንና በረከት መሆናቸው ፍንጭ ሰጥቷል። የወጣቷ አስከሬንም ሲመረመር የተገኘው አሻራ የእነሱ መሆኑን ለማረጋገጥ በቁጥጥር ስር ለማዋል ፍለጋው ቀጠለ።
ወጣቶቹ ለቀናት ተደብቀው እንደልማዳቸው ወደ ስርቆት ሊመለሱ ሲሉ ክትትል ሲያደርግ የነበረው የምርመራ ቡድን በቁጥጥር ስር ያውላቸዋል። የተጠርጣሪዎቹም አሻራ ከሟች አስከሬን ላይ ከተገኘው ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ፤ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ ወደ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በከባድ የውንብድና ወንጀል ክፍል ላከው።
የፍርድ ቤት ክርክር
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በከባድ የውንብድና ወንጀል በመክሰስ ተከሳሾቹ በጽኑ እስራት እንዲሁም ከማኅበራዊ መብቶች እንዲታገዱ ለማድረግ ፍርድ ቤት መከራከረ ጀመረ።
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ ወንድወሰን ተስፋዬ፣ 2ኛ በረከት በዛብህ የተባሉ ተከሳሾች የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ፒያሳ ሱማሌ ተራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሱነሜ አሕመድ ተከራይታ ከምትኖርበት የመኖሪያ ቤት ድረስ በመሄድ የሟች ንብረትን ለመውሰድ 1ኛ ተከሳሽ የሟችን አፏን በሻርፕ ጨርቅ አፍኖ ሲይዛት፣ 2ኛ ተከሳሽ በካርቶን ማሰሪያ ፕላስቲክ ገመድ የሟችን ሁለቱን እግሮች እና ታፋዋን እንዲሁም ሁለቱን እጆችዋ ወደ ኋላ በማድረግ በሻርፕ አስሮ ሕይወቷን እንዲያልፍ ካደረጉ በኋላ በቤቱ ውስጥ የነበሩትን የሟች ንብረት የሆኑትን 32 ኢንች ቴሌቪዥን እና ሞባይል ከነሲም ካርዱ የወሰዱ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ከባድ ውንብድና ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ተከሳሾች ቀርበው የተከሰሱበት ክስ በችሎት ተነቦላቸው የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አይደለንም ያሉ ሲሆን፤ አቃቤ ሕግም ተከሳሾች ክደው የተከራከሩ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን አቅርቦ በክሱ መሠረት ያስረዳ በመሆኑ በቀረበባቸው ክስ መሠረት እንዲከላከሉ ቀጠሮ በተሰጣቸው መሠረት ተከሳሾች 6 የሰው ምስክር አቅርበው ቢያሰሙም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን በተገቢው ያላስተባበሉ በመሆኑ ተከሳሾች ይከላከሉ በተባለበት ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ናችሁ ብሏቸዋል፡፡
ውሳኔ
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት የቅጣት እርከኑን 38 ስር መነሻ ቅጣት በመያዝ፣ ሁለቱም ተከሳሾች የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸውና ማኅበራዊ ተሳትፎ ያላቸው በመሆኑ፣ 2 የቅጣት ማቅለያዎች ተይዘውላቸው በእርከን 36 ስር በማሳረፍ ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን በእያንዳንዳቸው ላይ በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ እና እንዲሁም ተከሳሾች ከማኅበራዊ መብታቸው ለ4 ዓመት እንዲታገዱ ሲል ወስኖባቸዋል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም