ቀደም ሲል በንጉሡም ሆነ በደርግ ዘመን የፕሬስ ነጻነት የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ በአብዛኛው የአፈና መዋቅሮች ነበሩ፡፡ ዜጎች የመደራጀትም ሆነ ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለፅ ነፃነት አልነበራቸውም፡፡ ለዚህ የሚያገለግል የህግ ማዕቀፍም አልነበረም፡፡ በተለይ በደርግ ዘመን ይወጡ የነበሩ አዋጆች የዜጎችን የመናገር፣ የመፃፍ እና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ነጻነትን የሚገድቡ ነበሩ፡፡
በአገራችን የፕሬስ ነጻነት “ሀ” ብሎ የጀመረው ኢህአዴግ ሥልጣን በተረከበ ማግስት ነው፡፡ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 29 ላይ እንደተደነገገው የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እውቅና አግኝቷል፡፡ ከዚያ የሚመነጨው የፕሬስ አዋጅ ቁጥር 34/1985 ሥራ ሲውል የፕሬስ ነፃነት አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንዲራመድ አድርጓል፡፡
ይህ አዋጅ ዜጎች በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊ ግንዛቤ ሲኖራቸውና በመንግሥት አመራርና አሠራር ላይ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ማድረግ ሲቻል ጉልህ የሆነ ሚና የሚጫወቱ ስለሆነ፣ ፕሬስ ይህንን ተግባሩን ሊያከናውን የሚችለው የቅድሚያ ምርመራ (ሴንሰርሺፕ) እና ሌላም ተመሳሳይ ገደብ ሳይደረግበት በነፃና በኃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀስ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ሲፈጠርለት እንደሆነ በመታመኑ ተግባራዊ የተደረገ ነበር፡፡
ይሁንና በቅርቡ እስከመጣው ለውጥ ድረስ ህጉን ወደ መሬት ማውረድ ላይ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ በአንድ መልኩ በሙያተኛው ላይ የሚታዩ በተለይ የመንግሥት ሚዲያው ላይ የህሊና አርትኦት(Self Censorship) እያደረገ የመንግሥት ደጋፊነትንና አጋርነትን ብቻ ተልዕኮ አድርጎ የመውሰድ፣ የህዝብ ድምፆችን ያለማሰማት፣ ቅሬታዎችን አለመዘገብ፣ የምርመራ ዘገባን ያለመሥራት፣ ወዘተ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ የግል ሚዲያው ላይ ደግሞ ለተቃውሞ ፖለቲካ ትኩረት መስጠትና ሁሉንም አጠልሽቶ የመተቸት፣ የህዝብና የመንግሥት ጥቅምን ጭምር ለማናጋት መረጃችን የማውጣትና ግብታዊነት የሚታይበት ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የወጡ ህጎች በተገቢው ሁኔታ ለማስፈፀም የሚያስችል የሚዲያ ተቋማትን የመፍጠር እና ባለሙያውም በዚያ ስነልቦና እንዲንቀሳቀስ የማድረግ ሥራ ተጀምሯል፡፡ ሆኖም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አሁንም ስኬት ላይ ብቻ የመንጠልጠል ችግር ይታይባቸዋል፡፡
ነገር ግን መገናኛ ብዙኃን ሁሉንም በሚዛኑ የማየት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ የወጡትን ህጎችም በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ ለማዋል አንደኛ ሚዲያው የህዝብ ድምጽ መሆኑን ማረጋገጥ፤ በመንግሥትና በህዝብ መካከል ድልድይ ሆኖ ማገልግል፤ ከአድልዎ ነጻ ሆኖ መሥራት፣ ጥላቻን የሚያስፋፉና ግጭትን የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ማቆም፣ ለሀገራዊ ጥቅምና ለጋራ ጉዳይ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡
ሁለተኛ አሁን በመንግሥት በኩልም በማህበራዊ ሚዲያ አካባቢ ያለውን አሰራር ለማሻሻልና የህግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መሰረታዊውን የህግ ማዕቀፍ በማይጣረስ መልኩ ተጠያቂነትና ግልፅነትን በሚያሰፍን መልኩ ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡
በሌላ በኩል የፖለቲካ ኃይሎች የሚሰጡት ሃሳብ ሌላውን በማይጎዳ መልኩ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ እንዲህ እየሆነ ሲሄድ አጠቃላይ ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ ህገመንግሥታዊ መብቱ ያለችግር ወደፊት ሊራመድ ይችላል፡፡
ከህዝቡም የሚጠበቅ ነገር አለ፡፡ ህዝብ ያገኘውን መረጃ ሁሉ እንደወረደ መጠቀም የለበትም፡፡ በሃሳብ ነጻነት ስም የተገኘው መረጃ ሁሉ ትክክል ነው ብሎ ከመውሰድ የቱ ነው ትክክል? የቱ ነው ስህተት? ብሎ አመዛዝኖ መውሰድ አለበት፡፡
በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚያገናኛቸውን መረጃዎች በጥንቃቄ በማየት የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚለቁ ገፆችን እየጣለ መሄድ አለበት፡፡ በተለይ የተማረው ህዝብ የተሳሳቱ ሃሳቦችን በማጋለጥ ሚዛናዊነትና ትክክለኝነት እንዲዳብር የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡
በሌላም በኩል ህብረተሰቡ ለሚዲያ መረጃ በመስጠት ተባባሪ መሆን አለበት፡፡ የሚዲያ ነጻነት ሚዲያው ስለተቋቋመ ወይም ህግ ስላለ ብቻ አይረጋገጥም፡፡ ህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃዎችን ለሚዲያ ባለሙያዎች መስጠት መቻል አለበት፡፡ በትክክለኛ ሚዛን ላይም መቆም አለበት፡፡ ሁል ጊዜ ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለአገራዊ አንድነት እና ለብሄራዊ ጥቅም አንድ ላይ መቆም ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 /2011