በአንድ አገር ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን በመቀነስም ሆነ በማባባስ በኩል መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች መከሰታቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህን ግጭቶች
በዘላቂነት ለማስቆምም ሆነ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን ተገቢው ድርሻ መወጣት አልቻሉም፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሙላቱ ዓለማየሁ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን ለሰላም ያላቸው አበርክቶ አናሳ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ የህዝብ/የመንግሥት ሚዲያው ያለበት ኃላፊነት ከፍተኛ ቢሆንም በሰላም ጋዜጠኝነት ላይ ያለው አስተዋፅኦ ግን አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ግጭቶችን የመፍራትና ከርቀት የማየት ሁኔታ ውስጥ ናቸው የሚሉት ዶክተር ሙላቱ፤ ከዚህ ቀደም የመጡበት የፍርሃት መንገድ አሁንም ጠፍሮ እንደያዛቸው ያስረዳሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን መንስኤ፣ በግጭቱ ውስጥ ያሉ አካላት ሚና፣ ፖለቲካዊ ዳራቸው፣ ወዘተ… ምን
እንደሚመስል በዝርዝር ያለማየት ችግር አሁንም በነዚህ መገናኛ ብዙኃን እንደሚን ፀባረቅም ጠቁመዋል፡፡
ይህንን የማያደርግ የመገናኛ ብዙኃን ደግሞ ሙያውን አላከበረም የሚሉት ዶክተር ሙላቱ ተዓማኒነቱም ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ ነው የሚገልፁት፡፡ በዚህ የተነሳ እንዲህ አይነት የመገናኛ ብዙኃን በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ስለማይኖራቸው ግጭትን የመቀነስ አቅማቸው ዝቅተኛ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ፅጋቡ ሞትባይኖር፤ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ወደ ህብረተሰቡ ወርደው የህዝቡን ስሜት ከመዘገብ ይልቅ ከመንግሥት የሚወርድላቸውን አጀንዳ መነሻ አድርገው ይሠራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ አሁንም ቢሆን በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን እውነታ ወደ ጎን ትተውታል፡፡ በተለይ ግጭትን በተመለከተ ይህንን ብዘግብ ግጭቱ ይባባስ ይሆን የሚል ፍራቻ ስለሚያድርባቸው አለመዘገብን ይመርጣሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሰላምን ማረጋገጥ አያስችልም ይላሉ፡፡
አሁን በአገራችን ያለው የፖለቲካ አካሄድ በአብዛኛው የብሄር ፖለቲካ ነው የሚሉት ዶክተር ሙላቱ የግጭቱ መንስኤም በዚሁ ዙሪያ እንደሚያጠነጥን ይናገራሉ፡፡ ግጭቶቹም በአብዛኛው በማንነት ላይ የተመሰረተው የፌዴራሊዝም ውጤቶች ናቸው፡፡ ይህንን ደግሞ ደፍሮ የሚዘግብ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የለም፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ከፌዴራሊዝም ጋር የተያያዘ ነው ብሎ መዘገብ
መንግሥትን መቃወም ነው ብሎ ስለሚያስብ አለመዘገብን እንደአማራጭ ይወስዳል፡፡
አሁን ሁሉም ሚዲያ በየራሱ ጎራ ተሰልፎ «እኛና እነሱ» በሚል በየፊናው ይጓዛል የሚሉት አቶ ፅጋቡ በዚህ የተነሳ የጋራ የሆነው የሰላም ጉዳይ ተገቢው ቦታ እንደተነፈገው ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ሁሉም ጥግ ይዞ የራሱን አጀንዳ እያራገበ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የሰላም ጋዜጠኝነት ይህንን አይደግፍም፡፡ መገናኛ ብዙኃን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የእኛ ነው በሚል እኩል ማገልገል አለባቸው፡፡ በዚህ የተነሳ «ሚዛናዊነት» የሚለው የመገናኛ ብዙኃን መሰረታዊ መርህ ተጥሷል፡፡
እንደ ዶክተር ሙላቱ ገለፃ የግል መገናኛ ብዙኃን ቀደም ሲል ለተቃዋሚዎች ያደላሉ የሚል ትችት ይቀርብባቸው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ አብዛኞቹ ብሄር ተኮር እየሆኑ መጥተዋል፡፡ እነዚህ የመገናኛ ብዙኃንም በአብዛኛው ግጭቶችን ሲዘግቡ እንደፍላጎታቸው ወደ አንድ ወገን ይሳባሉ፡፡
በዚህ የተነሳ ሚዛን ይስታሉ፡፡ «እነሱና እኛ» ብለው በመክፈልም ወገንተኝነትን ያፀባርቃሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሰላምን ከማጣምት ይልቅ አሉታዊ ጎናቸው ያመዝናል፡፡ አንዳንዶቹ መገናኛ ብዙኃን ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በመሸሽ በመዝናኛ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ገቢ መሰብሰብ ላይ ብቻ ተጠምደዋል፡፡
በሌላ በኩል ኦንላይን ሚዲያው በአገራችን ተፅዕኖ ከሚፈጥሩ መገናኛ ብዙኃን አንዱ ሲሆን፤ እነዚህ መገናኛ ብዙኃን መረጃን ፈጥነው ከማድረስ አንጻር የተሻሉ እንደሆኑ ዶክተር ሙላቱ ይናገራሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን ልክ እንደ መንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን ሁሉ በነዚህም ላይ የወገንተኝነት ችግር ጎልቶ ይስተዋላል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የትክክለኝነትና የሚዛናዊነት ችግሮች በነዚህ መገናኛ ብዙኃን ላይ ጎልቶ የሚነሳ ችግር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ዶክተር ሙላቱ እንደሚሉት በአገራችን የመገናኛ ብዙኃን ያለባቸውን ችግር በመቅረፍ ለሰላም ተገቢውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ እያንዳንዱ የሚዲያ ባለሙያ የጋዜጠኝነት ሥነምግባርና መርሆዎችን ተከትሎ መዘገብ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም መሰረት ገለልተኛ ሆኖ በኃላፊነት ስሜት የሚዘግብ ከሆነ በቀጣይ ችግሮችን የመቅረፍ እድሉ እየሰፋ ይመጣል፡፡ ይህ ደግሞ ሙያውንም የማሳደግ አንድ እርምጃ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ለባለሙያዎች በየጊዜው ሙያውን የሚያሳድግበትን ሥልጠና መስጠት፣ ውይይቶችን ማካሄድ፣ ችግሮች ሲከሰቱ ምን መሆን እንዳለበት መወያየትና መወሰን፣ ይህንንም ተንተርሶ መረጃ ማግኘትና የሚገኘውንም መረጃ ለህዝብ ማድረስ ከተቻለ ህብረተሰቡ በሚያገኘው መረጃ ላይ እምነት ይኖረዋል፡፡ የመንግሥት አካላትም መረጃ መስጠት ላይ ተባባሪ መሆን አለባቸው፡፡
አቶ ፅጋቡ እንደሚሉት የሰላም ጋዜጠኝነት ግጭትን ብቻ እየተከታተለ መዘገብ ሳይሆን ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት በህዝቦች መካከል ሰላማዊ ግንኙነቱ እንዲጠናከር መሥራት ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ አንጻር ሰፊ ክፍተት አለ፡፡ ህዝቦችን የማቀራረብ ሥራም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ላይ መገናኛ ብዙኃኑ ተከታይ እንጂ አጀንዳ ፈጥሮ ቀድሞ መሥራት አልቻሉም፡፡ ግጭቶችም ሲፈጠሩ የግጭቱን መንስኤ ከመሰረቱ መርምሮ ለህዝብ ይፋ ማድረግ ከብዷቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ የሰላም ዘብ መሆን አልቻሉም፡፡
ጋዜጠኝነት ድምፅ ለሌላቸው ሰዎች ድምፅ መሆን ነው የሚሉት አቶ ፅጋቡ፤ ነገር ግን ይህንን መተግበር ካልቻሉና የጥቂቶች ድምፅ ከታፈነ የጋዜጠኝነት ሙያ ተከብሯል ማለት አያስችልም ይላሉ፡፡ ስለዚህ ሚዲያው እስከታች በመውረድና ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ድምፅ በመሆን መሥራት አለበት፡፡
በዓለም ላይ በመገናኛ ብዙኃን አባባሽነት የደረሱ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋዎች አሉ፡፡ ከ25 ዓመታት በፊት በሩዋንዳ የተከሰተው የዘር ማጥፋት ድርጊትና ከ14 ዓመታት በፊት በዩጎዝላቪያ የደረሰው የዘር ማጥፋት ድርጊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ያጠፋ አስከፊ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በአርሜኒያ በተደረገው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በርካታ ዜጎች ቢሞቱም ግጭቱ ይበልጥ እንዳይባባስና የበለጠ እልቂት እንዳይከሰት መገናኛ ብዙኃን የተጫወቱት ሚና በበጎ ገጽታ ይነሳል፡፡
ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የመገናኛ ብዙኃኑ በተለይ የህዝብና የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን በዚህ ደረጃ ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስ ካልቻሉ ህዝቡ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ደስተኛ አይሆንም፣ ሚዲያውም በህዝብ ዘንድ ያለው ተዓማኒነትና ተቀባይነት እየተሸረሸረ ይሄዳል፡፡
ተዓማኒነት ያጣ ሚዲያ ደግሞ ተከታይ የለውም፡፡ በዚህ የተነሳ ህዝቡ መረጃዎችን ከዚህም ከዚያም የመቃረም ሁኔታ ውስጥ ይገባል፡፡ ይህም ያገኘውን መረጃ ሁሉ ትክክል ነው ብሎ ወደ መውሰድ እንዲሄድ ያደርገዋል፡፡ በዚህ መካከልም እውነት ነው ብሎ የወሰደው መረጃ ሐሰት ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ የሐሰት መረጃ ላይ ተመስርቶም ወደ ተሳሳተ እርምጃ ሊሄድ ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 /2011
በወርቁ ማሩ