‹‹ካኦ ዴቢቴ ዴቢቴ›› በአማርኛ ትርጓሜው አጋጣሚው ይደጋገም የሚለውን ስንኝ የኦሮሞ ፈረሠኞች በዜማ እያጀቡ ሲቀባበሉ ለተመለከተ መዳረሻቸውን ለማወቅ ጉጉትን ያጭራል፡፡ በመሐል ተሽከርካሪዎች በዳር ደግሞ እግረኞች መንገዱን ሞልተው ከቤቱ የቀረ ሠው የለም ወይ? በሚያስብል መልኩ ከአምቦ ወደ ነቀምቴ ከተማ በሚወስደው መንገድ ላይ ይተማሉ፡፡ ፈረሠኞቹም ‹‹ጆሮሌ ፈርዳ ያ ጆሮሌ ኦሆ›› ቆንጆ ፈረሴ ቆንጆ በማለት በ‹‹ማያ ፈርዳ›› የተዋቡ ፈረሶቻቸውን ከስፍራው በቶሎ እንዲያደርሷቸው ያሞግሳሉ፡፡
‹‹ሉፊሳ›› ትከሻቸው ላይ ያደረጉት በአምቦ ከተማ ልዩ ስሙ ኪሶሴ ዶሊበን አካባቢ ነዋሪ ፈረሠኛ አቶ ሲሳይ ኃይሉ፤ የሁለቱ ክልል ሕዝቦች አንድ በመሆናቸው ያመጧቸው ለውጦች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ይህም ሰዎች አንድ ከሆኑና ከተባበሩ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ህያው ምስክር ይሆናል፡፡ የሁለቱ ክልል ሕዝቦች የተጠናከረ ግንኙነት በመላ አገሪቱ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት የሚፈጥር ነውም ብለዋል፡፡
ትናንት በአምቦ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የአማራና ኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ የምክክር መድረክ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች እንደሚገልፁት፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችም የራሳቸውን ጥቅም ማዕከል አድርገው በሚንቀሳቀሱና ቀና አመለካከት በሌላቸው ግለሰቦች የተፈጠረ ነው፡፡ መንግሥትም በልዩ ትኩረት ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ላይ በመሥራት አንድነትን ሊያጎለብት ይገባል፡፡
ከአማራ ክልል ጎንደር ከተማ አስተዳደር በመድረኩ የተገኙት አቶ ወሰንጌ ታደሰ፤ ምንም እንኳ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ቢነሱም ሕዝቦች ግን ለዘመናት የገነቡት ጠንካራ እሴት በመኖሩ አብሮ መኖሩ ሳይሸራረፍ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ ይህም ግጭቶቹ ስር የሰደደ መሠረት እንደሌላቸው አመላካች ነው፡፡ ይልቁንም ሕዝቡ የለውጡ ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚሹ አካላት አስተሳሰብን መሠረት አድርገው የሚነሱ ናቸው፡፡
አቶ ወሰንጌ፤ ግጭቶቹ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሚያደርሱት ሥነ ልቦናዊ፣ አካላዊ ብሎም የንብረት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ፤ ሕዝቡ ይህንን አውቆ በተረጋጋ ሁኔታ ነገሮችን ማጤን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ በለውጥ ሂደት ላይ ይህን መሰል ችግሮች መከሰታቸው አይቀርምና መንግሥትም ችግሮቹን ከሕዝቡ ጋር ተነጋግሮ ሊፈታ ይገባል፡፡
ትናንት በአምቦ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች አንድነት መድረክ ላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የሁለቱ ክልል ሕዝቦችና ጥሪ
የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ የሁለቱ ክልል ሕዝቦች ለዘመናት የቆየና የጸና ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሰነዶችም ቀርበዋል፡፡ ታዳሚዎችም ሕዝቦች በጋራ የመኖር እሴት ላይ ችግር እንደሌለባቸው በመግለጽ፤ በቀጣይም ይህ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሚጠቁሙ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ «ከአማራ ሕዝብ ጋር የከፈልነው መስዋዕትነት ብዙ ነው። ከአማራ ህዝብ ጋር በአንድ መቃብር ተቀብረናል፣ በአንድነት ሞተን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስጠብቀናል ፤ በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብ ከአማራ ህዝብ ጋር ለዘመናት የነበረውን ግንኙነት አጠናክረን ለኢትዮጵያ አንድነት እናውላለን። አንድነታችንን አጠናክረንም ይበልጥ የበለጸገች፣ ዴሞክራሲያዊትና ፍትህ የተከበረባት፣ አገራዊ ክብሯ ከፍ ያለ፣ አንድነቷ የማይነቃነቅ ኢትዮጵያን ለመፍጠርም በጋራ እንሰራለን።» ብለዋል።
የኦሮሞ ሕዝብ በባህሉ አቃፊና የአንድነት ዘማሪ መሆኑን ያወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ይህንንም አገሪቱ ችግር ላይ በወደቀች ጊዜ አባይን ተሻግሮ ወዳጅም ፣ ጠላትም እያየ ከአማራ ህዝብ ጋር በመቀላቀል አሳይቷል ብለዋል። በዚህም በሀገሪቱ ባለፈው አንድ ዓመት ለታየው ለውጥ የራሱን አስተዋጽዖእንዳበረከተ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ግንኙነቱን ለማጠናከር ሆደ ሰፊ በመሆን ህፀፆችን ማጽዳት እንደሚገባ ገልፀው፤ በዚህ ወቅትም ልዩነትን የሚያሰፋ ሳይሆን አንድነትን በሚያጠናክር ሥራ ላይ ማተኮር የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፡፡ ባለፉት ታሪኮች መቆዘምን በማቆም ወደፊት መራመድ ላይ ሊተኮር ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
አቶ ሽመልስ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህንን የአንድነት ሰፊ መሠረታቸውን ከመቼውም በላይ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ «አባቶቻችን በአንድ ጽዋ ጠጥተው በአንድ መቃብር ተቀብረው ሉዓላዊት ኢትዮጵያን እንዳቆዩን እኛም ይህንን የአንድነት መሠረት በማጠናከር የበለጸገች ዴሞክራሲያዊት፣ ፍትህ የተረጋ ገጠባትና አንድነቷ የማይነቀነቅ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንሰራለን» ብለዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የሁለቱ ክልሎች መሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ከነበራቸው ግንኙነት በላቀ ሁኔታ ተባብረውና ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሆን አገር የመገንባት ሂደቱን ዕውን ለማድረግ ይሠራሉ፡፡ በዚህም መሪዎች በመምራት ሕዝቦችም ታሪክ በመሥራት በእያንዳንዱ ጉዞ ከሚያጋጥሙ ችግሮች ትምህርት እየተወሰደ የበለጠ ታሪክ ለመሥራት ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡
ሕዝቡ መሪዎች እንዲቀራረቡ ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚችል እያረጋገጠ ነውና የሁለቱን አመራሮች መቀራረብ የማይሻ ኃይል በተለያዩ መንገዶች የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ከመሄድ በመቆጠብ የአገሪቱን አንድነት በሚያጎለብቱ ተግባራት ላይ ትኩረቱን ማድረግ አለበትም ብለዋል፡፡ ሕዝቡ በዚህ መልኩ ነገሮችን በንቃት መከታተሉና ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላት በሚፈጥሩት ማዕበል አለመወሰዱም መንግሥት ለጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽና አመራር መስጠት ያስችለዋልና ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ዶክተር አምባቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2011
በ ፍዮሪ ተወልደ