አዲስ አበባ፡- የኮሙኒኬሽንን ዘርፍ የሚቆጣጠር ጠንካራ ተቋም በባለስልጣን ደረጃ ሊቋቋም እንደሆነ በየኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ረቂቅ አዋጅ ላይ በተዘጋጀው የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ ላይ እንደገለፁት፣ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ቁጥጥር ባለስልጣን ሲቋቋም ብዙ ችግሮችን ይቀርፋል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የፖስታ አገልግሎትና የብሮድካስቱን ዘርፍ የሚቆጣጠረውን ባለስልጣን ማቋቋም ያስፈለገው ከፍተኛ የሆነውን ሀብት የሚይዙና የኮሙኒኬሽኑን ዘርፍ የሚመሩትን ተቋማት በቅርብ ሆኖ እንዲቆጣጠር ታስቦ ነው፡፡
ዶክተር ጌታሁን እንዳሉት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ህዝብን ሲያገለግል የኖረ ባለውለታ ተቋም ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ የበለጠ ሀብት ማፍራት እንዲችልና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ በዘርፉ የግል ባለሀብቶችን ማሳተፍ አስፈላጊ ሆኗል፡ ፡ ሀገራችን ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ ባለቤት እንደመሆኗ በኮሙኒኬሽኑ ዘርፍ የግዙፍ ገበያ ባለቤትም ናት፡፡
የግል ባለሀብቱን በማሳተፍና በዘርፉ ውድድር በመፍጠር በአነስተኛ ዋጋ ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት ይቻላል፡፡ ውድድር በሌለበት ሁኔታ ተጠቃሚው ሁሌም ተጎጂ ነው የሚሆነው፡፡ በመሆኑም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ሲቋቋም በፖሊሲ ደረጃ የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ይምራው እንጂ ሪፖርት የሚያቀርበው በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ጠንካራ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤት በማቋቋም የኢትዮ ቴሌኮምን ዘርፍ ለግል ባለሀብቱ ክፍት በማድረግ ጠንካራና ውጤታማ ማድረግ ይቻላል፡፡ ባለስልጣኑ ሲቋቋም በተለያዩ ኦፕሬተሮችና በግለሰብ መካከል የሚነሱ ቅሬታዎችን ይፈታል፡፡ ቅሬታዎችን በመፍታት ጤነኛ የሆነ ውድድር እንዲኖር ያደርጋል፡ ፡ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ጋር በጋራ ስለሚሰራም ለሀገር እድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን የቁጥጥርና የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው ያስችላል፡፡
የሰው ሀብት ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እምዬ ቢተው በበኩላቸው፤ መንግሥት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትን በተግባር ለማሻሻልና በኮሙኒኬሽኑ ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት የኢትዮ ቴሌኮም ገበያ እንደገና ማዋቀር አስፈላጊ መሆኑን አምኖበታል፡፡ እንዲሁም የኮሙኒኬሽኑን ገበያ ውድድር ለማስፋት ያስቀመጠውን ፖሊሲ እውን እንዲሆን ነፃና ጠንካራ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ለማቋቋም ከህዝብ ጋር በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት በማድረግ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አስታውሰዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝ 13/2011
ሞገስ ፀጋዬ