አዲስ አበባ፡- በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር የተቋቋመው የዳኝነት ሥርዓት ማሻሻያ ጉባዔ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ያዘጋጀ ሲሆን፣ አዋጁ ሲፀድቅ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚመጡ ጉዳዮችን ለመቀነስ እንደሚረዳ ተጠቁሟል።
ረቂቅ አዋጁ ላይ ትናንት ውይይት በተደረገበት ወቅት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ እንደተናገሩት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 25/88 ወጥቶ ሥራ ላይ ከዋለ ከሃያ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። በእነዚህ ጊዜያት አዋጁን ለማሻሻል በተከታታይ የወጡ አዋጆች ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት አቅም ያነሳቸው ናቸው። በመሆኑም በሀገሪቱ ያለውን የዳኝነት ሥዓት ለማሻሻልና በዘርፉ የሚስተዋሉትን የአዋጅ፤ የአደረጃጀትና አሰራር ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ለመጠቆም በተቋቋመው የዳኝነት ሥርዓት ማሻሻያ ጉባዔ ጥናት ተደርጎ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል ብለዋል።
አዋጁ ፀድቆ ወደ ተግባር ሲገባ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚቀርቡ ጉዳዮችን ለመቀነስ ይረዳል ያሉት ሚኒስትሯ ወደ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ ጉዳዮች ከዓመት ዓመት እየጨመሩ በመምጣታቸው በአሁኑ ወቅት ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ ጫና ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የዳኝነት ሥርዓት ማሻሻያ ጉባዔ አባል ጠበቃ አብደላ አሊ በበኩላቸው በቂ ምክንያት ሳይኖራቸው ወደ ሰበር ሰሚ የሚቀርቡት መዝገቦች ቁጥር እየጨመረ መምጣት ፍርድ ቤቱንም አቤቱታ አቅራቢውንም ለድካም እየዳረገ ነው ይላሉ። ጠበቃ አብደላ እንደሚያብራሩት በአሁኑ ወቅት መሰረታዊ የህግ ስህተት አለባቸው እየተባሉ ለሰበር ሰሚ እየቀረቡ ያሉት ጉዳዮች ከማህበራዊ ፍርድ ቤትና የሽምግልናና የግልግል ጉዳዮችን ጨምሮ በየትኛውም ደረጃ በሀገሪቱ ያሉ ፍርድ ቤቶች ላይ የሚሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዎች ናቸው።
ከዚህ ቀደም በተደረገ ጥናት እንደተረጋገጠው ከ1986 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ.ም ስምንት ሺ የፍትሐ ብሄር ጉዳዮች ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢቀርቡም ተገቢ ሆነው የተገኙት ሃያ አምስት በመቶ ብቻ በመሆናቸው ቀሪዎቹ መዝገቦች የዳኞችን ጊዜ የአቤቱታ አቅራቢዎችንም ጊዜና ገንዘብ ለብክነት የዳረጉ ሆነው ተገኝተዋል። በተመሳሳይ ከ2000 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር አጣሪና በሰበር ሰሚ ችሎቶች ከነበሩት መዝገቦች የመደበኛው ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሄርና ወንጀል ችሎት በሦስት በመቶ የሚበልጥ ነው። ይሄ ደግሞ የላይ ፍርድ ቤቶችን የተቋቋሙበትን መሰረታዊ አላማ በማሳት በጥቃቅንና በስር ፍርድ ቤቶች ሊጠናቀቁ በሚችሉ ጉዳዮች እንዲጠመዱ እያደረጋቸው ይገኛል። በመሆኑም የተዘጋጀው አዋጅ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት መሰረታዊ የህግ ስህተቶች ላይ ብቻ በማተኮር የተቀመጠለትን ዓላማ እንዲያሳካ የሚያስችለው ይሆናል ሲሉ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝ 13/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ