የፕሬስ ነጻነት ከማሰብ ነጻነት የሚጀምር ነው። ይህም እያንዳንዱ ዜጋ የፈለገውን በነጻነት የማሰብና የመናገር መብት አለው ከሚለው ይመነጫል። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሕዝቦች በተወካዮቻቸው በኩል ራሳቸውን ያስተዳድራሉና፤ ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ ምን እየተከናወነ እንዳለና የተወከለው መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ ማወቅ አለባቸው። ለዚህም በየቀኑ ፓርላማ አይካፈሉም፤ ይልቁንም በጋዜጠኞች ወይም በፕሬስ በኩል ነው ማወቅ የሚችሉት።
እናም የፕሬስ ነጻነት የሕዝብ የማወቅ መብት ነው። ብዙ ሰው የፕሬስ ነጻነት ሲባል ለጋዜጠኞች መሟገት አድርጎ ያስበዋል፤ ነገር ግን ለሕዝብ መሟገት ማለትም ነው። ምክንያቱም የማወቅ መብት ያለው ሕዝብ ነው። ሕዝብ ሊያውቅ የሚችለው ደግሞ በፕሬሱ በኩል ነው። ከነጻነቱ ጋር አብሮ የሕግ ተጠያቂነትም አለ፤ ነገር ግን በእያንዳንዱ ነገር ቅድመ ክልከላም ሆነ አንድ ሰው በጻፈው ዜና ወይም አስተያየት ስደትና እንግልት ሊደርስበት አይገባም የሚለው ነው መሠረታዊ ጽንሰ ሃሳቡ።
ቀደም ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ የነበረውን ስናይ በአንጻራዊነት ለቀቅ ተደርጎ ጋዜጠኛው እንደልቡ የጻፈባቸው ጥቂት ጊዜያት ነበሩ። አንዱ 1966/67ዓ.ም ለውጥ እንደመጣ ሲሆን ሌላው ኢህአዴግ እንደገባ የነበረውና የቅድመ ሳንሱር ተነስቶ የግል ሚዲያዎች የተፈቀዱበት ጊዜ ነበር። በኋላ ላይ ግን በሂደት በቀጥታ ሳንሱር ባይኖርም በሌላ የተለያዩ ሕጎች የጋዜጠኝነት እንዲሁም የፕሬስ መብት ተሸርሽሮ ነበር። ከዛም አልፎ በጻፉት ጽሑፍ ምክንያት ከአገራቸው የተሰደዱና የታሠሩ አሉ። መንግሥት በወቅቱ የታሰሩት በጋዜጠኝነታቸው ነው ባይልም፤ መሆኑ ይታወቅ ነበር።
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ አንጻራዊ ወይም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ነጻ ድባብ አለ። ይሁንና ህጎች በመቀየር ላይ እንዳሉና እየተረቀቁ እንደሆነ ስለምናውቅ እንጂ በህግ ደረጃ የተቀየረ ነገር የለም። ነገር ግን ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ ከሚነገረው ነገር በመነሳት ነጻነት ያለበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው ማለት ይቻላል።
ወደፊት እየተረቀቀ ያለው ህግ ነጻነትን የሚጠብቅና የጋዜጠኛውን መብት የሚያስጠብቅ ብሎም ጥሩ የሚዲያ ነጻነት ያለበት ሕግ ሆኖ ይወጣል ብለን እንጠብቃለን። እነዚህ አሠራሮች ተቋማዊና ሕጋዊ ሆነው ይቀጥላሉ ብለንም ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህ በተጨማሪ የፕሬስ ነጻነት ቀንን ስናከብር በተለይ ከጥላቻ ንግግር ጋር ተያይዞ በአውደ ጥናት፣ ሃሳብ በመለዋወጥና በሕጎቹ ዙሪያ በመነጋገር እንዲሁም ሕዝብን የሚያሳትፍ ውይይት በማድረግ ቢሆን መልካም ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝ 13/2011