– ለአማራ ክልል ልዑካን በቡራዩ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል
«ከኦሮሚያ ተነስተን የሁለት ወንድማማች ህዝቦችን ፍቅርና አንድነት ለማጠናከር ወደ ውቢቷ ባህርዳር ስንመጣ የአማራ ክልል ህዝቦች ከዓባይ ድልድይ ጀምሮ እስከ ባህርዳር ድረስ ስላደረጋችሁልን ወንድማዊና ልባዊ አቀባበል በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል መንግሥት ሳይሆን በመላው ኦሮሞ ህዝቦች ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ» ሲሉ ነበር የቀድሞው የኦሮሚያ
ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ባህርዳር ተካሂዶ በነበረው የኦሮሞና አማራ ህዝቦች የአንድነት መድረክ የተናገሩት።
አቶ ለማ በዚሁ መድረክ «ኢትዮጵያዊነት ምን እየሆነ ነው የሚለው በብዙዎቻችን አዕምሮ ውስጥ ግርታን ሳይፈጥር የቀረ አይመስለኝም። ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ምን እንደሆነ ዛሬ እዚህ መድረክ ላይ ባየነው ትዕይንት በሚገባ ተገልጾልኛል። ዛሬ ዛሬ አንድነታችን በተለያዩ ትንንሽ ምክንያቶች እየተሸረሸረ እንደሆነ እያየን ነው። ይህን ችግር አንስተን ካልተወያየንና ለዚህ በሽታ መድኃኒት ካላበጀንለት መጨረሻችን ምን ሊሆን እንደሚችል መነጋገር ያለብን በዚህ መድረክ ነው።» ሲሉም ተናግረው ነበር።
አቶ ለማ መገርሳ በተጨማሪም «ከኦሮሚያ ወጥተን አማራ ወንድሞቻችን ጋር የመጣነው ለሽርሽር ወይም ደግሞ ለአንድ ሰሞን ሞቅታ አይደለም። በእውነት ከልብ ስለምታስፈልጉን እና እንደምታስፈልጉን ስለገባንና ስላመንን ነው። ሌሎች ብሄር ብሄረሰብ ኢትዮጵያውያንም ያስፈልጉናል» ሲሉም ገልጸው ነበር።
በወቅቱ በተካሄደው መድረኩ ሁለቱ ታላላቅ ህዝቦች ለሺህ ዓመታት ተከባብረውና ተፋቅረው መኖራቸው ተወስቶ ይህ አንድነት እንዳይሸረሸር ብሎም ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ተመክሮ ነበር። ይህንን ቅዱስ ሃሳብ ለፍሬ ለማብቃትም ነው የአማራ ክልል የህዝብ ልዑካን ዛሬ አምቦ ላይ የሚታደሙት። ልዑካኑ ወደ አምቦ ሲመጡም በኦሮሞ ህዝቦች ቡራዩ
ላይ ደመቅ ያለ ወንድማዊ አቀባባል በትናንትናው ዕለት ተደርጎላቸው ነበር።
ቡራዩ ጉቴ ሆቴል በተካሄደው አቀባበል ላይ የቡራዩ ከተማ ጽ/ቤት የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ታደሰ እንደተናገሩት፣ ይህ ህዝብ በታሪክ አንድ ከመሆኑም በላይ ተዋልዶና በችግርና በደስታም ጊዜ አብሮ የኖረ ነው። ሀገር ማለት ህዝብ ነውና በመተሳሰር መኖር አለባቸው ብለዋል፡፡ የሁለቱ ህዝቦች ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ዋልታ ያሉት አቶ ሰለሞን፣ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚሞክሩ ኃይሎችን ከማንም በላይ ህዝቡ ራሱ መከላከል ይገባዋል። ያ ካልሆነ ግን የሁለቱን ህዝብ ክፍተት ለሚፈልጉ አካላት ስኬት ነው ብለዋል፡፡ ሁለቱን ህዝቦች የማጋጨት ሙከራና ምልክቶች ነበሩ ነገር ግን ጠንካራ ትስስር ስለነበራቸው በአጭሩ ሊቀጭ ችሏል ሲሉ አክለዋል፡፡
በባህር ዳር ከተማ ነዋሪና የሰላም ኮሚቴ አባል አቶ መንግስቱ ቸርነት የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች በፍቅር፣ በአንድነት በመተሳሰብ አብሮ መኖር መገለጫቸው ነው፡፡ ይህ መልካም ተግባር እንዲቀጥል እንዲህ ዓይነት መድረክ መዘጋጀት አለበት፡፡ አንድነታችንን ለማጠናከር መክፈል ያለብንን ዋጋ እንከፍላለን ብለዋል፡፡
በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የአማራ ምሁራን አባል የሆኑት ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው እንደሚናገሩት፣ ሁለቱ ህዝቦች ትልልቅና ሰፊ ህዝቦች ናቸው፡፡ ስለሆነም ይህች ሀገር እንደ አገር እንድትቀጥል የሁለቱ ህዝቦች አንድነት፣ መቻቻልና መከባበር በማይሰላሰል መልኩ መጋመድ አለበት፡፡ ባለፉት ዓመታት በጋራ በመሆን ለውጥ አምጥተዋል፡፡ አሁንም ለውጡ እንዲሰምርና ኢትዮጵያ ጠንካራና ሉዓላዊ ሀገር ሆና እንደትቀጥል አንድነታቸው ወሳኝ ነው፡፡ ሲሉ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
የቡራዩ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብዲሳ ሂርጳሳ ሁለቱ ህዝቦች ከዚህ በፊት በመተሳሰብና በመከባበር አብረው ኖረዋል፡፡ አንድነታችንን ለማጠናከር የሀገር ሽማግሌዎች በየክልላቸው ያሉ ወጣቶችን በመምከር ለሀገር አንድነትና ጠንካራ አገርን ለመፍጠር መስራት አለባቸው፡፡ በአንዳንድ እራስ ወዳድ ሰዎች ምክንያት ብሔርን ተኮር ያደረጉ መፈናቀሎች አሉ። ይህ ችግር በመነጋገርና በመተሳሰብ መፈታት አለበት፡፡ ሀገርን በመገንባት ሳይሆን በማፍረስ ጥቅም የሚያገኙና የሚደሰቱ ኃይሎች ግጭት ለመፍጠር ነገም አይተኙም። ነገር ግን ሁለቱ ህዝቦች አርቆ በማሰብ ለችግሩ መፍትሔ አምጭ መሆን አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ህዝቦች በጋራ በመሆን ሀገራችንን በውጭ ወራሪ እጅ እንዳትወድቅ ተዋግተዋል፡፡ ጠንካራ ማንነትና ታሪካዊ ትስስር ባይኖራቸው ኑሮ ሀገራችን ዛሬ ሳይሆን የውጭ ወራሪ በመጣ ጊዜ ትፈርስ ነበር ሲሉም አክለዋል፡፡ የውጭ ወራሪን በጋራ እንደተከላከሉት ሁሉ አሁንም ዘረኝነትን በጋራ ሆነው በማጥፋት የጋራ ሀገርን መገንባት አለባቸው ሲሉም ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2011
ሞገስ ፀጋዬ