ሞረትና ጅሩ ወረዳ ፡- በሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ ያሉ አርሶአደሮች በከብት ማደለቡና ለገበያ ማቅረቡ ላይ የተሸለ ተግባር ቢከውኑም የገበያው ሁኔታ የተመቻቸ ባለመሆኑ ትርፋማ መሆን እንዳልቻሉ ተገለጸ፡፡
የወረዳው የእንሰሳት ሀብት ልማት ተጠሪ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አበባው ገብረየስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የጅሩ ሰንጋ በጥራትም ሆነ በክብደት የተሸለ ከብት የሚቀርብበት በመሆኑ በአገር ደረጃ የ’ብራንድ’ ባለቤት ነው፡፡ ይሁንና አርሶአደሩም ሆነ በማህበር ተደራጅተው ከብት የሚያደልቡ አካላትየተጠናከረ ገበያ ባለመኖሩ የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እየሆኑ አይደለም፡፡
በወረዳው ከብቶች ሲደልቡ በብዙ እንክብካቤ ነው፤ ብዙ ወጪም ያወጡባቸዋል፡፡ ሆኖም በሽያጭ ግን ያወጡትን እንኳን መመለስ እየተሳናቸው እንደሆነ የገለጹት ደግሞ በወረዳው ንግድ ገበያ ጽ/ቤት የእንሰሳትና እንስሳት ተዋዕጽኦ ገበያ ልማት ቡድን መሪ አቶ ደረጄ ታደሰ ናቸው፡፡
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በተለይም ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በየጊዜው የአርሶአደሩ ከብትን አድልቦ የማቅረቡ ሁኔታ በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ ነገር ግን ምርቱን ተቀብሎ ለገበያው የሚያደርስለት አማራጭ እጅግ የሳሳና ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ በመሆኑም ከአጋር አካላት ጋር ለመስራት እየተሞከረ ነው፡፡
ቢሆንም የመንግት ትረት ዛሬም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዜና በተቀናበረበት እለት (ሚያዚያ 12) ከጅሁር ቀበሌ ትልቅ የሚባለውን ድልብ ከብት ይዘው የቀረቡት አርሶአደር አስታወስ እሸቴ በበኩላቸው፤ በየጊዜው ከብቶችን አደልበን ማቅረብ እንፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን ገዢ በሌለበት ምን ያደርጋለን ብለዋል፡፡
ምክንያታቸው ደግሞ ወጪያቸውን እንኳን የሚሸፍን ገንዘብ ባለማግኘታቸው ነው፡፡ ዓመት ጠብቆ ገበያ ማግኘት የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ አይችልም፡፡ በዚያ ላይ በዓመቱም ቢሆን ዋጋው ዝቅተኛና የማይጠቅም እየተደረገ ነው የሚሸጠው፡፡ ስለዚህም መንግስት ይህንን ችግራችንን አይቶ የገበያ አማራጮችን ሊያሰፋልን ይገባል ብለዋል፡፡
የመንገድ ጉዳይም እንዳሳሰባቸውና ምርታቸውን ለሚፈለገው አካል ለማቅረብ እንደተቸገሩ የሚያነሱት አርሶአደሩ፣ መንገድ ከሌለ ገዢው በምን መጥቶ ምርታችንን ሊያይና ሊገዛን ይችላል፣ ይሰራል የሚለው ተስፋም አንድም አይታይም፡፡ ስለዚህም ማምረቱ ከንቱ ነው፡፡
ለራስና ለአካባቢው ነዋሪ ብቻ ይሆናል፡፡ መንግስት ቃል ከመግባት አልፎ በተግባር ለተጠቃሚነታችን ሊሰራ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ከደሴ ከተማ ለከብት ግብይት እንደመጡ የገለጹት አቶ ጌታቸው ሀይሉ በበኩላቸው፣ አርሶአደሩ የገበያ አማራጩ ያልሰፋለትና የመንገዱ ሁኔታ ያልተመቻቸለት በመሆኑ መጠቀም እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡ የእርስ በእርስ ግብይታቸውም በዚህና መሰል ጉዳዮች ፈተና እየገጠመው መሆኑን አንስተዋል፡፡
በጽጌረዳ ጫንያለው
ፎቶ -ከኢንተርኔት .