ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጽሐፍ የሚጽፉ ሰዎች እየበዙ ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት መጽሐፍ መጻፍ የሚችሉት ታዋቂና ምሁር የሆኑ ሰዎች ብቻ ይመስል ነበር። መጻፍ ለእነርሱ ብቻ የተሰጠ መታደል ተደርጎም ይቆጠር ነበር።
ይህ የሆነው ለመጽሐፍ ባለን አመለካከት ነው። መጽሐፍ በውስጡ የያዘው በሆሄያት የተጻፈ ሀሳብ ነው። ያ ሀሳብ ማለት በየቦታው የምናወራው፣ የምናየውና የምንሰማው ማለት ነው። የሆነ የሚያስገርም ነገር ስናይ ለቤተሰቦቻችን ወይም ጓደኞቻችን እንናገራለን፤ ደራሲዎች ደግሞ በልዩ ተሰጥዖና ፈጠራ ጨማምረው መጽሐፍ ያደርጉታል ማለት ነው።
እነዚህን ነገሮች በመረዳት ይመስላል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ ሰዎች መጽሐፍ ሲጽፉ እያየን ነው። በየመንገዱ አዟሪ ላይ ከማያቸው መጽሐፎች በተጨማሪ የማውቃቸው ሰዎች መጽሐፍ ሲጽፉ እያየሁ ነው፤ በጓደኛ በኩልም ‹‹አንብብለት›› ተብዬ ይደርሰኛል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አሁንም የሴት ደራሲዎች ቁጥር አነስተኛ ነው። በዛሬው የዘመን ጥበብ ዓምዳችን የሴት ደራሲዎች ቁጥር ለምን አነስተኛ ሆነ የሚለውን በተለያየ ጊዜ ካስተዋልኳቸው ትዝብቶችና መረጃዎች በመነሳት ቅኝት እናድርግ።
የደራሲዎች ሕይወት ለብዙዎቻችን ግልጽ ነው። በእርግጥ የሁሉም ደራሲዎች አይደለም፤ የአብዛኞች ነው ማለት ግን እንችላለን። ይሄውም ሕይወታቸው የቅንጦት አለመሆኑ ነው። ለቁሳዊ ነገሮች ብዙም ቦታ የላቸውም። አለባበሳቸውም ሆነ አካላዊ ገፅታቸው ዘረክረክ ያለ ነው። ይሄ ውጫዊ መለያቸው የተፈጠረው በውስጣዊ ባህሪያቸው ነው። ለውጫዊ ነገሮች ብዙም ትኩረት ስለማይሰጡ ነው። እዚህ ላይ ግን ሁለት ነገር ልብ እንበል! አንደኛ፤ ይህ የሁሉም ደራሲዎች መለያ አይደለም፤ ሁለተኛ፤ ይህ ቀደም ሲል በነበሩት ዘመናት ይታይ የነበረ መለያ ነው።
ደራሲዎች ልዩ የማስተዋል ችሎታ አላቸው። አንድ ደራሲ ሥራው ተወዳጅ የሚሆነውም በዚህ ልዩ የማስተዋል ብቃቱ ነው። ሌላው ሰው ሲኖርበት የነበረውን ቦታ ደራሲ ግን አንድ ቀን አይቶ ብዙ ነገር ይጽፍበታል። ያ ደራሲ የጻፈውን ነገር ሌላው ሰው ግን ልክ አይቶት እንደማያውቅ ሁሉ ‹‹እንዲህም ነበር እንዴ!›› እያለ እንደ አዲስ ያየዋል።
ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) 70 ደረጃ የተሰኘውን ነጠላ ዜማ ያወጣ ሰሞን ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም አንድ ነገር ጽፎ ነበር። ‹‹ማንም ሲወጣበትና ሲወርድበት የኖረውን 70 ደረጃ ቴዲ በልዩ ጥበብ ገለጸው፤ ከዚህ በኋላ 70 ደረጃን በድሮው አይናችን አናየውም›› ነበር ያለው በዕውቀቱ።
የበዕውቀቱ አስተያየት ልክ ነበር። የቴዲ አፍሮ 70 ደረጃ ነጠላ ዜማ ከወጣ በኋላ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሁሉ 70 ደረጃን እንደ አዲስ ማየት ጀመረ። ንግድ ቤቶች በስሙ መሰየም ጀመሩ። የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች 70 ደረጃ ይቀረጹ ጀመር። ፊልሞች ቦታውን ማሳየት ጀመሩ። 70 ደረጃ ግን ብዙ ዓመታት የኖረ ቦታ ነበር።
ደራሲ እንዲህ አይነት አካላዊና መልከዓ ምድራዊ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ስሜቶችንም በልዩ አስተውሎት ይገልጻል። ራሳችን የምናደርገውን ነገር ይገልጽልናል። የሰዎችን ስነ ልቦና ይረዳል። ለዚህም ነው ሥራዎቻቸውን ስናነብ የምንመሰጠው።
እነዚህን ሁሉ ነገሮች ለማስተዋልና ሀሳብ ለማግኘት ደራሲ ማንበብ አለበት። ማንበብ ሲባል የግድ መጽሐፍ፣ ጋዜጣ ወይም መጽሔት… በአጠቃላይ የተጻፈ ነገር ብቻ ማለት አይደለም። ሰው ይነበባል፣ ተፈጥሮ ይነበባል፣ ቁስ አካል ሁሉ ይነበባል፣ የሰው ስነ ልቦና ይነበባል። ይሄ ነው የደራሲ ብቃት።
ርዕሰ ጉዳያችን ስለሴት ደራሲያን ለማውራት ነው። ስለሴት ደራሲነት ለማውራት ደግሞ እነዚህን ነገሮች ልብ እንበል። ለመሆኑ ማህበራዊ ሕይወታችንና ስነ ልቦናችን ሴቶች ደራሲ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው? አንድ ደራሲ የሚደርስበት ቦታ የመድረስ ዕድል አላቸው? ነገሮችን ለማስተዋል የሚያስችል ሁኔታ አላቸው? ተፈጥሮንና አካባቢን ለመቃኘት የሚያስችል ማህበራዊ ነፃነት ተሰጥቷቸዋል?
አንድ ልብ ያልተባለ ችግር ይታየኛል። በብዙ ነገሮች የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ ነው። ያ የሆነው ግን በተፈጥሮ የችሎታ ልዩነት ሳይሆን በማህበራዊ አኗኗር ውስጥ በተፈጠረ ልዩነት ነው። ይሄ ችግር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዓለም የሚታይ ዓለም አቀፍ ችግር ነው። አሁን ግን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ብቻ እንመልከት።
ሴቶች በብዙ ነገሮች ከወንዶች እኩል እንዳይሳተፉ ያደረገው ማህበራዊ አኗኗራችንና በዚያ የተቀረጸው ስነ ልቦናችን ነው። እንደ ማሳያ የምጠቀመው አሁን ባለንበት ዘመን ላይ ባለው ውስጥ ያስተዋልኳቸውንና እየሆኑ ያሉ ነገሮችን ነው። አንዱ ችግር መስሎ የሚታየኝ ቅድሚያ ለሴቶች በሚል ሰበብ ሴቶች ላይ የደካማነት ስነ ልቦና መፍጠር ነው። ‹‹አልችልም እንዴ!›› ብለው ራሳቸውን እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ ነው። ግልጽ ለማድረግ ከዚህ በፊት በሌላ ጽሑፍ የገለጽኩትን አንድ ገጠመኝ ላንሳ።
ከአራት ዓመታት በፊት ነው። 123ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ለማክበር ጋዜጠኞች ወደ ዓድዋ እየተጓዝን ነው። በጉዟችን ውስጥ ታሪካዊ ቦታዎች ይጎበኛሉ። ከእነዚህም አንዱ ወረኢሉ ነው። አካባቢው ምቹ የመኪና መንገድ የለውም። አንድ ቦታ ላይ ስንደርስ መንገዱ ለመኪና አስቸጋሪ ስለሆነ በእግር ለመውረድ ተገደድን። እዚህ ላይ ነው አሁን የምነግራችሁን ነገር የታዘብኩት።
ልክ ጉዞ ስንጀምር ‹‹ሴቶች እዚህ ይቆዩ›› ተባለ። ቦታውን የሚያውቁ ሰዎች ‹‹ኧረ ቅርብ እኮ ነው ይሂዱ›› አሉ። ይሄኔ ‹‹እናት የላችሁም? እህት የላችሁም? እንዴት በሴት ልጅ ላይ ትጨክናላችሁ?›› የሚሉ ቁጣዎች ተነሱ። ይሄ ሁሉ ሲባል ነፍሰ ጡርም ሆነ በዕድሜ የገፋች ሴት የለችም። ሁሉም ወጣቶችና ጤነኛ ናቸው። በነገራችን ላይ ወደ ቦታው ስንወርድ አንድም ሴት አልቀረችም፤ ሁሉም አብረው ወረዱ። ከአሁን አሁን አደገኛ የተባለውን ቦታ አየዋለሁ ስል የሚጎበኘው ቦታ ላይ ደረስን። እንኳን ለወጣት ለአዛውንት ሴቶችም የሚያስቸግር ቦታ አልነበረም።
የእኔ ጥያቄ የግድ ቦታው አደገኛ መሆን አለበት አይደለም፤ ትንሽም ቢሆን የሚያስቸግር ከሆነ መቸገር የለባቸውም። ዳሩ ግን ይሄ እንዲህ አይነት ድጋፍ ሴቶችን አይጎዳም ወይ ነው። እያወራን ያለነው ስለሴት ደራሲነት ነው። ታዲያ ያንን ቦታ እንዳታይ የተከለከለች ሴት እንዴት ነው የታሪክ ፀሐፊ የምትሆነው? ያንን ቦታ እንዳታይ የተከለከለች ሴት እንዴት ነው ስለአገሯ ነባራዊ ሁኔታ ከወንዶች እኩል የምታወራው? ልዩ ምልከታና ሀሳብ የሚገኘው ደግሞ ከእንዲህ አይነት ቦታዎች እንጂ ከትልልቅ መዝናኛ ቦታዎችና ከሆቴሎች አይደለም። ደራሲና ጋዜጠኛ የሚጽፈው ከእንዲህ አይነት ቦታዎች እንጂ ከትልልቅ የገበያ ማዕከላትና ከጌጣጌጥ ቤቶች ብቻ አይደለም።
ለሴቶች ቅድሚያ መሰጠት አለበት። እንዲህ አይነቱ ግን ቅድሚያ መስጠት ሳይሆን ቅድሚያ መከልከል ነው። እስኪ የአምስት እና የአሥር ደቂቃ መንገድ በእግር ይሂዱ ማለት ምኑ ነው ‹‹እህት የላችሁም? እናት የላችሁም?›› የሚያሰኝ? እናቴ ወይም እህቴ በዚያ መንገድ ቢሄዱ ምን ይሆናሉ? ሴቶችን ማብቃት ማለትስ ይሄ ነው ወይ? የግድ ስቃይና መከራ ማየት አለባቸው እያልኩ አይደለም፤ ዳሩ ግን ከልክ ያለፈ ቁጥብነት ደግሞ ብዙ ነገር እንዳያዩ ያደርጋል።
ይሄ የሴቶች ጉልበት ብዝበዛ ወይም የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይደለም። ይሄ ፆታዊ ጥቃት አይደለም። አንድ ኪሎ ሜትር እንኳን በእግሯ የማትሄድ ሴት ደራሲ ልትሆን አትችልም። በመጽሐፍ ውይይቶች ለምን የሴት ደራሲያን ቁጥር አነሰ የሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ይሰማል። ዳሩ ግን ሴቶች እንዲጽፉና እንዲያስተውሉ የሚያደርግ ማህበራዊ ስነ ልቦና የለንም።
የሆነው ሆኖ ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ የጻፉ ብዙ ሴቶችም አሉን። እነዚያ ሴቶች እንዴት ደራሲ ሆኑ ካልን ወንዶች በዋሉበት መዋል ስለቻሉ ነው። እነዚህን ሴት ደራሲዎቻችንን ማየት አለብን።
ሕይወት ተፈራ
ሕይወት ተፈራ ለብዙ ሴቶች ምሳሌ የምትሆን ናት። ለዚያውም ሴቶች ብዙም አይሳተፉበትም በሚባለው ፖለቲካ ውስጥ የተሳተፈች። መሳተፍ ብቻም ሳይሆን የኖረችበትን ዘመንና ያሳለፈችውን ሕይወት የጻፈች። የሕይወት ተፈራን ሕይወት ካየን ‹‹ሴት ስለሆነች›› ከሚለው አጥር ውስጥ እንወጣለን። ምክንያቱም የተጋፈጠቻቸው ፈተናዎች ሁሉ ከባድ ነበሩ።
ሕይወት ተፈራ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የነበረች ናት። ኢህአፓንና የኢህአፓን ዘመን ያስተዋለችና የተሳተፈችበት ናት። ከ1965 ዓ.ም የኢህአፓ የወጣቶች ሊግ ጀምሮ ብዙ እንቅስቃሴዎችን አድርጋለች። ‹‹ማማ በሰማይ›› በሚለው መጽሐፏ ያን ሁሉ ታሪክ ነግራናለች። ለስምንት ዓመታት ያህል እስር ቤት ውስጥ ቆይታለች።
መጽሐፏ ብዙ ተብሎለታል። ሌሎች መጽሐፎችም አሏት። በነገራችን ላይ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የሴት ደራሲዎችን የሕይወት ታሪክና ሥራዎቻቸውን መዘርዘር ሳይሆን ስማቸውን እየጠቀሱ ‹‹እንዲህም አሉን›› የሚለውን ማሳየት ነው። በሥራዎቻቸው ዝርዝር ላይ በሌላ ጽሑፍ መመለስ ይሻላል።
ሽቶ መዝገቡ
‹‹ሰው በመሆኔ ደከምኩ›› በሚለው መጽሐፏ ትታወቃለች። ይህ መጽሐፍ ከ50 ዓመት በላይ ሆኖታል፤ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በ2006 ዓ.ም ከ48 ዓመታት በኋላ በድጋሜ ታትሞ ለገበያ ቀርቦ ነበር። ሽቶ መዝገቡ ገና በለጋነት ዕድሜዋ በኢትዮጵያ የባህል አብዮት ለማምጣት የታገለችና የጻፈች ናት። በነበረው ኋላቀር አስተሳሰብ ሴቶች ላይ ይደርስ የነበረው ነገር እንዲቀየር ትሰራ ነበር፤ የአሁኑን ዘመንም ከ50 ዓመታት በፊት ቀድማ ተንብያለች። ‹‹መማር እንጂ ለመማር ብሎ መማር አይገባም›› ሴቶች ላይ ይደርስ የነበረው ማህበራዊ አስተሳሰብ ለመቅረጽ ጥረት ያደረገች ናት።
የዝና ወርቁ
‹‹መፍቻው እና ሌሎች አጫጭር ልቦለዶች›› የሚል መጽሐፍ አላት። ከ12 እስከ 18 ዓመት ባሉ ታዳጊ ሴቶች ስነ ምግባር ላይ ያተኩራል። በነገራችን ላይ ይሄ መጽሐፏ በነጻ ታድሏል። ለ30 ያህል ትምህርት ቤቶች ተሰጥቷል። የጥያቄና መልስ ፕሮግራም ላላቸው የሬዲዮ ጣቢያዎች ተሰጥቷል።
ፀሐይ መላኩ
የሥነ ሥዕል፣ የሥነ ግጥም እና የእደ ጥበብ ሙያተኛ የሆነችው ደራሲ ፀሐይ መላኩ ከአሁን ቀደም አንጉዝ፣ ቋሳ እና ቢስራሔል የተሰኙ ረጅም ወጥ ልቦለድ መጽሐፎችን ለንባብ አብቅታለች። ‹‹እመ ምኔት›› የተሰኘው መጽሐፏ ደግሞ በቤተ ክርስቲያንና በገዳማት ታሪክና ትውፊት ላይ ያተኩራል። መጽሐፉን ከመጻፋቸው በፊት ሐይቅ እስጢፋኖስ አንድ ሱባኤ ከመቀመጣቸው በተጨማሪ ዝቋላ፣ አሰቦት፣ ራማ ኪዳነ ምሕረት፣ ዋሸራ እና ሌሎች ገዳማትን በመጎብኘት በመነኮሳት አኗኗር ላይ ጥናት በማድረግ አሥር ዓመታት ያህል ፈጅቶባታል።
ከበደች ተክለአብ
ሠዓሊ ናት፣ ቀራጺ ናት፣ ገጣሚ ናት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህር ናት። በርካታ የሕይወት ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች። ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ እንዲህ ብላ ነበር።
‹‹…በቀበሌና በወጣት ሊግ አማካይነት በተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳትፎ ማድረጌን ቀጠልኩበት። ይሄም ሆኖ ግን ወታደራዊው መንግስት፤ የቀይ ሽብር ዘመቻን አውጆ ተማሪዎችን ከያሉበት እያደነ ማሰርና በጅምላ መጨፍጨፍ ሲጀምር፣ እኔም ለዚህ ክፉ ዕጣ ከታጩት ታዳኝ ተማሪዎች አንዷ መሆኔን አወቅሁት። ከተጋረጠብኝ አደጋ ማምለጥ ነበረብኝ። ለአንድ አመት ከመንፈቅ ያህል ከሌሎች አምስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ተደብቀን ቆየን። በስተመጨረሻም ድንበር አቋርጠን ጅቡቲ ለመግባትና ጥገኝነት ለመጠየቅ በማሰብ፣ በ1971 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወጣን። በድብቅ ድንበሩን ሊያሻግሩን ፈቃደኛ የሆኑ ነጋዴዎች ብናገኝም፣ ሙከራችን ግን እጅግ አደገኛ ነበር። አቋርጠነው ልናልፍ ባሰብነው ድንበር ላይ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ገጥመው ነበር። ይህ መሆኑን ሳናውቅ ነው፣ በእግራችን ጉዞ የጀመርነውና የሶማሌ መደበኛ ጦርና የሶማሊያ ነጻ አውጪ ግንባር ወታደሮች ሰፍረውበት ወደነበረው የጦር ካምፕ ሰተት ብለን የገባነው። በቁጥጥር ስር ውለን ወደ ሶማሊያ ተወስደን ታሰርን። በሁለቱ አገራት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ከሶስት አመታት ጦርነት በኋላ ቢጠናቀቅም፣ እኛ ግን ቀጣዮቹን አስር አመታት ያሳለፍናቸው በሶማሊያ እስር ቤቶችና የጉልበት ስራ ካምፖች ውስጥ ነው። በስተመጨረሻም በኢጋድ ስብሰባ ላይ በተደረገ ስምምነትና በአለማቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅት አግባቢነት ይመስለኛል፣ ሁለቱ አገራት የጦር እስረኞችን ለመልቀቅ ፈቃደኞች ሆኑ። እኛም በ1981 ዓ.ም ከእስር ተፈታን…››
የእነዚህን ሴት ደራሲያን ሕይወት መቀንጨብ ያስፈለገው ያለ ምክንያት አይደለም። ሴትም ትሁን ወንድ ደራሲነት አንድ ቦታ ቁጭ ብሎ እንደማይሆን ነው። አንድ ደራሲ ያላየውንና ያልሰማውን ሊጽፍ አይችልም። እርግጥ ነው ደራሲ ለመሆን ሲባል መጎሳቆልና መንገላታት ያስፈልጋል ማለት አይደለም። ቢያንስ ቢያንስ ግን አካባቢን እንኳን ለማስተዋል የሚያስችል እንቅስቃሴ መኖር አለበት። ይሄ ደግሞ ለደራሲነት ብቻ ሳይሆን ለየትኛውም ሥራ ቢሆን አካባቢን ማስተዋል የግድ ነው። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ‹‹ሴቶችና ሳይንስ›› በሚል ባዘጋጀው አንድ መድረክ ላይ አንዲት ጥናት አቅራቢ ይህንኑ ጉዳይ ሲናገሩ ሰምቼ ነበር። ሴቶች በሳይንስ ተመራማሪ ይሆኑ ዘንድ አካባቢያቸውን ማስተዋል አለባቸው። ለዚህም ማንኛውም ሰው ሊያደርገው የሚችለውን የእንቅስቃሴ ዕድል ማግኘት አለባቸው፤ ተፈጥሮን ማስተዋል አለባቸው።
ሴት ደራሲያን በጣም ጥቂት ናቸው። በግጥምና በፊልም ላይ ነው አብዛኛው ተሳትፏቸው፤ ብዙ የግጥም መድብል ያላቸው ሴቶች አሉን። ግጥም ደራሲ አያሰኝም ማለቴ አይደለም፤ እንዲያውም ትልቁ የጥበብ ጥግ የሚባለው ነው። ዳሩ ግን በፖለቲካና በታሪክ ፀሐፊነት ደግሞ በጣም አነሱ። እንደነ ገነት አየለ አይነት የታሪክ ፀሐፊዎችም ሊኖሩን ይገባል።
ከላይ የጠቀስናቸው ሴት ፀሐፊዎች መጽሐፍ የጻፉት ለመጻፍ የሚያስችል እንቅስቃሴ ስለነበራቸው ነው። የታደለች ኃይለሚካኤል መጽሐፍ(ዳኛው ማነው) የተጻፈው በእንደዚያ አይነት እንቅስቃሴ ውስጥ ስላለፈች ነው። ስለዚህ ደራሲ ለመሆን ስቃይና መከራ ማሳለፍ የግድ ባይሆንም አካባቢን መቃኘት ግን የግድ ነው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም