ከሰላሣ ስድስት ዓመት በፊት የታተሙ የአዲስ ዘመን ጋዜጦች የዛሬ ትኩረታችን ናቸው። ከተመለከትናቸው የጋዜጣው ዘገባዎች መካከል ከአደጋዎች፣ ከወንጀል እንዲሁም የትራንስፖርት ደንብን ከመተላለፍ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ዜናዎቹ በወቅቱ ጅቡቲን ጨምሮ በምሥራቅ፣ በደቡብና በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል የተፈጸሙ ክስተቶች ሲሆኑ ለትውስታ ያህል እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል፡፡
በባቡር አደጋ 9 ሰዎች ሞቱ
ጅቡቲ፡-(ኢ-ዜ-አ-) ፤ ከጅቡቲ ወደ ድሬዳዋ ይጓዝ የነበረ አንድ የሕዝብ ማመላለሻ ባቡር የካቲት ፳፱ ቀን ፲፱፻፸፱ የሐዲድ መስመር ስቶ በመውጣቱ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ ፴፮ ሰዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የጅቡቲ ሪፑብሊክ መንግሥት የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
አደጋው የደረሰው ከጅቡቲ ዋና ከተማ ፶፭ ኪሎ ሜትር ላይ በሚገኘው ሆል-ሆል በሚባል ቦታ ነው፡፡ ከጅቡቲ በደረሰው ሪፖርት መሠረት የባቡሩ ጐታች ሆል-ሆል በሚባለው አካባቢ አንድ ቁልቁለታማ ሥፍራ ከሐዲድ መስመር መውጣቱን አረጋግጧል።
(መጋቢት 1 ቀን 19 79 የወጣው አዲስ ዘመን)
ከ138 ሺ ብር በላይ ያጎደለው 14 ዓመት እሥራት ተፈረደበት
ሐረር (ኢ-ዜ-አ-)፤ በሐረር ክፍለ ሀገር የዋርደር አውራጃ ገቢዎች ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ተጠሪና ገንዘብ ያዥ ሆኖ ሲሠራ ፩፻፴፰ ሺህ ፭፻፸፱ ብር ያጎደለው ፍቅሩ ወልደማርያም በአሥራ አራት ዓመት ጽኑ እሥራት እንዲቀጣ የልዩ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ችሎት የካቲት ፴ ቀን ፲፱፻፸፱ ወሰነ፡፡
ልዩ ፍርድ ቤቱ በተከሳሹ ላይ ከላይ የተጠቀሰውን እስራትና ፮፻ ብር መቀጫ የወሰነው በሥራው አጋጣሚ በእጁ ከገባው ገንዘብ ውስጥ ፩፻፴፰ ሺህ ፭፻፸፱ ብር አጉድሎ ለመገኘቱ በዐቃቤ ሕግ የቀረቡትን ማስረጃዎች መርምሮ ካመሳከረ በኋላ ነው።
የፍትሐ ብሔሩን በሚመለከትም ተከሳሹ ያጠፋውን ገንዘብ ወለድ ከነዳኝነቱ ጭምር እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ ጨምሮ ወስኗል፡፡
(መጋቢት 11 ቀን 19 79 የወጣው አዲስ ዘመን )
ሰባት የነብር ቆዳ ደብቆ የተገኘው ተቀጣ
አዋሳ (ኢ-ዜ-አ) ፤በሲዳሞ ክፍለ ሀገር ከሰባት የነብር ቆዳዎችን ደብቆ የተገኘው አንድ ሺህ ብር መቀጫ እንዲከፍል የጌዴኦ አውራጃ ፍርድ ቤት ሰሞኑን ፈረደ፡፡
ሶሬሳ ደበሌ የተባለው ይኸው ግለሰብ ቆዳዎቹን በኮባ ቅጠል ሸፍኖ የጫት ቅጠል በማስመሰል በተሽከርካሪ ወደ አዲስ አበባ ለማሳለፍ ሲሞክር መያዙ ተረጋግጦበታል፡፡
ተከሳሹ የተያዘው በአውራጃው ፊናንስ ፖሊስ አባሎች ቁጥጥር አማካይነት ነው፡፡
( መጋቢት 11 ቀን 19 79 የወጣው አዲስ ዘመን)
በዕቃ መጫኛ መኪና ሰዎችን ያሳፈረ ተቀጣ
ምንጃር (ኢ-ዜ-አ)፤ በሸዋ ክፍለ ሀገር በምንጃር ወረዳ በዕቃ መጫኛ ቶዮታ መኪና ላይ ሰባት ሰዎች አሣፍሮ የተገኘው ሾፌር ሦስት መቶ ብር መቀጫ እንዲከፍል የአውራጃው ፍርድ ቤት ሰሞኑን ወሰነ፡፡
አበራ ተድላ የተባለው ይኸው ሾፌር የታርጋ ቁጥር ፲፬ ሺህ ፴፯ አ-አ- በሆነ ቶዮታ የዕቃ መጫኛ መኪና ላይ መጋቢት ፫ ቀን ፲፱፻፸፱ ከሞጆ ከተማ ወደ ምንጃር አረርቲ ከተማ ዕቃ ጭኖ በሚጓዝበት ጊዜ በዕቃው ላይ ሠላሳ ሰባት ሰዎችን አሣፍሮ መገኘቱ በምስክር ተረጋግጧል።
( መጋቢት 19 ቀን 19 79 የወጣው አዲስ ዘመን )
ነፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ 56 ቤቶች አፈራረሰ
አሰላ (አ-ዜ-አ-)፤ በአሩሲ ክፍለ ሀገር በአጐልቶ ከተማ በዜሮ አንድ ልዩ ቀበሌ መጋቢት ፲፯ ቀን ፲፱፻፸፱ ነፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ ሃምሳ ስድስት ቤቶች ፈራርሰዋል፡፡
ቤታቸውም የየቀበሌው ነዋሪዎች ጊዜያዊ መጠለያ ተዘጋጅቶላቸው በመረዳት ላይ መሆናቸውን የአሩሲ ክፍለ ሀገር ከተማና ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ነፋስ ቀላቅሎ በጣለው ዝናብ ከአገልግሎት ውጪ ከሆኑት ቤቶች መካከል ፲፰ የግለሰቦች ቤቶች ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ፴፰ መንግሥት በቁጠባ ያሠራቸው ቤቶች መሆናቸው ታውቋል።
( መጋቢት 19 ቀን 19 79 የወጣው አዲስ ዘመን )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም