የአፍሪካ ኅብረት መቋቋምን ከወጣትነት ጀምሮ ሲከታተሉት አድገዋል። አፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር ሲፈራረሙ በአካል ቆመው ታዝበዋል። ደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ደግሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት በአካል ተገኝተው ታዛቢ ነበሩ። በወጣትነት ዘመናቸው በጋዜጠኝነት አገልግለዋል። በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን በብስራተ ወንጌል የራዲዮ ስርጭት ሲጀመር በአማርኛ አስተዋዋቂነት ተቀጥረው ሠርተዋል። በትርፍ ጊዜ ሲሠሩ የነበረውን ሥራ ወደ ሙሉ ጊዜ ቀየሩት። የእንግሊዝኛ ክፍልም ማኔጂንግ ኤዲተር ሆነው አገልግለዋል።
የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት ሲገረሰስ ነበሩ፤ አለፍ ሲልም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል ታዛቢ ሆነው ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንተዋል። ‹‹እኔ የአፓርታይድ ሥርዓት ሲገረሰስ ነበርኩ፤ ከዚያም ኒልሰን ማንዴላን በማስመረጤ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል›› ይላሉ ያለፉበትን የዲፕሎማትነት የስኬት ዘመናት በጥቂቱ ‹ዓባይን በማንኪያ› ዓይነት ጨዋታ በቁምነር ሲያስታውሱት።
የተወለዱት በአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት መናገሻ በርፈታ የሚሰኝ ሰፈር ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሆለታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ደብረብርሃን ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ቀስመዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ሶሾሎጂ ተምረዋል። ጀርመን አገር የመሄድ ዕድል አግኝተው ስለነበር የሚዲያን ሕግ ቀሰሙ። እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ሼፊልድ ደግሞ በጋዜጠኝነት ዲፕሎማ አግኝተዋል። ቢቢሲ እና ሮይተርስ ደግሞ የልምድ ስልጠና ወስደዋል። በአሁኑ ወቅት 80 ዓመት ደፍነዋል፤ ግን ከሙያቸው አልተናጠቡም። ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አገራቸውን ወክለው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመንቀሳቀስ የዜግነት ድርሻቸውን ተወጥተዋል- አምባሳደር ተፈራ ሻወል።
አዲስ ዘመን፡-ወደ አምባሳደርነት የገቡበትን ሂደት ያስታውሳሉ?
አምባሳደር ሻወል፡- የኢትዮጵያ አውሮፕላን በፍራክፈርት ላይ በሻዕቢያ ተመትቶ ነበር። በዚያን ወቅት ሚዲያዎች ሁሉ በጣም ተቀባበሉት። በተለይም ኢትዮጵያን ለማጉደፍ ሲሞክሩ ፈረንጆች ዝቅተኝነታቸው ይታወቅባቸዋል። ትንሽ ችግር ካገኙ የበታች መሆናቸው እስከሚታወቅባቸው ድረስ የሚያሳብቁት በጣም በመቀባበል ነበር። በወቅቱ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከተማ ይፍሩ ‹ወደ ጀርመን ቦን ከተማ ሄደህ የግርማዊነታቸው ኤምባሲ ሁለተኛ ጸሐፊ እንዲሁም የፕሬስ ክፍል ኃላፊ ሆነህ ሥራ› ባሉኝ መሠረት ወደዚያ አቀናሁ። በፕሬስ ክፍል ኃላፊነት እየሠራሁ ወደ ሱዳን ካርቱም ተዘዋወርኩ። በዚህም አንደኛ ጸሐፊ እና ፖለቲካ ባለሙያ ሆንኩ። በሂደት መንግሥት ለውጥ መጥቶ የደርግ ሥርዓት ተተካ። በወቅቱ የሶሻሊዝምን አብዮት የምቀበል ቢሆንም ግን ጭልጥ ያለ የኮሚኒዝምን ሥርዓት ስለማልቀበል በወቅቱ ከነበሩት ኃይሎች ጋር ግጭት ተፈጠረ፤ ሦስት ዓመትም ታሰርኩ።
ከሦስት ዓመት እስር በኋላ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ጠርተውኝ ‹ተሳስተናል፤ ምሁራንን ማሰርና ማሰቃየት አልነበረብንም፤ በምን ልካስህ› ብለው ጠየቁኝ። እኔም በይቅርታቸው ተገርሜ፤ ሲሆን እኔ ነኝ ይቅርታ መጠየቅ የነበረብኝ አልኳቸው። በመቀጠል የእኔ ህልምና ርዕዮተ-ዓለም አገሬንና ሕዝቤን ማገልገል ነው። የእኔ ህልም የኢትዮጵያ ዕድገት ነው አልኩኝ። በዚህ ተስማማን።
አዲስ ዘመን፡- ከስምምነቱ በኋላ ወደየት አመሩ?
አምባሳደር ሻወል፡-እንደገና ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመልሼ የፕሬስ መምሪያ ኃላፊ ሆንኩኝ። እዚህ እየሠራሁ የቀይ መስቀል በበጎ አድራጎት ብዙ እርዳታም ማሰባሰብ ቻልኩ። ቀይ መስቀልንም ተቀላቀልሁ። ይህ እንደ ትልቅ ነገር ተቆጥሮ ወደ ውጭ ሄደህ በጀርመን፣ ቼኮዝላቪያ፣ በምሥራቅ ጀርመን አምባሳደር ሁን ተባልኩ። በመጀመሪያ ሚኒስትር ካውንስለር በኋላ ደግሞ አምባሳደር ሆንኩኝ። በእርግጥ እኔ የትም ቢያደርጉኝ አገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ። ጀርመን እያለሁ ሌላ ለውጥ መጣ። ከዚያ ወደ ቼኮዝላቪያ ዞሬ ፖላንድ፤ ሃንጋሪ፣ እያለገልኩ እያለሁ ሕወሓት በትረ ስልጣኑን ተቆጣጠረ። በዚህም በውጭ የነበሩ አምባሳደሮችንና ንክኪ ያላቸውን በሙሉ አነሷቸው። እኔም ልጆቼን ይዤ ወደ አገሬ መጣሁ።
አዲስ ዘመን፡- ወደ አገርዎ ሲመጡ ምን አጋጠምዎ?
አምባሳደር ተፈራ፡– እኔ አገሬን በጣም እወዳለሁ። አገሬን ለማገልገል ነበር የሄድኩት፤ የተመለስኩትም ወደ አገሬ ነው። በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትም ከዚህ በላይ ጀግንነትና አርበኝነት የለም፤ በዚያው ልትጠፉ ነው ሲባል ነበር አሉኝ። ‹‹እኔ አገሬን ለወያኔ ትቼ አልጠፋም›› አልኳቸውና ትንሽ እንደመገረም አሉ። ትንሽ ቆይተውም ‹አግዘን› የሚል ጥያቄ አቀረቡልኝ። ከዚያም ቀድሞ ስሠራበት በነበረው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሬስ መምሪያ እንደ ኃላፊ ሆኜ መሥራት ጀመርኩ።
የኤርትራን መገንጠል አስመልክቶ ውይይት ነበር። ይህ ነገር ወደ ጦርነት ያመራል፤ በሠላም እንፍታው፤ በኮንፌዴሬሽን ይታይ ስላቸው ሃሳቤን ብዙም አልተቀበሉትም። በዚህን ጊዜ ያለጡረታ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስወጡኝ። በዚህ ሁኔታ ሳለሁ ጀርመን ስሠራ ያውቁኝ ስለነበረም ከጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት ደወሉልኝ። የፕሮጀክት ሥራ ሰጡኝ፤ እናም ትግራይ ሄጄ ከኤርትራ የተፈናቀሉትን እንዴት ማስፈር እንደሚቻል ማስተባበር ጀምሬ ፕሮጀከቱን አጠናቀቅሁ።
በነገራችን ላይ ልጅ ሆነን ከኮፊ አናን ጋር እንተዋወቅ ነበር። ወጣት ሆኖ በአፍሪካ ኅብረት ይሠራ ነበር። በአጋጣሚ ተገናኝተን ምን እየሠራህ ነው ብሎ ጠየቀኝ። አማካሪ ነኝ ብዬ ነገርኩት። ከዚያ ምዕራብ አፍሪካ ዩኒሴፍ አማካሪ ሆነህ ሥራ አለኝ፤ ሠራሁ። ወደ አንጎላም ሄጄ ዩኒሴፍ አማካሪ ሆኜ ሠራሁ። ጥናቶችም ሠርቼ ተቀባይነት አገኘ። ጥናቱን ያዩት አንድ ጃፓናዊ እኔ ዘንድ ሥራ ብለው ጠየቁኝ። እኔም በዚህ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመሥራት ዕድል አገኘሁ።
እንግዲህ ቀይ መስቀል፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ሌሎች ቦታዎች መሥራቴ ተፈላጊ አደረገኝ። ዳሩ ግን ጃፓናዊው ወደ አገራቸው ሲመለሱ እኔም ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ። በመቀጠል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ቢሮ ኃላፊ ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። በተባረርኩት ኢህአዴግ መንግሥት ተመልሼ የሹመት ደብዳቤዬን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን ሰጠሁ።
በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ከተለያዩ አካላት ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ ብዙ ሠርቻለሁ። ሌሎች የቀድሞ አምባሳደሮችም ነበሩ። እኛ ዓማላችን አገራችንን ማገልገል ነው። በመጨረሻ በዚህ ሥራዬ ወደ ካሜሩን፣ ምዕራብ አፍሪካ እና ሌሎች አገራትም አቀናሁ። በጀኔቫ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ከፍተኛ አማካሪ ሆኜ ተቀጠርኩ። በመጨረሻ ደግሞ ባግዳድ ችግር ተፈጠረ። በዚህ ጊዜ ኮፊ አናንን አገኘሁ። ‹አሁን ወደየት ነህ› ብለው ሲጠይቁኝ ወደ አገሬ ነው፤ ጡረታዬም እየደረሰ ነው አልኳቸው። ግን ኮፊ አናን እኔ ጡረታ ሳልወጣ አትወጣም አሉኝ።
በኢራቅ ባግዳድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስትራቴጂክ ፕላኒንግ ዳይሬክተር ሆኜ ተመደብኩ። ሳዳም ሁሴን ሲታሰር ገባሁ፤ ሲሰቀል ወጣሁ። የፍርድ ሂደቱን ሁሉ ስከታተል ነበር። በመጨረሻም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ62 ዓመቴ ጡረታዬን ተቀብዬ ወጣሁ። ከጡረታ በኋላ የኢህአዴግ መንግሥት የምሥራቅ አፍሪካ የሠላም ጥበቃ ኃይል በናይሮቢ ላይ ስለተቋቋመ የዚያ ዳይሬክተር ሁን አሉኝ። እኔም ተስማማሁ፤ ሦስት ዓመት ሠርቼ መጣሁ።
ከናይሮቢ ስመለስ ደግሞ አፍሪካ ህብረት ካርቱም ሄደህ ሰብዓዊ እርዳታ የብሉ ናይል እና ኮርዱፋን ስቴት ተወካይ ሆነህ ሥራ ተባልኩኝ፤ ሁለት ዓመትም ሠራሁኝ። ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ ከእነ አምባሳደር ተቀዳ ዓለሙ እና ሌሎች አምባሳደሮች ጋር በመሆን የትብብር፣ ምክክርና ጥናትና ማዕከል መሠረትን፤ አሁንም የቦርድ አባል ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ልጅዎ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ በአምባሳደርነት ኢትዮጵያን አገልግለዋል። የእርስዎ ተፅዕኖ ይኖር ይሆን?
አምባሳደር ተፈራ፡– ተፅዕኖ ሊኖር ይችላል። እኔ የምሠራቸው ሥራዎችን እየተመለከተ ስላደገ ምናልባት የራሱ ግምት ወስዶ ይሆናል። ከሦስቱ ልጆቼ አንዱ የሆነው ልጄ ሄኖክ አገሩን ባለፉት አራት ዓመታት በአምባሳደርነት አገልግሏል። ከአሁን በኋላ መንግሥት ወደየት እንደሚመድበው አላውቅም። ሄኖክ በዓለም አቀፍ ግንኙነት፤ በኢኮኖሚክስ እና በሕግ ምሩቅ ነው። ፕሮግራም ኢንጅነሪንግ ተምሯል። እነዚህ ተደማምረው ለጥሩ ውጤት አብቅቶታል። ልጆቼን በአጠቃላይ በጥሩ ሁኔታ እንዲማሩ ነው ያደረኩት። በአጠቃላይ አገራቸውን በጽኑ ፍቅር ማገልገል እንዳለባቸው ነው ያስተማርኩት እና ያሳደኩት።
አዲስ ዘመን፡-በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጦች መካከል እርስዎ ወዲህ ወዲያ ሲዘዋወሩና ሲያገለግሉ አልተቸገሩም?
አምባሳደር ተፈራ፡- የእኔ ትልቁ ምስል አገሬን ማገልገል ነው። ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም መለዋወጥ ጋር ሳይሆን የእኔ ጉዳይ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ጥቅሟ እንዴት ይከበራል ብዬ ነው የምጨነቀው። በእርግጥ እስር ቤት ቀምሻለሁ፤ ችግር ደርሶብኛል። ልጆቼን ይዤ በየአገሩ ስዞር ነበር። ብዙ ፈተና ነው ያሳለፍኩት። ግን ለአገሬ፤ ለቤተሰቤ፣ ለወገኔ ያለኝ ፍቅር ጥልቅ ስለሆነ ብዙ ነገሮችን ማለፍ ችያለሁ። ለዚህ የፈጣሪም እርዳታ ታክሎበት ነው። ብዙ ፈተናዎችን ባለፍን ቁጥር ጠንካራ እንሆናለን። እኔ ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር እንጂ በአገሬ ጉዳይ ቅያሜን አላውቅም። ከአገሬ ወደየት እሄዳለሁ፤ ለማንስ እተዋታለሁ፤ ምንስ መሄጃ አለኝ?
በእኛ አገር ትልቁ ችግር የአገረ መንግሥት ባህላችን ያለፈውን እያወገዝን የመጣውን ማንገስ ነው። ይህ አገራችንን እየጎዳት ነው። መሆን ያለበት ያለፈውን ሥርዓት ከፖለቲካው ሥርዓትም ይህን በኢኮኖሚው መሠረት የያዙና መልካም የምንላቸውን ጠንካራ ጎኖችን በመውሰድ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ ነው። ደካማ ጎኖችን ደግሞ በጠንካራ መንገድ መተካት ነው። ትልቁ ምስል መሆን ያለበት ግለሰቦች ሳይሆን አገርን ማዕከል ያደረገ ሥራ መሥራት ነው። የእኔ እምነት አገሬን ማስቀደም ነው። ለዚህም ስል በሥርዓት መለዋወጦች ውስጥ በርካታ ፈተናዎች ቢደርሱብኝም እኔ ለአገሬ ስል ነገሮችን እረሳለሁ፤ ወደመልካም ሁኔታም እቀይራቸው ነበር። በተቻለ መጠን ነገሮችን በመወያየትና አስተዋይነት ማለፍ ነው የሚጠቅመው።
እኔን በደርግ ጊዜ ያሳሰሩኝ ሰዎች አውቃለሁ። ከእስር ቤት ስወጣ ግን አቅፌ ነው የሳምኳቸው። ፍቅርና ይቅር መባባል ይበልጣል። በማንኛውም ጊዜ ይቅርታ ችግሮችን ይፈታል። ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ እና ለምለም አገር ናት። አሁን ካሉት 80 ብሔሮች በተጨማሪ ሌላ 80 ብሔር ቢጨመር ትበቃለች። ትልቁ ጥበብ በፍቅር መምራት፤ በይቅርታ መተላለፍ፤ በመቻቻልና በአስተዋይነት መራመድ ነው። አንዱ የሌላውን መብት ካከበረ እና መቻቻል ካለ ነገሮች ሁሉ መፍትሄ አላቸው።
ጎጥ እየፈለጉ መናከስ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቀረ ክስተት ነው። ይህ ዘመኑና ፋሽኑ አልፎበታል። አውሮፓ ውስጥ ተጋጭተው! ተጋጭተው! አልፈውበታል። ምንም እንደማይጠቅማቸው ስላወቁ አንድነታቸውን አጠናክረው አሁን በዓለም ላይ ኃያላን ሆነዋል። አሁን አውሮፓውያን በአንድ ገንዘብ ይገበያያሉ። እኔ በተረዳሁት መጠን አሁን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ህልማቸው ይህ ነው። የግል ፍላጎታችንን ገታ አድርገን እንደ አገር በማሰብ ልናግዛቸው ይገባል። የጋራ ዕድገት፤ ብልጽግና እናስብ።
አዲስ ዘመን፡- በዲፕሎማት ዘመንዎ ሌሎች አገራትና ዲፕሎማቶች እንዴት ነበር ኢትዮጵያን የሚገልጿት?
አምባሳደር ተፈራ፡- ኢትዮጵያን ጥንቅቅ አድርገው ያውቃሉ። ታሪኳን ደጋግመው ያነበቡ አሉ። ለባህላችንና ማንነታችን ያላቸው ክብር በጣም ከፍተኛ ነው። ብቸኛ የአፍሪካ የፅሁፍ ቋንቋ ያላት ሀገር ኢትዮጵያ ናት። የመጀመሪያው የአፍሪካ ቻርተር የተፃፈው በአማርኛ ነው። መንግስታት ፊርማቸው ያረፈበት በአማርኛ በተጻፈው ላይ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ በርካታ ታሪክና ዝና ያላት አገር ናት። ለአገራችን ቋንቋ፣ ባህል፣ ማንነት ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል። ግን እኛ በዚህ ደረጃ ዋጋ እንሰጣለን፤ እናውቀዋለን ወይ ካልን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል።
የኢትዮጵያን ቋንቋ በአውሮፓ እና አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎችና የተለያዩ አገራት ትምህርት ይሰጣል፤ ምርምር ይደረግበታል። እኛ ግን ችላ ብለናል። ያለንን እሴት ማሳደግና ማበልጸግ ይጠበቅብናል። በርካታ አውሮፓ፣ በሞስኮ እና ሌሎች አገራት ዩኒቨርሲቲዎች በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ላይ በሰፊው ይሠራሉ። በሃይማኖታችን፣ ባህላችንና ማንነታችን ልናጠፋ የምንሯሯጠው እኛ ነን።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን ሲያብጠለጥሉ የነበሩ አገራት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ መስለው ቀርበዋል። ይህን በዲፕሎማሲ እይታ እንዴት ይገልጹታል?
አምባሳደር ተፈራ፡- አዲስ ነገር አይደለም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ናቫል የሚባል የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ሆር የሚባል የእንግሊዝ ሚኒስትር አንድ ላይ አብረው ሌግ ኦፍኔሽን ላይ ኢትዮጵያን ሲያብጠለጥሉና ሲከሱ ቆይተው ነበር። በኋላ ግን ኢትዮጵያ ጥብቅ አቋም ይዛ በመጓዟ እና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስደፈር ፈቃደኛ ባለመሆኗ እንዲሁም ፍትህ ይሰፍን ዘንድ ፋሺዝምን በመወጋቷ አሸናፊ ሆናለች። በዚህም ጠንካራ በመሆናችን ከአሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ጋር ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት መመስረት ችለናል።
ምዕራባውያን የሚያዩት ዘላቂ ጥቅማቸውን እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የላቸውም። ስለዚህ እኛ ደግሞ መማር ያለብን የኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ምንድን ነው ብለን ማሰብና ማስቀመጥ ነው። ልማት፣ ወንድማማችነት፣ የአገር ግዛት አንድነት መጠበቅ ፍትህ እና ሕግን ማስከበር ነው። ይህ ከሆነ ዘላቂ ጥቅማችን ማስከበር እንችላለን።
አፄ ኃይለሥላሴ ከኮሚኒስቶች፣ ዴሞክራቶች፣ ሶሻሊስቶች ጋር ሁሉ ወዳጅነት ነበራቸው። ይህን ሲያደርጉ የነበረው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ነው። የእርሳቸውን ጥረት በቀላሉ ማየት የለብንም። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ብዙ እየለፉ እንዳለ ይገባኛል። ታዲያ ይህን ጥረታቸውን እኛም ማገዝ አለብን። አገር ጥቅሟ የሚከበረው በአንድ ግለሰብ ወይንም ቡድኖች ስብሰብ አይደለም። ሁላችንም በየሙያ መስካችን ትልቅ ኃላፊነት አለብን። መሪዎች ሰዎች ናቸው የሚቀያየሩ፤ አገር ግን ዘላቂ ናት ሁሉንም የምትችል። ስለዚህ ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብረው የተባበረ ክንድ እንጂ የተወኑ አካላት ብቻ አይደሉም።
በሰሜን ኢትዮጵያ የሆነው ብናስታውስ አግባብ አልነበረም። ራሳቸው ያረቀቁትን ሕገ መንግሥት ጥሰው ነው ችግር የተፈጠረው። ይህ ሕግ ካለማከበር የሚመነጭ ችግር መደገም የለበትም። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አስቦ ቁጭ ብሎ መወያየትን መልመድ አለበት። ትምህርት ቤቶች በትምህርት ሥርዓታቸው አገራዊ አንድነት፤ ግብረ ገብነትና አንድነትን ማዕከል ያደረገ ትምህርት ሊያስጨብጡ ይገባል። ሁሉም ነገር ከመሠረቱ ያማረ እንደሆነ ውጤቱም ያማረ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን ችግር በገጠማት ጊዜ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ሲደረግ የነበረውን ያለፉት አራት ዓመታት የዲፕሎማሲ ሂደትን እንዴት ይገመግሙታል?
አምባሳደር ተፈራ፡– ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁሉም የአገሩን ጥቅም ለማስከበር ይለፉ ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በዚህ ደረጃ ሲሠራ ነበር። ርዕሰ ብሔሩም በዚህ ላይ ጠንካራ አቋም ነው ያላቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ የሥርዓት መለዋወጦች ቢኖሩም የአገሪቱን ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ ሁሉም አስተዋፅኦ አድርገዋል። በዘመናት መለዋወጥ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚበጃትን የሚያውቁ ብልህ መሪዎችና ሚኒስትሮችና አምባሳደሮች ነበሯት፤ አሁንም አሏት። ስለዚህ ባለፉት ዓመታትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የተሄደበት ርቀት በጣም ጥልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምን ነገሮች ይጎድሉናል?
አምባሳደር ተፈራ፡– በርካታ ጥሩ ነገሮች አሉን። ነገር ግን አሁንም የሚጎድሉን ነገሮች አሉ። ብዙውን ጊዜ ከዘመኑ ወይንም ጊዜው ጋር አብሮ አለመሄድ አለ። ዲጂታል ዲፕሎማሲ ላይ መሥራት አለብን። የመጠራጠር ዲፕሎማሲን ማስወገድ ይገባል። በአንድ አገር የሚሾም ዲፕሎማት ስለዚያች አገር መረጃ አብጠርጥሮ ማወቅና መረዳት ከዚያም ለአገሩ በሚጠቅም መንገድ መስጠት እና መጠቀም አለበት። ለዚህ ደግሞ የቋንቋ ክህሎት፣ መማር፣ ማንበብ፣ እይታን ሰፋ ማድረግና መሰልጠን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በአሁኑ ወቅትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲፕሎማቶችን እያሰለጠነ ነው የሚልከው። ይህ የሚበረታታ ነው። ከተወሰኑ መንጠባጠቦች በስተቀር ሁሉም ዲፕሎማት ለአገሩ ያገለግላል። እኛ ማንነታችንና ምንነታችን ላይ አተኩረን መሥራት አለብን።
አዲስ ዘመን፡- የዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘመን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታስ እንዴት ይገፁታል? አስፈላጊነቱስ?
አምባሳደር ተፈራ፡- በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ ዲጂታል ዘመን ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳትም አለው። በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ በቂ እውቀትና መረጃ ለማስተላለፍ ያስችላል። በቀላሉ ሐሳብ ለማሰራጨት ትልቅ ፀጋ ነው። ቲውተር፤ ዩቲዩብ፤ ፌስ ቡክ፤ ኢሜል በቀላሉ መታየት የለባቸውም። በተደራጀ እና በተናበበ መንገድ መጠቀም ከተቻለ በቅርበትና በፍጥነት መረጃ ለማስተላለፍ ይጠቅማል። እኛ ማድረግ ያለብን በዲጂታል ዓለም የፖለቲካ ገበያው ለራሳችን ጥቅም ማስጠበቂያ አድርገን መጠቀም ይገባል። ዲጂታል ዲፕሎማሲን በአግባቡ ልንጠቀመው ይገባል። ኢትዮጵያም በዚህ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል።
አዲስ ዘመን፡- የውስጣዊ ግጭቶች ከሌሎች አገራት ጋር ለሚኖረው ዲፕሎማሲ ተፅዕኖ እስከምን ድረስ ነው?
አምባሳደር ተፈራ፡– ውስጣዊ ሽኩቻ ምክንያቱ የውጭ ጣልቃ ገብነት ነው። በዓባይ ጉዳይ የተነሳ ግብፆች ለዘመናት ጣልቃ ይገባሉ። እኛ ደግሞ በተራችን ግብፅ በውስጣዊ ሽኩቻን ወደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመን የህዳሴውን ግድብ መገንባት ጀምረናል። ይህ ማለት ውስጣዊ ሽኩቻ ለውጭ ጣልቃ ገብነት ዕድል ይሰጣል ማለት ነው። በኢትዮጵያም ውስጣዊ ችግሮች በዲፕሎማሲም የሚኖረንን ግንኙነት በእጅጉ ያሻክረዋል። ስለዚህ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በአንድ አገር ዲፕሎማሲ ላይ የሚኖራቸው ሚና በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም።
የኢትዮጵያን ኃያልነት የሚያጎላ ሥራ ላይ ማተኮር አለብን። የአፍሪካ አገራት ከቀኝ ግዛት ነፃ ሲወጡ 200 ሰዎች ነፃ የትምህርት ዕድል የሰጠችው ኢትዮጵያ ናት። አገራችን በኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ሩዋንዳ እና ሶማሊያ ሠላም አስከባሪ በመላክ የሚስተካከላት የለም። የአፓርታይድ ሥርዓት እንዲገረሰስ ኒልሰን ማንዴላን ከማሰልጠን ጀምሮ ደማቅ ታሪክ የሰራች አገር ናት። ስለዚህ ከውስጣዊ ሽኩቻ መውጣትና የጎላው ታሪክ ላይ ማተኮር ይጠቅማል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍላችን ሥም አመሰግናለሁ። ተጨማሪ ሐሳብ ካልዎት ዕድሉንም መጠቀም ይችላሉ።
አምባሳደር ተፈራ፡– ብዙ ነገሮችን አንስተናል፤ አመሰግናለሁ። ‹‹50 years in life of veteran Ethiopia diplomat›› በሚል ርዕስ መፅሐፍ አሳትሜ በየትምርት በትምህርት ቤቶች ተሰራጭቷል። እኔ የምመክረው በሕይወት ዘመናችን ያሳለፍናቸውን ተሞክሮችን ለሌላው መማሪያ በሚሆን መንገድ ማስተላለፍ ቢለመድ መልካም ነው። ለአብርሆት ቤተ መጽሐፍትም በተመሳሳይ አበርክቻለሁ። አዳማ ከተማ ለሚገኝ ትምህርት ቤቶች በተመሳሳይ መጽሐፍትን በአባዱላ ገመዳ በኩል ለግሻለሁ። ለዚህ ዘመን ወጣት እና ትውልድ መጽሐፍ አስፈላጊ ነው። እያንዳንዳችን መማርና ማስተማር ይጠበቅብናል። የዕውቀት ማግኛ መንገዶችን በሙሉ መጠቀምና ወደ ስልጣኔ ማማተር አለብን።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2015