የሴትነቴ ኮቴዎች አይረሱኝም…ብቻዬን የረገጠኩት የምድር ርቃን የለም። በሀሳቤ ውስጥ፣ በምኞቴ ውስጥ እናቴ አብራኝ አለች። ብቻዬን የረገጥኩት በመሰለኝ የነፍሴ ምድር ውስጥ እንኳን በማላውቀው መንገድ እናቴን ከዳናዬ ጎን አገኛታለው። ብቻዬን የኖርኩት በመሰለኝ የአፍላነት መንገዴ ላይ እንኳን እንዳላፍር ተጠንቅቃ ከጎን ስትሳብ እናቴን አገኛታለው። ብቻዬን የኖርኩት በመሰለኝ የሴትነቴ ድብቅ እኔነት ውስጥ እንኳን በየት እንደገባች ሳላውቀው እናቴን ጎኔ ቆማ አገኛታለው። ብቻዬን የሄድኩበት…ብቻዬን የተራመድኩበት የብቻ ጎዳና የለኝም። አንዳንድ ጊዜ ለማንም የማይነገር የብቻ ሴትነት ያለ ይመስለኛል። አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ጣልቃ የማይገቡበት የራስ ብቻ ሚስጢር አለ እላለው… በዛ ሁሉ ውስጠ እናቴ አለች። ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰፈራችን ልጅ ፍቅር የያዘኝ ሰሞን እናቴ ነበር ሄዳ ያናገረችልኝ። ለመጀመሪያ ቀን የክፍላችን ተማሪ የሳመኝ ጊዜ ለእናቴ ነበር ቀድሜ የነገርኳት። በእኔ ውስጥ እሷን፣ በእሷ ውስጥ እኔን ስላ በአንድ ሴትነት ውስጥ ሁለት እርጋ ነው ያኖረችኝ። ይቺ ሴት ታማ ሆስፒታል ገባች።
እናቴን ድንገተኛ ክፍል ሲያስገቧት ድጋሚ የማላገኛት ነበር የመሰለኝ። ከእሷ የባሰ ታምሜ ተዝለፈለፍኩ…መዝለፍለፌን ማንም አላየልኝም። ዶክተሩ የሆነ ነገር ጽፎ በአስቸኳይ ይሄ መድሃኒት ይገዛላት ብሎ ሲናገር የማዘዣ ወረቀቱን ከእጁ ላይ የተቀበልኩት እኔ ነበርኩ። የእናቴ መኖር ከእኔ የተሻለ የሚጠቅመው ስለሌለ ነበር ወረቀቱን ተቻኩዬ የተቀበልኩት። የእናቴን ህይወት ለመታደግ ከኔ ፈጥኖ መድሀኒቱን ገዝቶ የሚመጣ ያለ ስላልመሰለኝ ነበር ተስገብግቤ የማዘዣ ወረቀቱን የነጠኩት።
መድሀኒቱን ፍለጋ ብዙ ቦታ ዞርኩኝ…ከገባሁባቸው አራት መድሃኒት መሸጫ ፋርማሲዎች በአንዱ ውስጥ የተባለውን መድሃኒት አገኘሁት። መች ሳቅሽ ላለኝ ዛሬ ስል ይሄን ቀን አስታውሰዋለው። እጅግ ተደስቼ ወደ እናቴ ሄድኩ። እኔና እናቴ የተሰፋንበትን የእናትና የልጅነት ቁርኝት እያነሳሁና እየጣልኩ ብዙ ተጓዝኩ። እናቴ የሌለችበት ህይወት የሌለኝ ሴት ነኝ። ጠዋት ከእንቅልፌ የምነቃው በእሷ ተቀስቅሼ ነው። ህይወቴን የምትኖርልኝ እሷ ናት። በራሴ ያደረኩት አንዳች ነገር የለኝም። በራሴ አስቤ የወሰንኩት፣ ያለ እርሷ ብቻዬን ሞክሬ የቻልኩት አንዳች ነገር የለኝም። ‹እማ ስልኬ የት ነው? ‹እማ ቀዩ ፓንቴስ? ‹እማ ጡት ማሲያዣዬ የት ነው? እነኚህ እናቴን የምጠይቃቸው የዘወትር ጥያቄዎቼ ናቸው። እንዲህ ስጠይቃት ነው የኖርኩት። ‹እማ ነገ ሁለት ሰአት እንድትቀሰቅሺኝ፣ እማ ነገ ፕሮግራም አለብኝ የትኛውን ልብሴን ልልበስ? እማ ጸጉሬን ቀለም ልቀባ አስቤአለው ምን ትይኛለሽ? እንዲህ ነን…እየጠየኳት እየመለሰች…እያስቸገርኳት እየተቸገረች የምንኖር።
ስልኬንም ሆነ ሌሎች ነገሮቼን አንድም ቀን ፈልጌ አግኝቻቸው አላውቅም። ማታ ስተኛ አልጋዬ ጎን ያደረኩትን ቦርሳና ጸጉር ማሲያዣን እንኳን እሷን ነው የምጠይቀው። ሰብሳቤዬ ናት…ዝርክርክ ብዬ የምጸዳው በእሷ ነው። ተመሰቃቅዬ የምስተካከለው በእሷ ነው። ዝርክርክ ማንነቴ…ምስቅልቅል ሴትነቴ ወግ ያየው በእሷ ነው። እኔ ምኗ እንደሆንኩ አላውቅም ሳስቸግራት እንጂ አንድም ቀን ስቸገርላት ራሴን አላገኘሁትም። የዚች ሴት በህይወት መኖር ዋጋው በምን ይለካል?
ሆስፒታል ደረስኩ…ሆስፒታል ስደርስ የማውቀው የአክስቴ ድምጽ የተሰማኝ መሰለኝ። እናቴ ወደተኛችበት ድንገተኛ ክፍል ስጣደፍ የለቅሶ ድምጽ ሰማሁ። እዛህ ጋ መኖር አቆምኩ። በምን ሀይል እንደተራመዱ አላውቅም እግሮቼ እየተሳቡ ከእናቴ ክፍል አደረሱኝ…የገዛሁት መድሀኒት ከላላ እጄ ላይ አምልጦኝ ወደቀ።
በህይወቴ ተመኝቼ ያጣሁት ነገር በዚህ ቀን ለዛውም በእናቴ ሞት መጀመሩ መቼም የማልቋቋመው ሀዘን ሆኖ ታየኝ። ክፉ ነገሬ በእናቴ ህመም ጀምሮ በሞቷ መጠናቀቁ አለምን፣ እግዜርን እንድጠላቸው አደረገኝ። እንዴት እንደማስብ አላውቅም ግን አስባለው…ከእናቴ ሞት በኋላ የሚኖር ሴትነት፣ የሚያስብ አእምሮ የሚኖረኝ አይመስለኝም ነበር። በቆምኩበት አይኖቼን ወደ እናቴ ክፍል ወረወርኩ እናቴ በተኛችበት አልጋ ላይ በነጭ አቡጀዴ የተሸፈነ አንድ በድን ተመለከትኩ…ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ያየሁት የእናቴ ሴትነት ያ ነው።
ወደፊት መራመድ አልቻልኩም…ወደ ኋላ ሳፈገፍግ ይታየኛል። ወዴት እንደምሄድ አላውቅም። የሆስፒታሉን ግቢ ለቅቄ ከአስፓልቱ ስገናኝ ግን ትዝ ይለኛል። እናቴ የሌለችበት ብቻዬን የረገጥኩት የሴትነት ዳናዬ ጀመረ…
ሞት እናቴን ወስዶ የጀገነ መሰለኝ። ሞት እኔን ከእናቴ፣ እናቴንም ከእኔ አቆራርጦ አሁን ገና ጥሩ ሰራሁ ያለ መሰለኝ። ግን እንዴት አምኜ ልቀበል? በእናቴ ከመጣብኝ በእግዜር ላይ እንኳን መፈንቅለ መንግስት የማደርግ ሴት ነኝ። በእናቴ ከመጡብኝ አለምን በአንድ ሰከንድ ውስጥ ከማጥፋት የማልመለስ ሴት እንደሆንኩ አውቃለው። ግን ምንም አላመጣሁም። ውሸታም ነበርኩ ማለት ነው? በእናቴ ሞት ምንም እንዳልተፈጠረ መሆኔ አስመሳይ እንደሆንኩ እንዳስብ አደረገኝ። እናቴ ወደሌለችበት…ትዝታዋ ናፍቆቷ ወደማይደርስበት የሆነ የምድር ጥግ ገብቶ መስመጥ አምሮኛል። ግን ያ ቦታ የት ነው?
ብዙ አይነት ሞቶች መጡብኝ..እናቴን እንድከተላት ብዙ ሀሳቦች ተፈጠሩብኝ። ብን ብለሽ የሚበር መኪና ውስጥ ግቢ፣ ራሽን ሰቅለሽ ግደይ፣ መጨረሻው ከማይታይ ገደል ላይ ራሽን ወርውሪ፣ ከረጅም ፎቅ ላይ ራሽን ፈጥፍጪ የሚሉ እልፍ የሞት ስሜቶች አእምሮዬን ወረሩት። ለምን መሞት እንዳልቻልኩ አላቅም? ግን ሞቼ እናቴን ከምረሳት ኖሬ በሞቷ እየናፈኳት ብኖር የተሻለ ስለመሰለኝ ነው እላለው።
ከእናቴ ርቄ በሴትነቴ ዳና ላይ አስር አመት አስቆጠርኩ። ያሳደገኝ የዲማው ጊዮርጊስ ምስክሬ ነው በነዚያ አስር አመታት ውስጥ ሳላለቅስና ሳልንገዳገድ በጽናት የኖርኩት ሴትነት አልነበረኝም። እናቴን ለመርሳት የሄድኩበት መንገድ እናቴን እንድናፍቅ አድርጎ መከራ ሲያበላኝ ነበር።
ከአስር አመት በኋላ ወደ ትውልድ መንደሬ ተመለስኩ። ለምን እንደተመለስኩ እርግጠኛ ባልሆንም ግን መመለስ እንዳለብኝ የሚጎተጉት ስሜት በውስጤ ተፈጥሮ ነበር። የትም አልሄድኩም…ወደዛች እኔና እናቴ ወደተመላለስንባት የጉልት ገበያ አቀናሁ። እናቴ እንጨትና ከሰል፣ ሽሮና በርበሬ
የምትሸጥባትን ትንሽዬ የመንደራችንን ጉልት ማየት አምሮኛል። በዛ ሳልፍ የሚዋሃደኝ አንድ ስሜት እንዳለ አውቃለው…እዛ ቦታ አለማልቀስ አልችልም። ጠዋትና ማታ ከእናቴ ጋር እዛ ቦታ ነበርን።
ጉስቁልቁል ብዬ ሄድኩ…ግን ግን…ህልም የሚመስል ነገር አስተዋልኩ። የማየው ነገር ከሆነ መንፈስ ጋር ተዋህዶ አንድ ነፍሴን እያስጨነቃት ከመሆን ውጪ ምንም እንደማይሆን ባለሙሉ ተስፋ ነበርኩ። በማየው ነገር ተደነባብሬ ወደ ፊት ተራመድኩ። እናቴን የምትመስል አንድ ሴት ከዛሬ አስር አመት በፊት የማውቀውን አዳፋ ነጠላዋን ለብሳ በዛ ቦታ አየሁ። ከራሴ ጋር አስር ሆኜ እሟገት ነበር።
ፊቷን አየሁት…እናቴ ናት…
ምን እንደማስብ፣ ምን እንደምል ጠፋኝ? ራሴ የፈጠርኩት የናፍቆት ድራማ መሰለኝ…ግን ደግሞ አይደለም። ባለሁበት ሳልንቀሳቀስ ቆየሁ…እናቴ መሆኗን የሚያረጋግጡ ብዙ ነገሮችን አስተዋልኩ። እናቴን እንዳጣሁበት እንደዛ ቀን የደስታ መጀመሪያዬ ከዛ ቦታ በዛ ቀን ጀመረ።
ጓዟን ሸክፋ ወደ ቤቷ ስትሄድ ከኋላ ተከተልኳት። የማውቀውን የድሮ መንገዳችንን ትታ በሌላ አቅጣጫ ሄደች…አእምሮዬ ውስጥ የሆነ ሀሳብ መጣ። ቤቷን ዋሲሁን እንደነጠቃት። ዋሲሁን አባታችን ከመሞቱ በፊት የተበደረው ገንዘብ አለ እሱን ሳይከፍል ነው የሞተው ሲል የውሸት ሰነድ አርቆ ብዙ ጊዜ ሲከራከረን ነበር። ከብዙ መራመድ በኋላ የእናቴን ደሳሳ ማረፊያ አየሁት። እናቴ በአንድ መንገድ ዳር በላስቲክ በተሰራ ደሳሳ ቤት ውስጥ ነበር የምትኖረው። እግዜር ስለዛች ነፍስ አለምን አለማጥፋቱ ገረመኝ። እግዜር ስለዛች ምስኪን ሴት ሲል አለምን በንፍር ውሃ አለመጥበሱ የለም ይሆን? እንድል አደረገኝ።
እናቴን ሳቅፋት…ስስማት ዳግም እየተወለድኩ ነበር።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት 10 ቀን 2015 ዓ.ም