አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሚሰጠው አገልግሎትና ተያያዥ ተግባራት ለመሰብሰብ ካቀደው ውስጥ 24 ሚሊዮን ብር ጉድለት እንዳሳየ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ። ተቋሙ የተለያዩ ወጪዎችን ተጠቅሞ 206 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ፈሰስ ለማድረግ አቅዶ 183 ሚሊዮን ብር ፈሰስ አድርጓል።
የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ረዳት ዳይሬክተር አቶ አለምሸት መሸሻ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት፤ የውክልና፣ የኑዛዜ የማረጋገ ጫና የመሻሪያ ሰነዶች የማረጋገጥ ሥራን ጨምሮ በሌሎች ተግባራት እስከ መጋቢት
30 ቀን 2011ዓ.ም ድረስ 635 ሺ 293 ጉዳዮችን ለማስተናገድ አቅዶ 597 ሺ 587 ጉዳዮች አሳክ ቷል። ኤጀንሲው ለአንድ ሚሊዮን 361 ሺ 492 ተገልጋዮች የተለያዩ አገል ግሎቶችን ለመስጠት በማቀድ ለአንድ ሚሊዮን 90ሺ 498 ተገልጋዮች አገልግሎት ሰጥቷል። 295 ነጥብ 7 ሚሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ በዕቅድ ቢይዝም ያሳካው 271 ሚሊዮን 656 ሺ ብር ነው።
እንደ አቶ አለምሸት ገለፃ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋሙ ከመጡ ተገልጋዮች መካከል 63 ሃሰተኛ ሰነዶች ተገኝተዋል።
ከእነዚህ መካከል 45 የመታወቂያ ሰነዶች፣ 17 ያላገባ ማስረጃ እና አንድ የጉምሩክ ክሊራንስ ሲሆኑ፤ ይህም በህግ አግባብ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን አስረድተዋል። በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ አስተያየት የሰጡት ተገልጋዮች ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አዎንታዊው አስተያየት በ11ነጥብ2 ብልጫ ማሳየቱን ከተደረገው የዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን አስታውሰዋል።
እንደ አቶ አለምሸት ገለፃ፤ ተቋሙ በዘረጋው የኦንላይን አገልግሎት 142ሺ465 ጉዳዮች የተስተናገዱ ሲሆን፤ በተለያዩ ምክንያቶች በተቋሙ በአካል ተገኝተው አገልግሎት ማግኘት ላልቻሉ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ነፍሰጡሮች እና ከሆስፒታል ማስረጃ ለተጻፈላቸው ተገልጋዮች ባሉበት ስፍራ የቅድሚያ አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡
ኤጀንሲው በአገልግሎት ቅልጥፍና ብቻ ሳይወሰን ተዓማኒነት ያላቸውና ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የአሰራር ሥርዓቶችን ዘርግቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም ኤጀንሲው 15 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በፈፃሚው ሥነ ምግባርና መሻሻል በሚገባ ቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
ኤጀንሲው ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም ባለው የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመንም ስምንት ሚሊዮን 850ሺ 962 ተገልጋዮችን በማስተናጋድ ሁለት ቢሊዮን 183 ሚሊዮን ብር በላይ ለማግኘት አቅዷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር