ለአዋጭነት ጥናት 300ሺ ዩሮ ተከፍሏል
አዲስ አበባ፡- አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በዘመናዊ መልክ በመገንባት ከተማዋን የዓለም የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ መዳረሻ ለማድረግ ጥናት ቢካሄድም በእቅዱ መሠረት ግንባታ አለመጀመሩ ተገለፀ። ማዕከሉ ለመገንባት የሚያስችለውን የአዋጭነት ጥናት ለማካሄድ 300 ሺ ዩሮ ክፍያ ተፈጽሟል።
የድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት አድማሱ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጠ ያለው የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት በአዋጅ ከተቋቋመ 35 ዓመታትን አስቆጥሯል። ሆኖም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ መሠረታዊ የሚባሉ ለውጦች አልተደረገለትም። በዚህም የተነሳ ፍላጎትና አቅርቦት ሳይመጣጠን ቆይቷል።
«የመንግስትና የግል ዘርፍ ጥምረት ለዘላቂ ልማት» በሚል እሳቤ የድርጅቱ የማኔጅመንት ሥራ ከ14 ዓመት ወዲህ ሙሉ ለሙሉ ለአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት መሰጠቱን ያስታወሱት አቶ ታምራት፤ በየወቅቱ የኤግዚቢሽን ተሳታፊዎች እና አዘጋጆች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ይናገራሉ።
ለአብነትም ድርጅቱ በ2010 ዓ.ም 75 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ አግኝቷል። በ2011 ዓ.ም ደግሞ80 ሚሊዮን ብር የሚያገኝበትን ጨረታ አጠናቋል። ከ14 ዓመታት በፊት 10 አዘጋጆች ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር አድጎ በያዝነው ዓመት 150 አዘጋጆች ይገኛሉ። ለ2012 ዓ.ም ደግሞ 85 ከመቶ የሚሆነውንም ዝገባ ከወዲሁ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ
ገለፃ፤ ምንም እንኳን
አሁን ባለው ሁኔታ
ከሚያዘጋጃቸው ዝግጅቶች 90 ከመቶ
የሚሆኑት በዓለም አቀፍ
የንግድ ድርጅት መስፈርት
መሰረት ደረጃውን የጠበቁ
ቢሆንም፤ ማዕከሉ መስጠት
የሚገባውን አገልግሎት እየሰጠ
አይደለም። ፍላጎትና አቅርቦቱ
የተመጣጠነ ባለመሆኑ «የአዲስ
አበባ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን
ማዕከል» በሚል ስያሜ
በአዲስ መልክ ግንባታ
ለማካሄድ ታስቦ ከሦስት ዓመታት በፊት ስፔን ባርሴሎና በሚገኝና በዘርፉ እውቅናና ልምድ ካለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር ጥናት መደረጉን አስታውሰዋል።
አቶ ታምራት እንዳሉት፣ የማዕከሉን ግንባታ የአዋጭነት ጥናት ለማካሄድም 300ሺ ዩሮ የተከፈለ ሲሆን፤ ሥራውን ለማጠናቀቅ 10 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል። ይሁንና የማዕከሉ ግንባታ በ2011 ዓ.ም የመጀመር ውጥን ቢኖርም እስካሁን ወደ ሥራ አልተገባም። ምክንያቱ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ያለው የኤግዚቢሽን ማዕከል2ነጥብ4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በአዲስ መልክ የሚገነባው ማዕከል 10 ሄክታር መፈለጉ ነው።
በዚህም መሠረት 7 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት ተጨማሪ የሚያስፈልግ በመሆኑ የወሰን ማስከበር ሥራዎች አስቸጋሪ ሆነው መቆየታቸው ነው። በተጨማሪም የማዕከሉ ዝርዝር የዲዛይን ሥራዎች ያለመጠናቀቃቸውና በዘርፉ ላይ ልምድ ያለመኖር ለመዘግየቱ ምክንያት መሆናቸውን አብራርተዋል። ይሁንና ግንባታው በ2012 ተጀምሮ 2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ ማዕከሉን ለመገን ባት «ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ» የሚለው አሰራር በሥራ ላይ የሚውል ሲሆን ይህ ሳይሆን ከቀረ ሌሎች አማራጮች የሚተገበሩ ይሆናል፤ በርካታ አማራጮች የሚታዩበት ዕድል መኖሩንም አስገንዝበዋል። ቱርክ፣ ቻይና፣ እስራኤል፣ ስፔን እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በግንባታው ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳደራቸውንም ጠቁመዋል። ማዕከሉ የሚተዳደረው በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ስር ቢሆንም ለግንባታው የፌዴራል መንግሥትም ድርሻም ትልቅ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
10 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የታቀደው የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታ ሲጠናቀቅ በዓመት 15 እስከ 20 የሚደርሱ ዝግጅቶችን በራሱ እንደሚያዘጋጅ ታሳቢ ተደርጓል።
ከገቢው 60 ከመቶ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል። ማዕከሉ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል፣ ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ባህላዊ ይዘታቸውን የጠበቁ መዝናኛዎ ችና መሰል ግንባታዎች የሚያካትት ሲሆን፤የአየር ንብረትና አካባቢያዊ ተዛማዶም ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር