ተዘዋዋሪ ፈንዱ በወቅቱ ያለመመለሱ ጫና እየፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመደበኛ እና ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከአንድ ሚሊዮን ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ። መንግሥት የበጀተው ተዘዋዋሪ ፈንድ በወቅቱ ያለመመለሱ በሥራ ዕድል ፈጠራው ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑም ተገልጿል።
የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት መሪ ወይዘሮ አቦዘነች ነጋሽ ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመደበኛ እና ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንድ ሚሊዮን 282ሺ 991 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለአንድ ሚሊዮን 101ሺ ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል። ይህም ከእቅዱ 86 ከመቶ ተፈፃሚ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልፀዋል። በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ለ8 ነጥብ4 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊዎች በመደበኛ እና ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሥራ ዕድል ለመፍጠር ከተጣለው ግብ አኳያም
በሦስት ዓመት ተኩል ውስጥ 6 ነጥብ7 ሚሊዮን የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስገንዝበዋል።
ወይዘሮ አቦዘነች እንዳሉት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አንቀሳቃሾች 6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንዲቆጥቡ ተደርጓል። ከዘመኑና ከውዝፍ ብድር ውስጥ 3 ነጥብ2 ቢሊዮን ብር ለማስመለስ ታቅዶ፤ ከዘመኑ ብድር ሁለት ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከውዝፍ ብድር 312ነጥብ4 ሚሊዮን ብር ተመልሷል። በተጨማሪም በኤጀንሲውና ህብረት ሥራዎች ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ 102 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል።
እንደ ወይዘሮ አቦዘነች ገለጻ መንግሥት ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ 10 ቢሊዮን ብር በተዘዋዋሪ ፈንድ በጅቶ ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ጋር የተቀናጀ ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል። ይሁንና አንዳንድ ክልሎች ወደ ሥራው በስፋት ያልገቡ ሲሆን፤ ጥቂት ክልሎች ደግሞ በተዘዋዋሪ ፈንድ ለወጣቶች ያበደሩትን ገንዘብ በወቅቱ ለመሰብሰብ አልቻሉም። ይህም ለሌሎች ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ላይ
እክል እየፈጠረ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአመራሮች ቁርጠኝነት ማነስ፣ ተቋሙ በበቂ በጀት ተመድቦለት አለመንቀሳቀሱ፣ የፕሮሞሽን ሥራዎች በሰፊው አለመከናወናቸውና ሌሎችም ጉዳዮች ተጨማሪ ችግሮች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እቅድ ሲወጣ 900 ከተሞች ታሳቢ ተደርገው የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የከተሞቹ ቁጥር ወደ 1ሺ በማደጉ ሥራውን በተፈለገው ልክ ስኬታማ አለመሆኑን ጠቁመዋል። ከኤጀንሲው በተገኘው መረጃ መሰረት፤ በአሁኑ ወቅት በከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ከተካተቱ 11 ከተሞች በተጨማሪ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት 72 ከተሞች በመርሐ ግብሩ የሚካተቱ ይሆናል።
የፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 374/2008 በአዲስ መልክ መቋቋሙ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር