አዲስ አበባ፡- የእምቦጭ አረምን ጨምሮ ከቆሻሻ ነዳጅ ማምረት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የአቶ አበሻ ዳርጌ የፈጠራ ሥራ የሆነውን ከቆሻሻ ነዳጅ የማምረት ፕሮጀክትን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሠራ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የፈጠራ ሥራው እምቦጭና የፕላስቲክ ቆሻሻን ጨምሮ ከሚወገድ ማንኛውም ቆሻሻ ነጭ ጋዝ፣ ቤንዚን፣ ናፍታ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ እና ሚቴን ማምረት የሚያስችል ነው ተብሏል ፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ከሚገኘው ተረፈ ምርት ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ፣ ማለስለሻ ግሪስ፣ ሻማ፣ የጫማ ቀለምና ሌሎችንም መሥራት ያስችላል፡፡
የነዳጅ ምርቱን በፍጥነት ለመጀመር ለነዳጅ ማምረት ሂደት የሚጠቅም ያልተወሳሰበ ማሽን ለመሥራት የሚችል የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
ከኬሚካልና መካኒካል ኢንጂነሪንግ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተውጣጣው ይህ ቡድን ለነዳጅ ማምረቻ የሚያገለግል የማሽን ዲዛይን ሠርቶ ካቀረበ በኋላ፤ ወደ ማሽን ምርት ተገብቶ በየከተሞቹ ነዳጅ ማምረት የሚያስችል አቅም
ለመፍጠር ይሠራል፡፡ ምርቱ ጥራት እንዲኖረው ለማድረግም በዘርፉ የተሻለ እውቀት ያላቸውን ሰዎች በማሳተፍ የሚሠራ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጀማል በከር ኢትዮጵያ ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ ለማስቀረትና ለመንግሥት ፈተና የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል በተቻለ ፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የፈጠራ ባለቤት አቶ አበሻ ዳርጌ በበኩላቸው፤ ምርምሩን ከ10 ዓመት በፊት ጀምረው ሲሠሩ እንደቆዩና በተለያዩ የመንግሥት አካላት ጫና ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻሉ ገልጸዋል። የፈጠራ ባለሙያው የካርበን ልቀትን እስከ 95 በመቶ መቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጅም እንዳላቸው ነው የተናገሩት።
የእንቦጭ አረምን ወደ ነዳጅነት መቀየር ካልሆነም ብዝሃ ህይወቱ ሳይጎዳ እዚያው ባለበት ማጥፋት የሚያስችል የፈጠራ ሥራም እንዳላቸውም አቶ አበሻ ዳርጌ ተናግረዋል ሲል ፋና ብሮድካስቲን ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2011