የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በበኩሉ ችግሩ በቅርቡ ይፈታል ብሏል በጀሞና አካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ከረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ የሚወጣው ከፍተኛ ድምጽ እየረበሻቸው መሆኑን ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ሰሞኑን ዳግመኛ ሥራ የጀመረውን የቆሻሻ ኃይል ማመንጫን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው የሚሰማው ከፍተኛ ድምጽ እንቅልፍ እየነሳቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በጀሞ አንድ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከሚገኙ ነዋሪዎች መሀል አቶመንግስት አለነ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤የኃይል ማመንጫው ማሽን ለዋና መንገዱ የቀረበና ከመኖሪያ ቤቶቹ እምብዛም ያልራቀ መሆኑን ነዋሪው በድምጹ ብክለት እንዲታወክ ምክንያት ሆኗል።
እንደ አቶ መንግስት አገላለጽ የኃይል ማመንጫው ቀደም ሲል ባደረገው ሙከራና በነበረው ከፍተኛ ድምጽ ነዋሪው ሲማረር እንደነበር አስታውሰው፣ሰሞኑን ሥራ ሲጀምር ግን ማስተካከያ ይደረጋል የሚል ግምት እንደነበራቸው ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ዘውዴ በቀለ በበኩላቸው፤ በኃይል ማመንጫው ከፍተኛ ድምጽ ምሽቱን ጨምሮ ሌሊቱን በሙሉ አካባቢው ሲረብሽ እንደሚያድር ይናገራሉ። ድምጹ ያልተለመደና የማያቋርጥ መሆኑ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው የሚሉት ወይዘሮ ዘውዴ፤ በተለይ በምሽቱ ክፍለ ጊዜ ጎልቶ መሰማቱ ለእንቅልፍና እረፍት ማጣት እየዳረገ መሆኑን ይገልጻሉ።
ለድምጹ ብክለት ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል የሚለው ወጣት ማሙሸት መልኬም በአካባቢው ከተለመደው የቆሼ ሽታ በዘለለ ይህ መሰሉ አዋኪ ድምጽ መታከሉ ለአካባቢው ነዋሪዎች ተጨማሪ ፈተና እንደሚሆን ይናገራል። ምንም እንኳን የኃይል ማመንጫ ሥራውን ለማካሄድ ጅማሬ ላይ ቢሆንም በያዘው መንገድ የሚቀጥል ከሆነ ግን ለነዋሪው መረበሽ ምክንያት እንደሚሆን ስጋቱን ይናገራል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር
አቶ ሞገስ መኮንን
በበኩላቸው ነዋሪዎቹ ያነሱት
ቅሬታ እውነት
መሆኑን ይናገራሉ። ችግሩ የተከሰተው የኃይል ማመንጫው ረዘም ላለ ጊዜ ያለሥራ ከመቆሙ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ክፍተት ነው። በአሁኑ ጊዜ ሂደቱን ወደ ሥራ ለማስገባት በሚኖረው ጥረትም የቆሻሻው እንፋሎት ወደ ተርባይን እንዲገባ የሚደረግ ይሆናል። ሥራው ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት እስኪጀምርም ለተወሰነ ጊዜያት ድምጹ በዚህ መልኩ ስለሚቀጥል ሊረብሽ እንደሚችል ጠቁመዋል።
የማቃጠያ ማሽኑ ለረጅም ጊዜ ያለሥራ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ ይህ ዓይነቱ ድምጽ የሚጠበቅ ይሆናል ያሉት አቶ ሞገስ ይሁን እንጂ እንደነዋሪዎቹ ስጋት ድምጹ ለዘለቄታው የሚቀጥል ሳይሆን በጣም አጭር ለሚባል ጊዜ ብቻ የሚቆይ ነው።
እንደ አቶ ሞገስ ማብራሪያ፤ በአሁኑ ጊዜ ሥራውን ከሚያካሂዱት ሁለት ተርባይኖች መሀል በአንዱ ላይ ያለው ችግር ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ተወግዷል። በሁለተኛውም ላይ የሚጠበቀው እንፋሎት ገብቶ ተርባይኖቹ እስኪሞቁ ድረስ ችግሩ የሚዘልቅ ቢሆንም ከዚህ በኋላ ድምጹ ለአካባቢው ስጋት ሆኖ እንደማይዘልቅ ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ብቸኛ የሆነው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ሥራ መጀመሩንም አቶ ሞገስ አክለው ገልጸዋል።
በአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ ብክለት ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሉብርሀን ታሪኩ እንደሚናገሩት፤ የድምጽ ብክለት የሰው ልጆችንና አካባቢን የሚረብሽ፣ ያልተፈለገና በጤናማ አኗኗር ላይ ሁከት የሚያስከትል ችግር ነው። የድምጽ ብክለቱ ከተገቢው በላይ ሆኖ ከተገኘም ሰላማዊ ህይወትን ከማናጋት ጀምሮ የማሰብ ችሎታን በመቀነስ በነርቭና በዓይን፣በልብና በሆድ ዕቃ አካላት ላይ ጉዳት የማስከተል ኃይል አለው።
የጆሮ ታንቡርን እስከመቅደድ የሚደርሰው ከፍተኛ ድምጽ መጠኑ እስከ አንድመቶ ሀምሳ እንደሚደርስ የሚናገሩት ዳይሬክተሯ፤ ቅሬታ የተነሳበትን የረጲ የኃይል ማመንጫ የድምጽ ደረጃ ለማወቅ ልኬት ሊደረግለት እንደሚገባና ብክለቱ ከኢንዱስትሪዎች በሚወጣ የድምጽ መጠን መስፈርት መታየት እንዳለበት ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ በህግ በተቀመጠው የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 300/1995 መሰረት የድምጽ ብክለት ለሰው ልጆች ጤንነት ጎጂ ከሚባሉት መሀል መፈረጁንም ወይዘሮ ሙሉብርሀን አክለው ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2011
በመልካምስራ አፈወርቅ