በ1985 ዓ.ም በጥርና በየካቲት ወራት እንዲሁም በ1956 በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለንባብ የበቁ ዘገባዎችን ዛሬ ለትውስታ ያህል መራርጠን እንመለከታለን። ሮይተርስን ምንጭ በማድረግ የተሰራ አንድ አስገራሚ ዘገባ ‹‹በንቦች የተነደፈ ሰው ሞተ ይለናል። ምን አድርጎ? እንዴት ሞተ? የሚለውን ዝርዝር እንድታነቡት እንጋብዛለን። ሠፋሪዎች የእርሻ በሬ አገኙ። ነጋዴዎቹ ሱቅ አገኙ። በገለብ ሐመር አካባቢ ፖሊሶች ፀጥታ ከማስጠበቅ አልፈው ለነዋሪዎቹ እርሻ እያስተማሩ አስደሳች ጥቅም አስገኝተዋል የሚሉን ሌሎች ዘገባዎችንም እንደሚከተለው ለንባብ ጋብዘናል።
አንድ ሺህ ጊዜ የተነደፈው ሞተ
ዛፎችን በመከርከም ላይ እንዳለ ከአንድ ሺህ ጊዜ በላይ በንቦች የተነደፈው የአውስትራሊያ ማዘጋጃ ቤት አንድ ሠራተኛ ሞተ።
ዳረን ፕሪየር የተባለው የ25 ዓመት ሰው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት አንድ የንብ ቀፎ በቀሰቀሰበት ወቅት በአንድ ተንጠልጣይ ወለል ( መሰላል) ላይ ሆኖ ዛፎችን በመከርከም ላይ ነበር። የንቦቹ ጥቃት ለማስቀረት ሲሉ ሰውዬውን ወደ መዋኛ ገንዳ ውስጥ ወርውረው ሲከቱት የዐይን ምሥክሮች እንዳሉት ከሆነ ግለሰቡ ሙሉ በሙሉ በንቦች ተሸፍኖ ነበር።
ሮይተርስ ( የካቲት 7 ቀን 1985 ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ሠፋሪዎች የእርሻ በሬዎች አገኙ
ጎባ፤ (ኢ-ዜ-አ) በባሌ ዞን በሐረዋ ዘጠኝ በጃሚ ሠፈራ መንደር ለሚገኙ ሦስት መቶ ስልሳ ሁለት አባወራ ሠፋሪ ገበሬዎች የእርሻ በሬዎች ባለፈው እሁድ ታደላቸው።
የእርሻ በሬዎች እደላ ያስፈለገው በሐረዋ ከነበሩት ዘጠኝ የሠፈራ መንደሮች መካከል የስምንቱ መንደር ገበሬዎች ደርግ በተደመሰሰበት ወቅት በተፈጠረው አለመረጋጋት ያላቸውን ንብረትና ቤት ሸጠው ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ሲሔዱ የጃሚ ሠፈራ መንደር ሠፋሪዎች ግን መንደራቸውን ለቀው ባለመሔድ መንደራቸውን ከዘራፊዎችና ከወንበዴዎች ተከላክለው ለመቆየት በመቻላቸውና በወቅቱ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት የደረሰባቸውን ችግር ለማቃለል እንዲቻል ነው።
ሦስት መቶ ስልሳ ሁለት በሬዎችን በ ፪፻፲፯ ሺህ ብር ገዝቶ ለሠፋሪ ገበሬዎች በነፍስ ወከፍ ያደለው የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን (እማማኮ) ነው። በዕደላው ወቅት ለእያንዳንዱ ገበሬ በትክክል መድረሱን የሚያረጋግጥ ደረሰኝ ከሠፈራ መንደሩ ሊቀመንበር ከአቶ ታደለ አስፋው የተረከቡት አቶ ተስፋዬ ለታ የባሌ ዞን እማማኮ ተወካይ ናቸው።
አቶ ኃይለማርያም ሁንዴ የባሌ ዞን እርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን የግብርና ቴክኖሎጂ ኃላፊ ማብራሪያ ከዋናው መሥሪያ ቤት አንድ ቡድን ሠፈራው ድረስ ሔዶ ችግራቸውን ካጠና በኋላ የእርሻ በሬዎች መግዛታቸውን ጠቅሰው፤በሬዎቹ ከዞኑ እማማኮ ፤ከግብርና ከገበሬው የተውጣጡ አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በክልሉ ባሉ የወረዳ ገበሬዎች በመዘዋወር ተገዝተው ለማከፋፈል መቻሉን ገልጠዋል። (ጥር 1ቀን 1985 ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
ነጋዴዎች ሱቅ አገኙ
አዲስ አበባ ፤(ኢ-ዜ-አ) በመርካቶ አካባቢ ጆንያ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ፲፱፻፹ ሱቅ ለተቃጠለባቸው ግለሰቦች መንግሥት ከአንድ ሚሊዮን ተኩል በላይ ያሠራው ሱቅ የክልል ፲፬ ምክር ቤት ባፈው ማክሰኞ በእጣ አከፋፈለ። ሱቅ የተቃጠለባቸው ግለሰቦች ከአምስት ዓመት በላይ ቦታ ሳይሰጣቸው የቆዩ ከመሆኑም በላይ ለእነሱ ተብሎ የተሠራው ሱቅ ከዓመት በፊት የተጠናቀቀ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያች በመጓተቱ መንግሥት የሚያገኘው ገቢ እንደቀረና ሰዎቹ እንደ ተጉላሉ ተገልጧል።
የሱቆቹ ክፍፍል የተደረገው የክልል ፲፬ የኢኮኖሚ አገልግሎት ዘርፍ የባለሱቆችን አቤቱታ ትኩረት በመሥጠት ከባለጉዳዮች ጋራ ከሰባት ጊዜ በላይ በመሰብሰብ የተቃጠለባቸውን ሰዎች በማጣራት ለዘጠና ነጋዴዎች ደርሰዋል። ነጋዴዎቹ በሰጡት አስተያየት ራሳቸው ያቋቋሟቸው ኮሚቴዎችም ሆኑ ያለፈው አስተዳደር በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳዩን ሲያጓትቱት ቢቆዩም የክልል ፲፬ አስተዳደር ፍትሐዊ በሆነ አሠራር ችግራቸውን መፍታቱ ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጠዋል። (ጥር 10 ቀን 19 85 ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
የፖሊሶች እርሻ
በገለብና ሐመር ባኮ አውራጃ የሚገኙ ፖሊሶች ከፀጥታ ጥበቃቸው ጋር ሕዝቡን ስለ እርሻ ጥቅም ያስተምራሉ። ከዚህ ቀደም ባሳዩት የእርሻ አዝመራ አስደሳች የጤፍ ምርት አግኝተዋል። ባለፈው ዓመትም እርሻቸውን በጥራጥሬ ዘር ሞክረውታል ። መሬቱም ፍጹም ድንግል በመሆኑ ፤አስደሳች የሆነውን ምርት አግኝተዋል።
ሕዝቡም የፖሊሶቹን አርአያ በመከተል የእርሻን ሥራ እንደሚያስፋፋና የራሱን ኑሮ እንደሚያሻሽል ፖሊሶች ተስፋ ያደርጋሉ ። (መስከረም 6 ቀን 1956 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም