የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን ለለውጥ መርተው አታግለዋል፡፡ ብርቱዎች ናቸው፤ የለውጥ ሃሳባቸውንም የሚከተለው ብዙ ነው፤ በየክልሎቻቸው መርተው ለውጥ ያመጡት እኚህ መሪዎች በአዲስ ኃላፊነት ወደ ፌዴራል መጥተዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት በልዩ ተሸላሚ በጎ ሰው ተብለዋል፤ አቶ ለማ መገርሳ። ከአነጋገራቸው ብስለትና ጥልቀት እንዲሁም የመንግሥት ፖሊሲዎችን ከመደበኛ የትረካ ስልት በተለየ መንገድ ማቅረባቸው፤ አልፎም ከተናጋሪነት ይልቅ አድማጭ በመሆናቸው ለዚህ መብቃታቸውን ሽልማቱ ያዘጋጀው ዓመታዊ መጽሔት ያትታል። ምዕራብ ወለጋ ዞን ያፈራቻቸው እኚህ ሰው፤ ከትላንት በስቲያ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ለማ ወደ ከፍተኛ አመራርነት የመጡት ኢትዮጵያ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበትና አጣብቂኝ በበዛበት ጊዜ ነው። በጊዜው የነበረውን ስጋትም ወደ ፍጹም ተስፋ እንዲሸጋገር ካስቻሉ ሰዎች መካከል ግንባር ቀደም ናቸው።
ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ በነበሩት ጊዜያት አቅማቸውን እና ለአገራቸው የመሰጠታቸውን ልክ በቅርብ ከሚያውቋቸው ሰዎች ውጪ ብዙዎች አያውቋቸውም ነበር። ኦዴፓ /ኦህዴድ/ን ከተቀላቀሉ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ የተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ በታማኝነት ያገለገሉ ሰው ናቸው።
በመንግሥት መዋቅር የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የኦሮሚያ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ የኦሮሚያ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ የጨፌ ኦሮሚያ ም/ቤት አፈ-ጉባዔ ሆነው አገልግለዋል። በተሰጣቸውና በሚረከቡት የኃላፊነት ደረጃ ሁሉ ችግሮችን የሚጋፈጡ፤ ለውድቀት የማይንበረከኩ፣ ንግግር አዋቂ፣ ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫ መቃኘት የሚችሉ ሆነው ተገኝተዋል። ይህንንም ጥንካሬና ስኬታቸውን ተከትሎ በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ የቀድሞው ኦህዴድ የአሁኑ ኦዴፓ ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾመዋል።
ከአንድ ዓመት ወዲህ ባለው የለውጥ ሂደት ውስጥ፤ አቶ ለማ ድርሻቸው ብዙና ጉልህ ነው። በስልጣን ላይ ያላቸው አቋም የጸና ነው። ስልጣን ከሕዝብ አይበልጥም፤ አይነጻጸርም። ይህንንም
በተግባርም አሳይተዋል። «ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው» በሚለው ንግግራቸውም ተጽእኖ መፍጠር ችለዋል። በለውጡ መጀመሪያ በኦሮሚያ ክልል ጉዳዮች ላይ የፌዴራል ፖሊስ ጣልቃ እንዳይገባ በማለት ባቀረቡት ጥሪ፤ በክልሉ ይደረጉ የነበሩ ተደጋጋሚ ሰልፎችን ለመቆጣጠር በሚል ያለ አግባብ ሲደረግ የነበረውን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ማስቆም ችለዋል።
ደንብንና መመሪያን ያልተከተሉ እንዲሁም ለክልሉ በማይጠቅሙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ እርምጃ ወስደዋል። «የፓለቲካ ባህላችን የታመመ ነው። እያፈረሰን ያለው ይህ የፖለቲካ ባህላችን ነው። በመካከላችን ያለው ጥላቻና መጠፋፋት፣ አንዳችን በሌላችን ላይ የምናደርገው ዘመቻ መቆም አለበት…» የሚሉት አቶ ለማ፤ በተሰጣቸው ልክ የሠሩት ሥራና ያሳዩት ጥረት ስለገዘፈ ከክልል ርዕሰ መስተዳደርነት ወደ ፌዴራል መንግሥት ስልጣን ከፍ ብለዋል። ከቀደመውም ይልቅ አሁን ላይ የበለጠውን ኃላፊነትም ተቀብለዋል።
በተመሳሳይ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቀድሞው ብአዴን በአሁኑ አዴፓ ሊቀመንበር ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው በቅርቡ ነበር ስልጣናቸውን ለዶክተር አምባቸው መኮንን ያስረከቡት። ላመኑበት ሟች፤ ደፋር ሰው መሆናቸውን በተለያየ ጊዜ በተግባር አሳይተዋል። አቶ ገዱ ሙስናን የሚጠየፉና አመዛዛኝ ትጉህ መሪ መሆናቸውንም ከተግባራቸው በመነሳት ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል።
ከ 1982 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ከወረዳ እስከ ክልል አመራርነት አገልግለዋል። ከጥቅምት 2003 ዓ.ም በርዕሰ መስተዳደርነት እስከ ተሾሙበት ዕለት ድረስ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል።
በዚህ ወቅት ባላቸው ኃላፊነት መሰረት በክልሉ የሰብል ምርታማነት እንዲያድግ፤ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ እንዲስፋፋ፤ ግብርናው አስተማማኝ መሰረት ይዞ እንዲዘልቅ የተሻሻሉ አሠራሮችና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አርሶአደሩ የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ትራኮማን ለመከላከልና ለመቀነስ በተደረገ ጥረት በአማራ ክልል ጥሩ ስኬት እንዲመዘገብ የአመራርነት ሚናቸውን ተወጥተዋል፤ ይህም የአመራሩና ህዝብ ድርሻ ትልቅ ነው በማለት የላይንስ ክለብ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ሸልሟቸዋል።
አቶ ገዱ ከዓመት በፊት ለጀመረውና በኢትዮጵያ ለተገኘው ለውጥና ሂደቱ፤ ባበረከቱት ጉልህ ድርሻ በመላው ኢትዮጵያን ተመስግነዋል። ከሀገር ውጭም ባሉ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እና ተሰሚነት ከፍ ብሏል። አሁን ላይም አገራቸውን በውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ የበለጠውን ኃላፊነት ተቀብለዋል።
እነዚህ ሁለት ከክልል ወደ ፌዴራል መንግሥት የቀረቡ ባለስልጣናት እንደተባለው ከቀድሞው የላቀ ብዙ ኃላፊነት አሁን ተጥሎባቸዋል። ለስኬት መሪ ብቻ ሳይሆን የተመሪም አስተዋጽኦ አስፈላጊ ነውና፤ ድሉን ብቻ ሳይሆን ችግርና ተግዳሮታቸውንም መጋራትን ይጠይቃል። እናም ያለፈው እንዲያ ከሆነ፤ አሁንም የሆነው ሆኖ እነዚህ አዳዲስ አመራሮች ነገ ላይ ፍሬያማ የሚሆኑበት፤ ለአገራቸውም እንደቃላቸውና ተስፋ እንደተጣለባቸው የተሻለውን ለውጥ የሚያመጡበት ጊዜ እንዲሆን እንመኛለን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2011
በሊዲያ ተስፋዬ