የግጥምና ዜማን ቀመር እሱ ብቻ ያገኛት እስኪመስል ድረስ ከሁለት ሺህ በላይ የሙዚቃ ግጥምና ዜማዎች ላይ አሻራውን አሳርፏል። በወርቃማው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመን ከብዙዎቹ እውቅና ተወዳጅ ድምጻዊያን ዘመን ተሻጋሪ ውብ ዘፈኖች ጀርባ እሱ ነበረ። ይህ የዜማ ሊቅ ማነው? ቢባል የሁሉም ሰው መልስ አበበ መለሰ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ከ800 በላይ ዜማዎች፣ ከ250 በላይ ግጥሞች፣ ከ400 በላይ ቅንብሮች (አሬንጅመንት) በመስራት ከ27 ታላላቅና ተወዳጅ ድምፃውያን ጀርባ ምሰሶ ነው። የኢትዮጵያ የሙዚቃው አብዮት በተጋጋለበት በ1970ዎቹ አበበ መለሰ ያሳረፈው አሻራና የተጫወተው ሚና በእጅጉ የላቀ ነው።
የተንጣለለው የጣና ሀይቅ እምብርት በሆነችው ውቧና ለምለሟ ባህር ዳር ከተማ የተወለደው አበበ መለሰ ገና በልጅነቱ እኩዮቹ ከጣና ሀይቅ አሳን እያሰገሩ በመንጠቆ ሲይዙ እሱ ከታላቋ የቅኔ ሀይቅ ውስጥ ግጥምና ዜማን በማስገር አንድ ሁለት እያለ የሙዚቃን መረብ መሙላት ጀመረ። ልጅ ሆኖ በሚመለከታቸው ቲያትርና ፊልሞች ውስጥ የሚገኙ ሙዚቃዎችም በጓሮ በኩል እጁን ይዘው ወደ ሙዚቃው የጥበብ አውድማ ወስደውታል። የሙዚቃ ፍቅሩም ከፍ እያለ ሲመጣ የራሱን ትንሽ ጊታር አዘጋጅቶ በቀጫጭን ጣቶቹ እየገረፈ ዜማና ግጥም ማፍለቅ ጀመረ።
አበበ መለሰ በ1970ዎቹና 80ዎቹ በተደመጡ ሙዚቃዎች በአብዛኞቹ ውስጥ ማለት በሚቻል ደረጃ የእርሱ ስም አርፎባቸዋል። የዚያ ዘመን ገናና ድምጻዊያን ስማቸው እንደ መብረቅ እየተተኮሰ የዝና ማማ ላይ እንዲወጡ ያደረጓቸውን ሙዚቃዎች ያበጁት የዚህ ባለቅኔ እጆች ናቸው። ከሁለት ሺህ በላይ የዜማ፣ ግጥምና ቅንብር ስራዎች ውስጥ የጥበብ መዳፋን ያሳረፈው ይህ ብርቱ የጥበብ ሰው ለበርካታ ከዋክብት ድምፃውያን ነጥሮ መውጣት ምክንያት ነው።
እሱ የጥበብ አሻራውን ካሳረፈባቸው የምን ጊዜም እውቅ ድምጻዊያን መካከል የሙዚቃ ንጉሱ ጥላሁን ገሰሰ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ሂሩት በቀለ፣ አስቴር አወቀ፣ ቴዎድሮስ ታደስ፣ ንዋይ ደበበ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ ነጻነት መለሰ፣ ሐመልማል አባተ፣ ኤሊያስ ተባበል፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ አረጋሃኝ ወራሽ፣ ኬኔዲ መንገሻ እና ሌሎችም ዛሬ ላይ አንጋፋ የተሰኙ ከያኒዎች ይጠቀሳሉ። እነዚህ በሙዚቃ ስራዎቻቸው እንደ ተራራ የገዘፈ ስም ያተረፉ ድምፃውያን የገነነ ዝና ላይ ለመውጣት የአበበ መለሰን የቅኔ ማዕድ ተቋድሰዋል።
ከእነዚህ መካከልም የአንዳንዶቹ ድምፃውያን ከግማሽ በላይ በሆኑ አልበሞች ውስጥ የዜማና ግጥም አባት ሆኖ የሚገኘው አበበ መለሰ ነው። እሱ ግጥምና ዜማውን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን የሙዚቃ አብዮተኞችንም ጭምር ወልዷል ማለት ይቻላል። ከእነርሱ ጋር ያገናኘው ስራው ቢሆንም ከሰዎች ጋር በነበረው ጥሩ ግንኙነት ከበርካቶቹ ድምጻዊያን ጋር ከስራ ያለፈ ጓደኝነትም መመስረት ችሏል።
አብዛኛውን ጊዜ ጠለቅ ያለ የሙዚቃ እውቀትን ያዳበሩ ሰዎች ካልሆኑ በቀር አንድን ሙዚቃ አድምጠን ሙሉ አድናቆትና እውቅናን ለድምጻዊው በመስጠት ጀምረን በድምጻዊው እንዘጋለን። ከመጀመሪያው ሂደት ጀምሮ ተጨንቀውና ተጠበው አምጠው የወለዱትን የዜማና ግጥሙን ባለቤቶች እንረሳቸዋለን። ድምጻዊውን እየሸለምን እንኳን አናስታውሳቸውም። መቼም ያለአባት ወይም ያለ እናት የሚወለድ ልጅ የለምና ሁለቱም ወሳኝና መሰረታዊ ናቸው።
ትናንትም፣ ዛሬም፣ ወደፊትም እንደ አዲስ የሚደመጡ ውብ ሙዚቃዎች በዚያን ዘመን ሲፈጠሩ አበበ ብቻውን አልነበረም። አንደኛው ግጥሙን ሌላኛው ደግሞ ዜማውን በመስራት ሁለት ሆነው እንደ አንድ በመዋሃዳቸው የትኛው የማን እንደሆነ መለየት እስኪያዳግት ድረስ ከአበበ ጋር በጋራ ይሰራ የነበረው ቀኝ እጁ ይልማ ገብረአብ መሆኑን እራሱ አበበ ይናገራል። ሁለቱም በጥምረት እርፍና ሞፈር ሆነው ሳይነጣጠሉ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ማሳ ከጫፍ እስከ ጫፍ ቆፍረው እንቁ አዝመራ አብቅለውበታል።
በሁሉም ቦታዎች ላይ አበበ ካለ ይልማ ይኖራል፣ ይልማ ካለ ደግሞ አበበ የማይቀር ነው። በአንድነትና ህብረት ተራራውን ንዶ፣ ኮረብታውን ፈንቅሎ ተአምርን መስራት እንደሚቻል ያሳዩ የጥበብ አርበኞች ናቸው። አበበ መለሰ ለዚህ ስኬት የበቃበትን ትልቅ ሚስጥር አይዘነጋውም። ስለራሱ ተጠይቆ እንኳን ይልማ ገብረአብን ሳይጠቅስ አያልፍም።
አበበ መለሰ እና ይልማ ገብረአብ በጋራ ከሰሯቸው ሙዚቃዎች መካከል አንደኛው የአስናቀች ወርቁ ‘እንደኢየሩሳሌም’ የሚለው ሙዚቃ ነው።
“የገብርኤል መንገድ ጎዳናው መንታ ነው
አንድም በግንፍሌ አንድም በግቢ ነው
ትመጣ እንደሆን ናና… ናና በመልካሙ
በገብርኤል በኩል በደጀ ሰላሙ”
ይህ ሙዚቃ በወቅቱ ለነበረው የደርግ መንግስት የተጻፈ ቅኔ አዘል ዜማዊ ደብዳቤ ነበርና ሙዚቃውን የሰማ አንድ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣን በቁጣ በግኖና በንዴት ገንፍሎ ሙዚቃውን የሰሩትን ሰዎች እንዲያመጡለት አዘዘ። አበበና ይልማም በደርግ ወታደር ተጎትተው ተወሰዱ። ከግቢው ደርሰው ባለስልጣኑም እነዚህን ሁለት ልጆች በሚመለከት ጊዜ ያልጠበቀውና ለአይን የማይሞሉ ገና ልጆች ሆነው አገኛቸው። በነገሩ የተገረመው ባለስልጣንም ሁለቱንም ወጣቶች በአርጬሜ ገርፎ ወደመጡበት ሸኛቸው።
በሌላ ጊዜ ደግሞ የደርግ መንግስት በሀገራዊ ወከባ ውስጥ ሳለ ‘ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!’ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ። በአርጬሜው ግርፊያ ያልተደናገጡት ሁለቱ ጓደኛሞች ግን ከትዝታ ንጉሱ ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ ተስረቅራቂ ድምፅ ጋር ግጥምና ዜማቸውን አዋደው እንዲህ የሚል ሙዚቃ ሰሩ
“ለሰው ልጆች ፍቅር
ለሰው ልጆች ሰላም
ለሰው ልጆች በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ሰላም ይሁን ምድሩ ሁሉ
ሰላም…ሰላም…ሰላም
በዓለም ዙሪያ ሁሉ
ለሰው ዘር በሙሉ”
እንደገና ተጠርተው ሄዱ። በዚህኛው ዙር ግን በቀጭን አርጩሜ ብቻ አልታለፉም ነበር ትንሽ ቆንጠጥ ተደርገው ሙዚቃውም እንዲታገድና በህዝብ ጆሮ እንዳይገባ ተደረገ። ይህ በሆነ በትንሽ ጊዜያት ውስጥ ደግሞ የተገላቢጦሽ ነገር ተከሰተ። መቼስ የማይቆም የለምና ጦርነቱ በእርቅ ተቋጭቶ ሙዚቃውም ከፍ ተደርጎ እንዲደመጥ ተደረገ። ሙዚቃው ዛሬም ድረስ ብሔራዊ የሰላም መዝሙር እስኪመስል ድረስ ሰላምን በተራብንና በተጠማን ቁጥር ሰላም…ሰላም..ሰላም እያልን እናዜመዋለን። ግጥሙ ከአንደበታችን፣ ዜማውም ከልባችን የማይፋቅ ሆኖ ታትሟልና።
አበበ መለሰ በጋራም በግልም እየሆነ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ቃና ደህና አድርጎ ቀምሞታል። ጊዜው እየሄደ መንግስታት ተለዋውጠው ዘመናትን ቢያስቆጥሩም ለየትኛውም ዘመንና ትውልድ የሚሆኑ አንጀት አርስ የሙዚቃ ስጦታዎችን አበርክቶልናል። ስራዎቹ ደግሞ እየቆዩ በሄዱ ቁጥር እንደ ወይን የሚጣፍጡ ናቸው።
የሚገርመው ደግሞ በሙዚቃ ውሃ ልክ ለክቶና በላብራቶሪ መሳሪያ ቀምሞ ያዘጋጃቸው እስኪመስሉ ድረስ ከድምጻዊያኑ የድምጽ ቀለም ጋር ልክክ ብለው እንዲሄዱ የማድረግ እንዲሁም ዜማውን በሚመቻቸው መልኩ የመቅረጽ ልዩ ችሎታ ያለው ጥበበኛ መሆኑ ነው። እሱ በሰራላቸው ግጥምና ዜማ በርካቶቹ ድምፃውያን በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ስምና ዝናቸው ገኖ ምን ጊዜም የማይረሱ ሆነዋል።
ግጥምና ዜማ ከሰጣቸው ድምጻዊያንና ከሰራቸው ስራዎች መካከል ጥቂቱን ለማንሳት ያህል ለክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ከሰራቸው በርካታ ግጥምና ዜማዎች አንደኛው ዛሬም እንደ አዲስ የሚደመጠው ሳይጠቀስ አይታለፍም።
“በባይተዋር ጎጆ፣ በባይተዋር አልጋ
እንግዲህ ለሊቱ፣ ዋ! እንዴት ይንጋ” ሌላው ደግሞ ‘ኢትዮጵያ’ የሚለው ሀገራዊ ፍቅርና ስሜት የሚቀሰቅሰው ግሩም ሙዚቃ ነው። የዚህን ሙዚቃ በሳልና ጠጣር ግጥም ስሜት እንዲፈነቅል አድርጋ ያዘጋጀችው ሌላኛዋ የጥበብ ፈርጥ ዓለምፀሐይ ወዳጆ ናት። አበበ መለሰ ደግሞ ውብ ዜማ አበጅቶለት ነብስ የዘራበት ሰው ነው።
አበበ ለሌላኛው የቅርብ ወዳጁ ድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽ በበርካታ የአልበም ስራዎች ውስጥ አሻራውን ያሳረፈ ሲሆን
“ሸጊዬ እንዳልሰበስበው
ሸጊዬ እንዳልገዛው ቀልቤን
አለሜ እኔ አላበጀሁትም
አለሜ አልሰራሁት ልቤን” የሚለው ሙዚቃ ይገኝበታል።
“የአገር ቤቷ አይናማ፣ አንቺ ለግላጋ
አንቺ የገጠር መለሎ፣ የገጠር ሎጋ
ልቤን ሆዴን ሰወርሽው፣ ሳይመሽ ሳይነጋ”
ለተወዳጁና አንጋፋው ማህሙድ አህመድ ከሰጣቸው ስራዎች እጅግ በጣም ተወዳጁ ሆኖ ዛሬም ይደመጣል።
“ድማም ጎኔ አንቺ ድማም ጎኔ
መጥተሽ አነጋግሪኝ ታምሜአለሁ እኔ” እያለ ደግሞ ለሙሉቀን መለሰ ከሽኖ ያቀረበለት ምርጥ ስራ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል።
በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ሁለት ሺህ የሚደርሱ የዜማ፣ የግጥም እና ሙዚቃ ቅንብር ስራዎችን ሰርቶ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ የማይረሳ አሻራውን ማሳረፍ የቻለውና አበበ እነዚህን ዘመን የማይሽራቸው ሙዚቃዎችን አምጦ ሲወልድ ሁሉ ነገሩን ለጥበብ ሰጥቶ ማህበራዊ ሕይወቱን ጭምር ሰውቶ ነው። ሌትና ቀኑ መሽቶ ሲነጋ እንኳን የማያውቅበት ጊዜ እንደነበረም የሙያ ጓደኞቹ ይመሰክራሉ። አበበ መለሰ የጥላሁንን ‘ኢትዮጵያ’ ከሰራ በኋላ ከስራ ጫና የተነሳ ሁለቱም ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጭ በመሆናቸው ለሕይወቱ የሚያሰጋ ደረጃ ደርሶ ነበር። በዚህም ምክንያት ስራ እንዳይሰራ በሀኪም ትዕዛዝ ከሙዚቃ ለረዥም ጊዜ ተገሏል።
በዚህ ችግር ውስጥ ሕይወቱ ከሞት ጋር ተፋጣ በነበረችበት ወቅት ግን ጥበብ በክፉ ቀን ውለታውን መልሳለታለች። የሕይወቱ ብርሃን ዳግም የምትፈነጥቅበትን እድል ስራዎቹን አብዝቶ የሚወድለት አንድ አድናቂው “እሱ ቆሞ ይሄድ ዘንድ ኩላሊቴን እኔ እሰጠዋለሁ” አለ። የማይታመን ነበር፣ በአካል እንኳን አይቶት ለማያውቀው ሰው በደስታ ኩላሊቱን እንዲሰጥ ያደረገው ወጣት ለጥበብና ለጥበበኛው አካሉን ቆርጦ እንዲሰጥ አደረገው። ኢትዮጵያዊነት ይህ ነው፤ ያለምንም መስፈርት መተዛዘን፣ አንዱ ለሌላው መኖር። አበበ መለሰም ከህመሙ አገግሞ ዳግም ቆሞ ለመራመድ የበቃ በዚህ ነው።
አበበ በወርቃማው የኢትዮጵያ የሙዚቃ አብዮት ውስጥ ጉልህ ሚና መጫወት የቻለ ባለቅኔ ቢሆንም፤ የሰራውን ያህል እውቅና ሳያገኝ ቆይቶ በ2009 ዓ.ም ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማግኘት ችሏል። ኑሮውን በእስራኤል አገር ካደረገም የሰነባበተ ሲሆን በሕይወት ዘመኑ ለሙዚቃ ላበረከተው ትልቅ አስተዋጽኦ ከቀድሞ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ እጅ ሽልማት ተቀብሏል።
በስራዎቹ ደከመኝና ሰለቸኝ የማያውቀውና በዜማ ባህር ውስጥ እየዋኘ ውሎ የሚያድረው አበበ መለሰ በቅርቡ አንድ ትልቅ ስራ ለመስራት በዝግጅት ላይ ነው። በወርቃማው ዘመን ዜማና ግጥም ከሰራላቸው ክዋክብት ድምጻዊያን መካከል አንደኛው ተወዳጁ ኬኔዲ መንገሻ ሲሆን የራሱ የአበበ መለሰ የሆኑትን የዚህን ድምጻዊ ስራዎች በዳግም ቅንብር ሊሰራ እንደሆነ ገልጿል። የተመራረጡት እነዚህ ስራዎቹም በድምፃዊ እንዳለ አባተ ተዚመው በቅርቡ ወደ አድማጭ ጆሮ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2015