ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት ደግሞ ከ105 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 4 ቀን 1910 ዓ.ም የእቴጌ ጣይቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ነው።
‹‹ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ›› በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት እቴጌ ጣይቱ ከአባታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም እና ከእናታቸው ወይዘሮ የውብዳር ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም በጌምድር ውስጥ ደብረታቦር ከተማ ተወለዱ።
ወደ ፖለቲካዊ ታሪካቸው እንሂድና፤ የፋሲካ ዕለት ሚያዝያ 25 ቀን 1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ከአጼ ምኒልክ ጋር ቅዱስ ቁርባን ተቀብለው ተጋቡ። ንጉሡ ‹‹አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› የሚለውን ስም በተቀዳጁ በማግሥቱ ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ.ም ወይዘሮ ጣይቱ ብጡል እቴጌ ተብለው ተሰየሙ።
ከእቴጌ ጣይቱ የፖለቲካ ተሳትፎዎች ጎልቶ የሚታየው፤ ኢትዮጵያ ሚያዝያ 25 ቀን 1981 ዓ.ም በውጫሌ ላይ ከኢጣሊያ ጋር በተፈራረመችው ውል ውስጥ በኢጣሊያንኛው ትርጉም ሀገሪቷን ነፃነት እንደሌላት ጥገኛ በማስመሰል ዓላማ ላይ የተመረኮዘ ውንብድና መኖሩ ሲታወቅ በተናገሩት ነው።
የጣሊያንን ሴራ ከተረዱ በኋላ «እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ሆኖም ይህን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ» የሚል አቋማቸው በታሪክ ሰነድ በደማቁ ተጽፏል።
እቴጌ ጣይቱ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች መረጋጋት የሚያረጋግጥ የሀገር ግንባታ ተግባሮች በማከናወን ረገድና የአዲስ አበባ ከተማ መቆርቆር በእቴጌ ጣይቱ ከተጠናቀቁት የግንባታ ተግባሮች አንዱ ነው። ከሚታወሱባቸው አንዱ ደግሞ ፒያሳ ያለው ጣይቱ ሆቴል ነው።
በልጅ እያሱ አስተዳደር ዘመን እቴጌ ጣይቱ ከቤተ መንግሥት ተወግደው በግዞት ላይ ለአንድ ዓመት በላይ እንደተቀመጡ ይነገራል። ሆኖም ታማኝ አሽከሮቻቸውና መላው ሠራዊት የእቴጌነታቸውን ልዕልና አላጐደለባቸውም። መሳፍንቱ መኳንንቱና ወይዛዝርቱም ቢሆኑ ተገቢውን አክብሮት ሳይነፍጓቸው ዕለት በዕለት ይጠይቋቸው ነበር።
የልጅ እያሱ ሥልጣን ብዙም ሳይቆይ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም የሚኒስትሮች ካቢኔ ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥተ ነገሥታት ተብለው መንግሥቱን በመምራት እንዲተኳቸው መደረጉ ለእቴጌ ጣይቱ ታላቅ ድል ሆነ። በመሆኑም የእቴጌም የእስራት ቀንበር ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ሊወድቅላቸው ቻለ። ንግሥት ዘውዲቱ ሥልጣናቸው ተዳክሞ ትዕዛዛቸው እንዳይዛባ በማለት ከተጓዙበት ከእንጦጦ ሳይቀር ምክር መለገሳቸውን አላቋረጡም ነበር።
እቴጌ ጣይቱ የደረሰባቸውን ፈተና ሁሉ በትዕግስት ተቀብለው ጥቂት እፎይ ካሉ በኋላ ከአፄ ምኒልክ ጐን ሆነው የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ ለማረጋገጥ ሲታገሉ ያለፉት ዘመን ከዕለታት አንድ ቀን ትዝ ስላላቸው ከሰገነት ላይ ብቅ ብለው «ያ ቤት የትኛው ነው?» ብለው ሲጠይቁ ከደንገጡሮቹ አንዷ «የእመቤቴ እልፍኝ ግምጃ ቤት ነበር» አለች። እሳቸውም ትንሽ ተከዝ ብለው ከቆዩ በኋላ ቀበል በማድረግ «ነበር ለካስ እንዲህ ቅርብ ኖሯል» አሉ ይባላል። ይህም እንደ አባባል ሆኖ ይነገርላቸዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም