ቱሪዝም ምጣኔ ሀብትን ከሚያነቃቁና የአገር ገፅታን ከሚገነቡ ጠንካራ ኢንዱስትሪዎች መካከል የሚመደብ ዘርፍ ነው። አገራት ያላቸውን የመስህብ ሀብት በመለየት፣ በማልማት፣ በመጠበቅና በማስተዋወቅ የእድገታቸው መሰረትና የጀርባ አጥንት እንዲሆን ተግተው ይሰራሉ። በውጤቱም ጠንካራ ምጣኔ ሀብትና መልካም ገፅታን የገነባች አገርን ይመሰርታሉ። ከዚህ አኳያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚገኝበት እንደመሆኑም “ጭስ አልባ” ኢንዱስትሪ ተብሎ ይጠራል።
ቱሪዝም ከተፈጥሮ፣ ቅርስ፣ ባህል፣ ታሪክ አርኪዮሎጂካል ሀብትና ሌሎች አይነተ ብዙ ጉዳዮች ጋር በቀጥታ ይያያዛል። እነዚህን አጣምረው የያዙና ልዩ ትኩረት የሰጡ አገራት የጥረታቸውንና የልፋታቸውን ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ አግኝተውታል። ለእዚህም የዓለም የቱሪዝም መዳረሻ የሚባሉትን ፓሪስ፣ ጣሊያን፣ ግብፅን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
የቱሪዝም አይነቶች ብዙ ናቸው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ቱሪዝም የሀገር ውስጥ ቱሪዝም፣ ዓለም አቀፍ ቱሪዝም በመባል ይከፈላል፡፡ ሌሎች አይነተ ብዙ የቱሪዝም ንኡስ ክፍሎችም አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በዓለማችን ላይ ተወዳጅና በጎብኚዎች ተመራጭ እየሆነ የመጣው የፌስቲቫል ቱሪዝም (ትእይንተ ቱሪዝም) አንዱ ነው። አሁን አሁን “ፌስቲቫል ቱሪዝም” ባህልን፣ እምነትን፣ ታሪክን፣ጀግንነትን ማህበራዊ ትስስርንና አብሮነትን በአንድ ቦታና ስፍራ ማግኘት የሚቻልበት በመሆኑ ጎብኚዎች ይህንን ለመመልከትና ከቀሪው ዓለም ጋር ትስስር ለመፍጠር ይመርጡታል። በተለይ እነርሱ ፍፁም ካልለመዱትና ከማያውቁት ባህላዊ ልምምድ (Exotic culture) ጋር የሚያገናኛቸው እንደመሆኑ “የፌስቲቫል” ቱሪዝምን ተወዳጅና ተመራጭ ያደርገዋል።
በዓለማችን ላይ ተወዳጅ ከሆኑት የፌስቲቫል ቱሪዝም አይነቶች መካከል የብራዚል (ሳምባ/ ዳንስና ትርኢት፣ የስፔን የሰንጋ ፍልሚያ፣ በጀርመን የቢራ ፌስቲቫል፣ በሜክሲኮና በአንዳንድ የላቲን አሜሪካ አገራት ደግሞ የሞቱ ወዳጅ ዘመዶች የሚዘከሩበት ትእይንት ይጠቀሳሉ። በእነዚህና ሌሎች በርካታ ተወዳጅ የአለማችን ምርጥ ፌስቲቫሎች ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ይገኛሉ። አገራቱም በዚህ የቱሪዝም አይነት ገፅታቸውን ከመገንባታቸውና ሀብታቸውን ከማስተዋወቃቸው ባሻገር ከጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ረብጣ ገንዘብን ያፍሳሉ።
“ፌስቲቫል ቱሪዝም – ጽንሰ-ሐሳብ፣ ዋና ተግባሮች እና ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ተግባራት” በሚል ርእስ የፌስቲቫል ቱሪዝም ላይ ዘለግ ያለ ጥናታዊ ፅሁፍ የሰራው ቶማስ ዞውኪ የተባለ ምሁር የቱሪዝም ዘርፈ ብዙ የመስህብ ሃብቶችን በአንድ ላይ ጠቅልሎ ለጎብኚዎች ማስቃኘት የሚችለው “የፌስቲቫል ቱሪዝም” ተመራጭ እየሆነ የመጣ ንዑስ ክፍል እንደሆነ ጠቅሶ አገራት አዋጪ በሆነው ኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል በማለት ምክረ ሃሳቡን ይሰጣል።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ አያሌ የመስህብ ሀብት ያላት ነች። በተለይ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው በርካታ ፌስቲቫሎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ይካሄዳሉ። በመስከረም የመስቀል ደመራ፣ በጥር የጥምቀት በአላት ይከበራሉ፤ በነሐሴ የደብረ ታቦር በዓል በደብረ ታቦር አካባቢ በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ በድምቀት ይከበራል፤ በዚህም የእምነቱን ስርአት ከማድመቅ ባሻገር ባህላዊና ትውፊታዊ መስህቦች ይከወናሉ፤ በሐረር የሚካሄደው የሻዋሊን በዓል (በሙስሊሙ ማህበረሰብ)፣ በኦሮሞ ብሔር ዘንድ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል (የኦሮሞ ገዳ ስርዓት የሚታይበት)፣ በሲዳማ ህዝብ የሚከበረው ፍቼ ጫምባላላ፣ በዋላይታ የሚከበረው ጊፋታ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚከበሩት ሻደይ አሸንድዬና ሶለልን ጨምሮ እጅግ በርካታ በአደባባይ ላይ እንደሚከበሩ ይታወቃል፤ ኢትዮጵያ የእነዚህ ሁሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ፌስቲቫሎች መገኛ ነች።
ይሁን እንጂ እነዚህን ሀብቶች በአገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት በማስተዋወቅ፣ በመጠበቅ፣ በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንዳልተቻለ መናገር ይቻላል። የዘርፉ ምሁራን እምቅ ሀብት ያለውን የፌስቲቫል ቱሪዝም ወደ ምጣኔ ሀብት አቅም ለመቀየር መስራት እንደሚገባ በተደጋጋሚ ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
ከፌስቲቫል ቱሪዝም እና በኢትዮጵያ ከሚከበሩ ተወዳጅ የአደባባይ በዓላት መካከል የአገው ፈረሰኞች ማህበር በየዓመቱ ላለፉት 83 ዓመታት የሚያዘጋጀው ፌስቲቫል ይጠቀሳል፤ የጌዴኦ ብሔረሰብ የአዲስ ዓመት መለወጫ የሆነው “ደራሮ” ሌላው ፌስቲቫል ቱሪዝም ነው። እነዚህን ትልቅ አቅምና ባህላዊ ሀብትን የያዙ ክብረ በዓላት ባሳለፍነው የጥር ወር ውስጥ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ድምቀት አላብሰው አልፈዋል። ከዚህም ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ተጨማሪ ገፀ በረከት በመሆን ተጨማሪ አቅም መፍጠር የሚችሉ ናቸው። የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንም ለእነዚህ ባህላዊ ሀብቶች እውቅና በመስጠት በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ እየሰራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአገው ፈረሰኞች
የአዊ ዞን ብሔረሰብ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ለይኩን ሲሳይ የአገው ፈረሰኞች በየዓመቱ በተለየ ሁኔታ በቅኔ መወድስ፣ በጃኖ ባህላዊ አለባበስና በፋሽን ትርኢት፣ በሩጫ ውድድር፣ በሙዚቃ ፌስቲቫል፣ በቁንጅና ውድድርና በጎዳና ላይ የፈረስ ትርኢት እስከ ዋዜማ ድረስ በድምቀት እንደሚከበር ተናግረው፣ በባህላዊ ምግብ ዝግጅትና ጉብኝት፣ በፈረስ ሸርጥና ፈረስ ጉግስ፣ በሽምጥ ግልቢያና ስግሪያ ውድድሮች በድምቀት ተከብሮ የሚጠናቀቅ የብሔረሰቡ ልዩ ሀብት እንደሆነ ይናገራሉ።
በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የአገው ፈረሰኞች ማህበር ጎብኚዎችን ቀልብ እየሳበ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ዘርፉን እያነቃቃ መምጣቱን በመግለፅም፤ በተለይ በዓሉን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ይገልፃሉ። ለዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ በዓሉ በቅርስነት ተመዝግቦ ከብሔራዊ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የምስክር ወረቀት ቀደም ብሎ እንዲያገኝ መደረጉንም ያስረዳሉ።
በዓሉ “በድምቀት መከበር ከጀመረበት ከዛሬ ስድስት ዓመት ወዲህ የእንጅባራ ከተማ የጎብኚዎች ቀልብ በመሳብ ኢኮኖሚዋ እየተነቃቃ መጥቷል” የሚሉት አቶ ለይኩን፤ የፌስቲቫል ቱሪዝምና የማህበረሰቡን ቱባ ታሪክ ባህልና ልዩ ልዩ ሀብቶችን ጠብቆ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቦ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አለቃ ጥላዬ አየነው የአገው ፈረሰኞች ማህበር ሊቀ መንበር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በጣሊያን ወረራ ወቅት በፈረስ ተዋግተው ድል ያደረጉና የተሰው ጀግኖች አርበኞችን ለመዘከር ነው ማህበሩ በ1932 ዓ.ም የተመሰረተው። በወቅቱ ከ30 በማይበልጡ አባላት ማህበሩ የተመሰረተ ሲሆን፣ በተደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረትም አሁን ላይ የአባላቱን ቁጥር 62 ሺህ 221 ማድረስ ተችሏል፡፡
በቀጣይም በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለው ጥረት እንዲሳካ የአባላቱን ቁጥር ወደ 150 ሺህ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹እኛም አባቶቻችን ያስረከቡንን ባህል በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማስተዋወቅ ባለፈ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ በማድረግ ሀገራችንንና አካባቢያችንን ለመጥቀም ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። በእንጅባራ ከተማ በሚከበረው ዓመታዊ የፈረሰኞች ማህበር በዓል የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጌዴኦ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል – ደራሮ
በኢትዮጵያ ለፌስቲቫል ቱሪዝም ትልቅ መነቃቃትን ከሚፈጥሩና አቅም ካላቸው በዓላት መካከል በጌዴኦ ማህበረሰብ በየዓመቱ በልዩ ድምቀት የሚከበረው ደራሮ አንዱ ነው። ይህ የብሔረሰቡ የአዲስ ዘመን መለወጫ አብሳሪ ፌስቲቫል የብሔረሰቡን ቱባ ባህል፣ እምነት፣ እውቀት የመልከዓ ምድር አጠባበቅና ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት እጅግ በርካታ ህዝብ አደባባይ በመውጣት የሚያሳይበት ነው። በቅርቡም የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድርና አጠቃላይ የማህበረሰቡን እሴቶች በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከጫፍ እንደተደረሰ የዝግጅት ክፍላችን ቀደም ባሉት እትሞቹ ማውጣቱ ይታወቃል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ እንደሚናገሩት፤ የደራሮ አዲስ ዓመት ጌዴኦ ቀዬ መንደሩን ሰላም ላደረገ፣ አዝመራና ሰብሉን ከተምች ለጠበቀ፣ ህዝቡንና ምድሩን ከመዓትና እርግማን ለታደገ “ማጌኖ” ወይም ፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት ቀን ነው። ለአባ ጋዳ ጉማታ ወይም ሰጦታ የሚሰናዳበት በጋራ የሚከበር የምስጋናና የስጦታ በዓል ጭምር ነው።
በጌዴኦ ብሔር ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የምስጋና የስጦታ በዓል ደራሮ በስፖርታዊ ውድድሮች፣በቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶቸ ባህላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ በዲላ ከተማ በድምቀት የሚከበር ልዩ የአደባባይ ፌስቲቫል ክብረ በዓል ነው። ከምንም በላይ ባህላዊ እሴቶች ለዘላቂ ሰላምና አንድነት ካላቸው የላቀ አስተዋጽኦ ባሻገር ቱሪስቶችን በመሳብ ባህልን አስተዋውቆ ምጣኔ ሃብትን ለማሳደግ የማይተካ ሚና መጫወት ይችላል።
በአደባባይ ላይ በልዩ የጉማታና ሶንጎ ባህላዊ ስርዓት ተከብሮ ከሚውለው ባህላዊ ፌስቲቫል ባለቤትነቱ ባሻገር የጌዴኦ ብሔረሰብ በርካታ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርስ ባለቤት ነው። ጎብኚዎች ይህንን ፌስቲቫል ለመመልከት ወደ ስፍራው ሲሄዱ እግረ መንገዳቸውን መልከዓ ምድሩ በውስጡ የያዘውን ጥብቅ ደን፣ ጥምር ግብርናና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ በምስራቅ አፍሪካ በእድሜ ረጅም እንደሆኑ የተነገረላቸው ከ6000 በላይ የትክል ድንጋዮችን እንዲሁም የሙዚቃ፣ የአመጋገብና ሌሎች መስህቦችን መጎብኘት ይችላሉ። ቅርሱን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንሰና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከጫፍ መድረሱም የፌስቲቫል ቱሪዝምን በጌዴኦ አካባቢ ለማስፋፋትና ጎብኚዎች ወደዚያ እንዲያቀኑ ለማስቻል ልዩ እድል ይፈጥራል።
የደራሮ በዓል ባሳለፍነው ጥር ወር በደማቅ ፌስቲቫልና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሮ አልፏል። በተለይ የዘንድሮው በዓል ከስምንት ዓመታት በኋላ ዲሞክራሲያዊ የአባ ገዳ መሪዎች የስልጣን ሽግግር የተደረገበት፣ የዞኑ ልዩ ጣእም ያለው የቡና ፌስቲቫል የተካሄደበትም ነበር። በመግቢያችን ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው እንደ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ብራዚል የመሳሰሉ አገራት ቱሪስቶችን ለመሳብና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለመገንባት ያላቸውን ሀብቶች ለዓለም ህዝብ ያስተዋውቃሉ። ይህንን ስልት ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ደራሮን የመሰሉ ተወዳጅ ባህሎች ለዓለም እንዲተዋወቁ መስራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
እንደ መውጫ
የኢትዮጵያ መንግሥት ቱሪዝም የምጣኔ ሀብት ምሰሶ ከሆኑት አምስት ዘርፎች መካከል አንዱ እንደሆን መደረጉን ይፋ አድርጎ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሰራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። አገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ እምቅ ሀብትና በርካታ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና የአርኪዎሎጂ መስህብ ሀብቶችን የታደለች መሆኗም እሙን ነው። ከዚህ ውስጥ ሃይማኖትን እንዲሁም ባህልን መሰረት ያደረጉ የማይዳሰሱ ሀብቶች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ የቱሪዝም ሀብቶች በተለይ በዓለም ዙሪያ ተመራጭ የሆነውን የፌስቲቫል ቱሪዝም የሚፈልገውን ይዘት ያሟሉ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው በተለይ በጥር ወር በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት ተከብረው የሚያልፉበት እንደመሆኑ መጠን ከአንድ ስፍራ ወደ አንድ ስፍራ የሚደረገው ጉዞና ከዚያም የሚገኘው ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በተለይ ከውጭ አገራት ከሚመጡ ቱሪስቶች፣ ትውልደ ኢትዮጵያኖችና የውጭ አገራት ዜጎች በተለየ መንገድ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች መጠን በእጅጉ ከፍተኛ ነው። ይህንን አቅም ይበልጥ በማጎልበት የጥምቀት፣ መስቀል፣ ኢሬቻ፣ ፊቼ ጫምባላላ እንዲሁም በዛሬው የባህልና ቱሪዝም አምድ ላይ በስፋት የዳሰስናቸው የአገው ፈረሰኞች ፌስቲቫልና የደራሮ የአዲስ ዘመን መለወጫ ክብረ በዓላት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ በመስራት ማህበረሰቡንና አገርን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል እንላለን። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም