የዛሬ የዘመን እንግዳችን አቶ መኮንን እሳቱ ሚካኤል ይባላሉ። አቶ መኮንን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ በነበሩበት ወቅት ብሔራዊ ውትድርና ዘመቻን በመሸሽ፤ ወደ ኬኒያ ተሰደዱ። ከኬኒያ ወደ እንግሊዝ ሀገር በመሄድ የቋንቋና የቢዝነስ ትምህርት ተከታተሉ። በመቀጠል እዛው በእንግሊዝ ሀገር የጋዜጠኝነት ትምህርትን ከተከታተሉ በኋላ፤ ቢቢሲ ትሬኒንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት የሚባል ቡድን ከተማሪዎቹ ውስጥ ለማሰልጠን ሶስት ልጆች ሲመለመሉ አቶ መኮንን አንዱ ሆነው ይመረጣሉ። በዛም አጭር የጋዜጠኝነት ቴክኖሎጂ ሙያ ትምህርት ወሰዱ። በመቀጠል በአፍሪካ እስተዲ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ።
በቢቢሲ ለአስራ አራት ዓመት፤ የቤን ቴሌቪዥን በሚባል የአፍሪካ ቴሌቪዥን ውስጥ ለአምስት አመታት፤ አፍሪካን ስፔክተር የሚባል የሬዲዮ ፕሮግራምን በመምራት ለ3 አመታት ሰርተዋል። በዶክመንተሪ ፊልሞችና በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ለሰለሳ ዓመታት የስራ ልምድ ካላቸው አቶ መኮንን ጋር እንዲህ አውግተናል። መልካም ቆይታ፡-
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ በጋዜጠኝነት ሙያ ያሳለፉትን የሕይወት ልምድ ቢያካፍሉን?
አቶ መኮንን፡- ከልምዴ በፊት ጋዜጠኛ ምን መሆን አለበት? የሚለውን ላብራራ። ጋዜጠኝነት ከሃይማኖት ከፖለቲካና ከሌሎች ወገንተኝነት የፀዳ መሆን ይኖርበታል። ጋዜጠኛ እራሱን ከአድሎ አፅድቶ ለሚያገለገለው ማህበረሰብ ታማኝ መሆን አለበት። የጋዜጠኝነት መመሪያዎች መርህ ሆኖ እድሜ ልኬን አብሮኝ እንዲኖር የሆነው እንግሊዝ ሀገር ባገኘሁት የስራ ልምድና ትምህርት ነው።
ይሄን ስል እኔ ለበርካታ አመታት ያገለገልኩበት ቢቢሲ የመጨረሻ ነፃና ገለልተኛ ነው ማለት አይደለም። ይህ ሲባል ለሚፈለጉት አካል ወገንተኞች መሆናቸው፤ በሀገራዊ ጥቅማቸው የማይደራደሩ መሆናቸው፤ ከፖለቲካ አስተሳሰባቸው ጋር ለሚቃረኑ ነገሮች ቦታ የሌላቸው መሆናቸው የሚካድ አይደለም። ቢቢሲ የእንግሊዝ መንግስት አፍ ማለት ነው። ሁሉም ሀገር በዚህ ደረጃ ሀገሩን የሚጠብቅ ጠንካራ መገናኛ ብዙሃን ያስፈልገዋል።
በዚህ ሁሉ ውስጥ የጋዜጠኝነት አኗኗርን የጋዜጠኝነት ቁመናን በተገቢው እንዲኖረኝና ተቋሙን እንዳገለግል ተቃኝቻለሁ። ከቢቢሲ ቆይታዬ በኋላ በርካታ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ሰርቻለሁ። በቢቢሲ አስራ አራት አመት ከሰራሁ በኋላ፤ የአፍሪካ ቴሌቪዥን ውስጥ የቤን ቴሌቪዥን ላይ ከበርካታ ኬኒያዊያን ጓደኞቼ ጋር ለአምስት አመታት ሰርቻለሁ። አፍሪካን ስፔክተር ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከተውጣጡ ጋዜጠኞች ጋር የሬዲዮ ፕሮግራም ስንሠራ የምመራው እኔ ነበርኩ። በዛም ለሶስት ዓመታት ሰርቻለሁ።
በተለያዩ የስራ ልምዶችና በወሰድኳቸው ሙያዊ ትምህርቶች ጋዜጠኛ ዜና ወደ እሱ እንዲመጣ የሚፈልግ ሳይሆን እራሱ ዜናውን ፈልጎ የሚያገኝ የአነፍናፊ ባህሪ ሊኖረው የሚገባ መሆኑን ተምሪያለሁ። ጋዜጠኛ ከቤቱ ወጥቶ ስራው እስኪደርስ ያለውን ማህበራዊ ችግሮችን የሚያይ ነው። የትም ቦታ ላይ ቢሆኑ የጋዜጠኝነት ዓይን ካለ ጋዜጠኝነት በደንብ የሚሠራ የሚወደድ ሙያ መሆኑን ባሳለፍኩት ልምድ ተመልክቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የምርመራ ጋዜጠኝነት ስንል ምን ማለታችን ነው?
አቶ መኮንን፡- የምርመራ ጋዜጠኝነት (Investigative Journalism) የምንለው ከጋዜጠኝነት ሥራ መካከል አንዱ ነው። የምርመራ አዘጋገብ በሚያካትታቸው ነጥቦች ሥልታዊ፣ ጥልቀት ያለው፣ ያልተቀዳ ጥናትና ዘገባ፣ ብዙ ጊዜ በምስጢር የተያዙ ጉዳዮችን የሚያጋልጥ የጋዜጠኝነት የሥራ ዓይነት ነው። ሥራውን የሚሰሩ ጋዜጠኞች ተግባራዊነቱ ላይ የሕዝብ የሆኑ መዝገቦችንና መረጃዎችን በከፍተኛ ደረጃ አካትተው አትኩሮታቸውን ማኅበራዊ ፍትህና ተጠያቂነት እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው ይሰራሉ።
በዩኔስኮ የታተመ ‹ስቶሪ ቤዝን-ኢንኳየሪ› የተሰኘ የምርመራ ጋዜጠኝነት መመሪያ መጽሐፍ፣ የምርመራ ዘገባን እንደሚከተለው ይተረጉመዋል። ‹‹የምርመራ ጋዜጠኝነት ኃይል ባለው ሥልጣን ሆነ ተብሎ አልያም በድንገት በእውነታዎች መደበላለቅና ለመረዳት ግልጽ ባልሆኑ ሁኔታዎች የተደበቁ ጉዳዮችን ለሕዝብ መግለጥን ያካትታል። በምስጢር የተያዙ እንዲሁም በግልጽ የሚገኙ ምንጮችንና ሰነዶችን መጠቀምንም ይጠይቃል።›› በተጓዳኝ የ‹ደች- ፍሌሚሽ› የምርመራ ጋዜጠኝነት ማኅበር (VVOJ) የምርመራ ዘገባን በቀላሉ ‹ወሳኝ እና ጥልቀት ያለው ጋዜጠኝነት› ሲልም ይተረጉመዋል።
በምርመራ ጋዜጠኝነት ከፍተኛ ሽልማቶችን ያገኙ ዘገባዎች፣ ሙያው ምን ያህል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለ ጥናታዊ ምርምርና አዘጋገብ እንደሚፈልግ ማሳያ ናቸው። እነዚህም የተዘረፈ የሕዝብ ገንዘብ፣ ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም፣ የአካባቢ ብክለት፣ የጤና ዘርፍ ላይ ያሉ አሳፋሪ ጥፋቶችንና መሰል ሌሎች ጉዳዮችን የሚከተሉ ጥልቀት ባለው መልኩ በጥንቃቄ የተሠሩ ምርመራዎች ናቸው።
በሙያው አንጋፋ የሆኑ አሠልጣኞች እንደሚሉት፣ ምርጥ የሚባል የምርመራ ጋዜጠኝነት በጥንቃቄ የተመራ፣ ከመጀመሪያ ደረጃ ምንጭ የተገኙ መረጃዎች ላይ መሠረቱን የጣለ፣ መላ ምት ያለውና ያንንም የሚፈትሽ እንዲሁም ማስረጃዎችን በተደጋጋሚ ማጣራትን የሚያካትት ነው። መዝገበ ቃላቱም ‹ምርመራ› የሚለውን ቃል ‹ሥልታዊ ምርምር› ሲል ይተረጉመዋል። ይህም በአንድ ቀን ወይም በኹለት ቀን ተሠርቶ የሚጠናቀቅ አይደለም፤ ሰፊ ጊዜን ይፈልጋል።
በእንግሊዝ ሀገር ከጋዜጠኝነት የስራ መደቦች ውስጥ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው የስራ ዘርፍ ነው። ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ለመማር ከፍተኛ ውጤት ማምጣት የግድ ነው። መገናኛ ብዙኃን አራተኛ መንግስት መሆናቸውን የተቀበሉት ሀገሮች የምርመራ ጋዜጠኝነትን በዚህ ልክ እንዲሰፋፋ እየሰሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የምርመራ ጋዜጠኝነት ከሌላው የጋዜጠኝነት በምን ይለያል?
አቶ መኮንን፡- የምርመራ ጋዜጠኝነት ጋዜጠኛው ያስብና አንድ ፕሮጀከት ይነድፋል፤ ይሄን ፕሮጀከት እንደ እራሱ ጉዳይ በመያዝ ጥናት ይሠራል። በጥናቱ ምንን ይይዛል? ምን ተፈጠረ? ማን ፈጠረው? ለምን ተፈጠረ? እንዴት ተፈጠረ? ለሚሉት ጥያቄዎች በሙሉ መልስ ይሰጣል። የምርመራ ጋዜጠኝነት ይሔ ነው።
አንድ ሰው የምርመራ ጋዜጠኝነትን ሰርቶ ማንም አያቀርብለትም፤ የሚያቀርበው ራሱ ነው። የሚፈጀው ጊዜም ከወራት እስከ አመታት ሊሆን ይችላል። ሁሉም ጋዜጠኝነት የራሱ አላማ ቢኖረውም የምርመራ ጋዜጠኝነት አንድ የትኩረት አቅጣጫ ላይ በመመሥረት የሚሠራ የጋዜጠኝነት ከፍል ነው። ጥልቅ የሆነ መረጃን የያዘ፤ ለማንም ያላዳላ የጋዜጠኝነት ዘርፍ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ካልዎት ሰፊ የጋዜጠኝነት ልምድ አኳያ የሀገራችንን የምርመራ ጋዜጠኝነት እንዴት ያዩታል?
አቶ መኮንን፡- ወደ ሀገራችን ስንመጣ ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ በቂ ትኩረት እየተሰጠው አይደለም። ሁሉም ሰው እየተነሳ ጋዜጠኛ የሚሆንበት አግባብ አለ። ማንም ሰው በሆነ ዘርፍ ዲግሪ ካለው ከየትም ተነስቶ ጋዜጠኛ መሆን ይችላል። ይህ ደግሞ እጅግ አደገኛ ነው። አንድ ጋዜጠኛ ጋዜጠኛ ከመሆኑ በፊት መታነፅ አለበት። በትምህርት የጋዜጠኝነት ስነምግባርን መያዝ አለበት። የጋዜጠኝነት ስራ ምን እንደሚፈልግ ጋዜጠኛው ከትምህርት ማግኘት አለበት።
ከእንግሊዝ ሀገር የአርትስ ቴሌቪዥን መስራች በመሆን ለመስራት መጥቼ እያለ የታዘበኩት ብቃት ያለው ሰራተኛ ማግኘት እጀግ ፈታኝ እንደሆነ ነው። ጋዜጠኞችን ለመቅጠር የቀረበውን ፈተና ማለፍ አይደለም መሞከር የከበዳቸው ልጆች ነበሩ፤ እንደ ምንም አስልጥነን ስራ ውስጥ ከገቡ በኋላም በግል የፖለቲካ አመለካከት የሚፈጥሩት ሽኩቻ ስራቸውን ይገድልባቸው ነበር።
የቴሌቪዥን ባለቤት በመሆን ገንዘብ ስላወጡ ራሳቸውን እንደ ቴሌቪዥን አስተዳዳሪ የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ሀገር ውስጥ ከመጣሁ ሁለት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ሠርቻለሁ። በቲቪ ጣቢያዎቹ በጣም የሚያሳዝን ቆይታ ነበረኝ። ይህን ስል እድሉን አግኝቼ ሀገር ውስጥ ያለውን ሚዲያ እንድተዋወቅ ላደረጉኝ ሰዎች ምስጋና ቢስ እየሆነኩ አይደለም። መንግስትም ሆነ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን አውጥተው ሙያውን ለባለሙያው መስጠት አለባቸው።
ሀገሪቱ መቀየር ያለባት በርካታ ጉዳይ አላት። የፖለቲካ ወገንተኝነቱ ከሚዲያው መውጣት አለበት። የትምህርት ካሪኩለሙም የጋዜጠኝነት ትምህርት ላይ በቂ ትኩረት መስጠት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ ጋዜጠኝነት ከተለያዩ ፈተናዎች ጋር ይነሳል፤ እርስዎ የገጠሞት ነገር ነበር? ከገጠምዎትስ እንዴት አለፉት?
አቶ መኮንን፡- እኔ ዶክመንተሪ ፊልሞችን እሰራለሁ። እዚህ ላይ ለፊልም ቀረፃ በጣም ገጠራማ የሆኑ የአፍሪካ መሬቶችን ረግጫለሁ። ከከተማ ሲወጣ ጫካ ውስጥ ሲኬድ የሚገጥሙ የተለያዩ ችግሮች ይኖራሉ። በጋዜጠኝነት ግን እንደ እድል ሆኖ ምንም አይነት ችግር ሳይገጥመኝ ሥራዬን ለዓመታት አከናውኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለንበት የሚዲያ ዘመን በሀገራችን የምርመራ ጋዜጠኝነት እየተተገበረ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ መኮንን፡- እንዳየሁት ከሆነ ከበርካታ ጋዜጠኞች ጋር ስወያይ እንደታዘብኩት በተለይም ወጣት ጋዜጠኞች ላይ መነሳሳት ይታያል። የምርመራ ጋዜጠኝነት እየተተገበረ ነው ወይ ለሚለው ጥያቄ ግን መልሴ ‹‹ አይደለም የሚል ነው።›› የምርመራ ጋዜጠኝነት ማንኛውም ጋዜጠኝነት በተቀመጠለት የስነ ምግባር ሁኔታ እየተተገበረ ነው ለማለት አልደፈርም።
የጋዜጠኝነት ትምህርት በአግባቡ ተማሪዎች ማግኘት የሚጠበቅባቸውን እውቀት መጨበጥ እንዲችሉ የሚያደርግ ትምህርት ያስፈልጋል። የምርመራ ጋዜጠኝነትም ራሱን የቻለ ኮርሰ ሆኖ ለብቻው መሰጠት ይኖርበታል። ይህም የጋዜጠኝነት ልምምዱ ከፍ እንዲል ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ትምህርትና ስራ የተለያየ መሆኑን በርካታ ጋዜጠኞች ይናገራሉ፤ ትምህርቱና ሥራው እንዲጣጣም ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
በስራ ደረጃ ግን የተለያዩ ሙከራዎች ቢኖርም በምርመራ ጋዜጠኝነት መርህ የተመራ ስራ ተስርቷል ለማለት አያስደፍርም። በአብዛኛው የሰውን ሮሮ በመስማት የሚሰሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚሰሩ ስራዎች አሉ። እውቀቱ አለ፤ ፍላጎቱ አለ፤ መንግስት የበለጠ ትኩረት ቢሰጠው ውጤታማ የሚሆን መስክ ነው።
አቶ መኮንን፡- የጋዜጠኝነት ትምህርት በራሱ በጣም ደስ የሚል ከዩኒቨርስቲ ወጥተው በተግባር እስኪገልጡት የሚቸኩሉበት አይነት ነው። ከዩኒቨርሲቲ ይዘው የወጡትን እውቀት በተግባር ለመግለፅ ከራሱ ከጋዜጠኛው የበለጠ ማንም ሀላፊነት ሊወስድ አይገባም። በተቻለ መጠን መመሪያዎችን ተከትሎ ለመስራት መጣር የጋዜጠኛው ሀላፊነት ነው።
ምንም እንኳን የተቋማቱ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ቢወስነውም ጋዜጠኛው በራሱ ጥረት ይህ እንዲቀየር ማድረግ ይገባዋል። ሀገሪቱ ውስጥም ለጋዜጠኞች ክብር መሰጠት አለበት። እንግሊዝ ሀገር ጋዜጠኛ ታወቂ ግለሰብ ነው። ከፊልም አክተሮች እኩል የሚታይ ነው። እዚህ ሀገር ግን ክብር ሲሰጠው አይታይም።
መንግስት ነፃና ገለልተኛ የሆነ የመገናኛ ብዙሃን እንዲኖሩ እድል ሊሰጥ ይገባል። ነፃና ገለልተኛ ሲባል ግን ብሄራዊ ጥቅምን ባከበረ መልኩ መሆን አለበት። ምንም እንኳን የመናገር ነፃነት ያለገደብ የሆነበት ሀገር ኖሬ ብመጣም እንኳን ለአንድ ማህበረሰብ ነፃና ገለልተኛ እሆናለሁ ተብሎ ማህበረሰብን የሚጎዳ የሀገር ሉዓላዊነትን የሚፃረር ተግባር መከናወን አለበት ብዬ አላምን።
ስለዚህ መንግስትም፤ ማህበረሰቡም፤ ጋዜጠኞችም ማህበረሰቡን በመረዳት የህዝብን ጥቅም ባስጠበቀ የሀገር ሉዓላዊነትን ያከበረ በሆነ መልኩ ነፃና ገለልተኛ፤ አድሎ የሌለበት የሚዲያ ተቋም እንዲሆን ግን የሁሉም ጥረት ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ሲናገሩ ይሰማል፤ አሁን በሀገራችን የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግር፤ በልሹ አሰራርን ለማስተካከል ይህ የጋዜጠኝነት መንገድ ሊያደርገው የሚችለው አስተዋፅኦ እንዴት ይታያል?
አቶ መኮንን፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየገነቡ ያሉት ተቋም ነው። ሀገሪቱ በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ሆና ተቋም እየሰሩ ነው። ይህ ንግግራቸው ለመገናኛ ብዙኃኑ እድገት፤ አራተኛው መንግስት የመገነባበት መንገድ እንዲኖር የሚፈለግ መሆኑን የሚያሳይ ነው። አሁን በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ተቋማት በሙሉ ከሙስና የፀዱ እንዲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየሰሩ ነው።
ሙስናን ለመዋጋት ከምርመራ ጋዜጠኝነት የበለጠ መድሃኒት አይገኝም። በሀገሪቱ ብልሹ አሰራር ውስጥ የተገኙ፤ በሙስና የተያዙ፤ ተይዘው ምን እንደደረሰባቸው ማሳየት ዳግም ሙስና እንዳይፈፀም ያደርገዋል። የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በተቀናጀ ሁኔታ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ሊሰሩ ይገባል የሚባለው ለዚህም ነው።
ነገር ግን በቂ ስልጠና ለጋዜጠኞች መሰጠት አለበት። ሙያው ጥንቃቄን የሚጠይቅ ስለሆነ ሙያተኛው ምን አይነት መንገዶችን መሄድ እንደሚኖርበት፤ በቂ ከህሎት ያለው የራሱ ቡድን ተዋቅሮ በሰርዓት መሰራት ይኖርበታል። መንግስትም ለአራተኛው መንግስት ምስረታ ማለትም ለመገናኛ ብዙኃኑ እድገት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የምርመራ ጋዜጠኝነት ለአንድ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ መሻሻል ምን አስተዋፅኦ ይኖረዋል?
አቶ መኮንን፡- ለአንድ ሀገር የምርመራ ጋዜጠኝነት እጀግ ጠቃሚ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት የሰጡበት ዋና ምክንያት ይሔ ነው። ህዝቡ የሚዲያን ጥቅም መረዳት አለበት። መንግስትም በንቃት ይህን ዘርፍ መገንባትም ሆነ መደገፉ የሀገር ስጋት የሆኑ ጉዳዮች ባሉበት እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል። የማህበረሰብ ሰንኮፍን ለመነቀስ፤ ለሀገር እድገት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን አጥርቶ ሀገር እንደ ሀገር እንዲቀጥል ለማድረግ ከምርመራ ጋዜጠኝነት የላቀ አመራጭ የለም።
በእንግሊዝ ሀገር የሚኖር የእግር ኳስ ደጋፊ አንድ ቡድን፤ የአውሮፓ ሻምፒዮንን እየተከተለ በመዞር ሁከት ይፈጥራል። ይህ ቡድን የሚያደርጋቸው ነገሮች በሀገር ገፅታ ላይ ጥላ የጣለ ኢኮኖሚውንም ባልተገባ መንገድ ያደቀቀ ነበር። አንድ ጋዜጠኛ ፑሊጋንስ እየተባሉ ከሚጠሩት ከደጋፊዎች ጋር በመቀላቀል ይህን ቡድን የሚመሩ አካላት እነማን እንደሆኑ በማጋለጥ የምርመራ ጋዜጠኝነት ምን ያህል ዋጋ ተከፍሎበት ችግሮችን እንደሚነቀሱ ለመመልከት ችለናል።
በዚህም ያንን መረጃ የሚያስተላልፈው መገናኛ ብዙኃን የተመልካች ቁጥሩን ከፍ አድርጓል። ሌላው ደግሞ ህዝብ እውነትን በመመልከት መንግስትና ህዝብ መካከል ያለውን ተአማኒነት ያረጋግጣል። ስለዚህ የሀገርን ችግሮች ለመቅረፍ ከዚህ የበለጠ አማራጭ የለም እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ጋዜጠኞች ካላቸው አቅም፣ ለሙያው ከሚሰጡት ክብርና ቁርጠኝነት ጋር ተያይዞ ሙያውን በትክክል ሊወጡት ይችላሉ ? ካልሆነስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ መኮንን፡- ለጋዜጠኝነት ትምህርት ከሚሰጠው ትኩረት አንስቶ በርካታ ችግሮች ይታዩኛል። በሀገሪቱ ትላልቅ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች የሚመደቡት እንደ ህክምና ዶክተር፤ ኢንጂነር ያሉ ትምህርቶች ላይ ነው። ደረጃ በደረጃ ሌሎቹ የትምህርት ዘርፎች ላይ ተመድበው ሲያልቁ ዝቅ ያለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ለጋዜጠኝነት የትምህርት ዘርፍ እንዲመደቡ ይደረጋል። ይህ ደግሞ ለዘርፉ ምንም አይነት ክብር እንዳልተሰጠ የሚመለከተው ነው። ሚዲያ አራተኛው መንግስት ከሆነ ዘርፍ በተገቢው መልኩ ከትምህርት ስርዓቱ ጀምሮ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
አንድ ጋዜጠኛ ጋዜጠኛ ሲሆን፤ ፖለቲከኛ ሳይሆን ጋዜጠኛ እንዲሆን መደረግ አለበት። ከአድሎ የፀዳ ጋዜጠኛ የሚሆነው በበቂ ሁኔታ ሥነ ምግባርን ተምሮ ሲወጣ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከጋዜጠኝነት ሙያ ሥነ- ምግባር አንጻር ምን ሀሳበ አልዎት?
አቶ መኮንን፡- የጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ-ምግባር ዋና ዋና መርሆዎች አሉ። አንደኛው እውነትን መፈለግ (Seeking the Truth) እውነትን መዘገብ ማለት ከትክክለኛ ምንጭ የተገኘ መረጃ ላይ የራስ ሃሳብ ሳይጨምሩ ወይም ሳይቀንሱ ማቅረብ ማለት ነው። እውነትን ለህዝብ ለማቅረብ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ድፍረትም ይጠይቃል። ጋዜጠኛ ለእውነት ሲል ዋጋ ይከፍላል። ድፍረትና ብቃት ወሳኝ መሣሪያዎች ናቸው። ጋዜጠኛው የሚያውቀውና የመረጃ ምንጮች የሚሰጡት መረጃ ባይጣጣም ከሶስተኛ ወገን አጣርቶ እውነቱን መዘገብ ያስፈልጋል፡፡
ሁለተኛው ትክክለኛነት እና ህጋዊነት ነው። ዜናው ትክክለኛ መሆን ስላለበት የዜናውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የዜና ምንጩን ማለትም የመሥሪያ ቤቱን ወይም የተቋሙን ትክክለኛ ስም፣ ዜና የሰጠውን ሰው ስም፣ የኃላፊነት ደረጃ በትክክል መዝግቦ መያዝ አለበት። ትክክለኛነቱ ከመረጃው ምንጭ እስከ መልዕክቱ ጭብጥ ያለውን ያጠቃልላል። ይሄንን መተላለፍ የሙያውን ሥነ-ምግባር እንዳለ ማክበር ይቆጠራል፡፡
ሶስተኛው ፍትሃዊነትና ሚዛናዊነት (Fairness and Balance) ፍትሃዊነት የአንድን ወገን ብቻ ማስተላለፍ ሳይሆን የሁለት ወገኖችን ሃሳብና አመለካከት ማስተላለፍ ይጠይቃል። በእኩል ዓይን ማየት ፍትሃዊነት ነው። ከቋንቋ አጠቃቀምና የፎቶግራፍ አጠቃቀምን ጨምሮ ለዜናው የተሰጠው አንቀፅ መጠንና ጊዜ ፍትሃዊነትን ያሳያል። ሚዛናዊነት ደግሞ ስለሁለቱ ወገኖች ስንዘግብ አንዱን የሚያጥላላ፤ ሌላውን የሚያወድስ፤ ወይም አንዱን ጭራቅ ሌላውን ቅዱስ አለማድረግን ይመለከታል፡፡
አራተኛው ገለልተኝነት ነው። አንዱን ወገን ለመጥቀምና ሌላውን ለመጉዳት መሥራት አይፈቀድም። ዜናና የግል አስተያየት መለያየት አለባቸው። በዜና ውስጥ የግል አስተያየትን መስጠት ፈፅሞ አይፈቀድም፤ አስተያየትን ለህዝቡ መተው ይሻላል፡፡
ሌላው ስም ማጥፋትና ትክክለኛ ያልሆነ ገጽታ (Defamation) ነው። ስም ማጥፋት የሰዎችን መልካም ስምና ዝና የሚያጎድፍ ነገር መፃፍ/ መዘገብ በሥነ- ምግባር የተከለከለ ነው። ያልሆነውን ነገር እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ስም ማጥፋት ነው። መልካም ስምንና ዝናን ማጥፋት ወንጀል ነው። ይህን መርህ ያልተማረ፣ ያላወቀ እና የማይተገብር ጋዜጠኛ ደግሞ ጋዜጠኛ ሲሆን እጅግ አደገኛ ይሆናል። በአጠቃላይ ጋዜጠኞች የጥልቅ እውቀት ባለቤት መሆን አለባቸው እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየሰሩ ነው?
አቶ መኮንን፡- ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ አንድ ሀሳብ አቅርበው ነበር። አፍሪካ የራሷ ሚዲያ ያስፈልጋታል፤ ምክንያቱም የአፍሪካን ታሪክ የውጭ የመገናኛ ብዙኃን በፈለጉት መልኩ እየተናገሩት ነው። ይህንን ሀሳብ ከሰማሁ በኋላ የአፍሪካን ሚዲያ ፕሮጀከት ይዤ መጥቻለሁ።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረትን እንደ መመስረቷ ከፊት ሆና የአፍሪካ ሚዲያን ለማቋቋም መብት ይኖራታል። ይህን በማለት ከቢቢሲ ተቃራኒ ከቆሙት ተቋማት ጋር፤ ፓይኒሰት እና ላቲኖ ፕሮዳክሽን ከሚባሉ ተቋማት ጋር ቅንጅት ካምፓኒ በማቋቋም ፕሮጀክቱን ይዤ ሀገር ውስጥ መጥቻለሁ።
አፍሪካ ካሉ ከተለያዩ መንግስታትና ከተለያዩ ታላላቅ መገናኛ ብዙኃን ጋር በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ግንኙነት እየፈጠርን እንገኛለን። ይህን ፕሮጀክት በተጨማሪ የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርና አተገባባር ላይ ትኩረት በመስጠት እየሰራሁ እገኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ውድ ጊዜዎን ሰውተው ረጅሙን የጋዜጠኝነት ልምዶን ስላካፈሉን በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት ስም የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
አቶ መኮንን፡- እኔም ሀሳብህ ይጠቅማል ብላችሁ ልታናግሩኝ ስለወደዳችሁ አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም