እለተ ቅዳሜ በወበቃማው አየር ድብትብት ብላለች። መጣ ሄድ የሚል አይናፋር ንፋስ በእሳታማዋ ጀምበር እየተገላመጠ ይመለሳል። የአርባ ስድስት አመቱ ቢሆነኝ በዳዴ የሚሄድ ልጁን ጭኑ ላይ አስቀምጦ ያጫውተዋል። በፈገግታው ውስጥ አለምን እያየ፣ በፀዓዳ ሳቁ ሐሴት እያደረገ። ምን እንደሚለው አይገባውም..ብቻ ግን ያወራዋል..ፍጹም የሆነ እውነት..ድንቅ የሆነ ነገር። የተጨበጠ እጁን ወደ አፉ እያለ፣የሚዝረከረክ ለሀጩን ወደ ጭኑ እያንጠባጠበ እንደዚህ፡፡
በረቀቀ አባታዊ ፍቅር አየው..በረቀቀ አባታዊ ስስት ወደ ደረቱ አስጠግቶ አቀፈው። በልጁ ውስጥ ብዙ እውነት ታየው.. ለዘመናት ፈልጎ ያጣውን የአባቱን እውነት በልጁ ነፍስ ውስጥ አገኘው፡፡
ደጋግሞ ሳመው..። እንደ መገበሪያ ስንዴ የሚያሳሳ ጉንጩ..ለዘላለም በንጽሕና የሚታወሱ አይኖቹ የጠፋበትን እውነት ነገሩት። አባቱ እውነቴ አንተ ነህ..ከእንግዲህ በአንተ እኖራለሁ አንተም የሚያኖርህን እውነት ፈልግ..የእውነትህን ስፍራ ድረስበት ብለውት ነበር። እውነቱን በልጁ ነፍስ ውስጥ አገኘው። አባቱ ምን ያክል ጠቢብ እንደሆኑ በደንብ የገባው ዛሬ ነው..አባት ከሆነ በኋላ። ኢትዮጵያዊነትን ያስተማሩት፣ሀገርና ታሪክን ያወረሱት አባቱ ናቸው። ፍቅርን ትህትናን ያለበሱት እሳቸው ናቸው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በልጅነት ልቡ ውስጥ ያስቀመጡት አባቱ ናቸው። የአባቱ ትሑታን ንግግሮች በሕይወቱ ሁሉ ይከተሉታል። ዛሬም በጎልማሳነት እድሜው እየተከተሉት ነው። የአባቱን እውነት ለልጆቹ ሊሰጥ ለራሱ ቃል ገባ፡፡
ጆሮውን ወደ ሳሎን ወረወረ..የእናትና ልጅ ፍቅር ተሰማው። መጠየቅ የማይሰለቸው ልጃቸው እናቱን በጥያቄ እያስጨነቀ ሲያጉተመትም.. በልጇ ጥያቄ ልቧ የወለቀ ግን ደግሞ ደስተኛ እናት ለባልና ለልጆቿ ራት ልትሠራ ምድጃው ስር አጎንብሳ ታየችው። እየተቆጣች የምትራራ፣እየተከፋች ይቅር የምትል፣ እያዘነች የምትጽናና ነፍስ ፊቱ ድቅን አለች። አባቱ ሀገር የቤተሰብ ነጸብራቅ ነው ይሉት ነበር። አንተን እንዲህ የማሳድግህ ነገ ላይ ከኔ የወረስከውን እውነት ለልጆችህ እንድትነግራቸው ነው እንዲህም ይሉት ነበር። አባቱ ብዙ እውነቱ..ብዙ እውቀቱ ናቸው። በሕይወቱ ሁሉም ቦታ ላይ አሉ። ጎልምሶ እንኳን በአባቱ እውነት ነው የሚኖረው። ከነገሩት እውነት ሁሉ ግን ‹ሀገር ነፍስ የላትም..ሀገር እኔና አንተ ነን። ሀገር የኔና የአንተ የሌላው ሰው ሰውነት ነው። ሀገር የእኔና የአንተ የሌላው ሰው የጋራ ቀለም፣ የጋራ አስተሳሰብ፣የጋራ ባሕልና እሴት ነው። ሀገር ሌላውን በመውደድ የሚገለጽ ነው። የሀገር ፍቅር በሌሎች ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ መብቀል ነው ያሉትን አይረሳውም። በዚህ እውነት ውስጥ እንዲኖርም አደራ ብለውታል። ዛሬ ለእሱ ሀገር የአባቱ አስተሳሰብ ናት። ዛሬ ለእሱ ኢትዮጵያዊነት የአባቱ የአደራ ቃል ናት። ዛሬ ለእሱ ሀገር መውደድ በሌሎች ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ መብቀል ነው። ከአባቱ ለምዶበት የሚወደውን ነገር በሀገሩ መመሰል ይወዳል። አባቱ በልጅነቱ ጭናቸው ላይ አስቀምጠውት ሀገሬ ነህ ይሉት ነበር። እሱም ዛሬ ልጁን ጭኑ ላይ አስቀምጦ ሀገሬ ነህ አለው። ያለው የገባው ይመስል ትንሹ ልጅ ሳቀ..የአባቱን ደረት በእጆቹ እየጠበጠበ ከተንስኦ የጣመ ድምጹን አሰማ። ሳቁ ሰማየ ሰማያት ደርሶ ተመለሰ፡፡
ከእናቱ ጋር ሳሎን ሲነታረክ የነበረው ልጅ ያኮረፈ ፊቱን ይዞ ወደ አባቱ መጣ። ገና ከመድረሱ..እናቱ የቤት ሥራውን ማታ ነው የምሠራልህ ስላለችው እንዳኮረፈ ነገረው፡፡
‹ይሄ እኮ የሚያስኮርፍ ነገር አይደለም…አሁን ሥራ ላይ ስለሆንኩ ማታ እሠራልሀለሁ ማለት እኮ እምቢ ማለት አይደለም። ሁሉም ነገር ጊዜ አለው..ያንን ጊዜ የመጠበቅ ትዕግስት ሊኖርህ ይገባል፡፡
‹ትዕግስት ምንድነው? ልጁ ጠየቀ፡፡
መጠበቅ..በጽናት በእምነት መጓዝ፡፡
‹ግን እኮ እማዬም ሥራዋን ትታ የኔን የቤት ሥራ መሥራት ትችላለች..
‹ትችላለች እኮ..ግን በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች አሉ። ከዘገዩ የሚጎዱ..ከረፈዱ የማይጠቅሙ የሕይወት ገጾች። እስከ ማታ በመጠበቅህ ምንም አትሆንም..በመጠበቅ ውስጥ ትዕግስትን ትማራለህ፡፡
‹እሺ አንተ ንገረኝ..
‹ምን ልንገርህ?
‹ሀገር ማለት ምንድነው?
ብዙ ሳቆች ጠይም ፊቱ ላይ እየመጡ ይሄዳሉ። ከአባቱ ተጋብቶበት ስለ ሀገር ሲሰማ ደስ ይለዋል። ግን አባቱ ከነገሩት እውነት ውጪ የሚነግረው ሌላ እውነት የለውም። የአባቱ እውነት ለሁሉ የሚበቃ እውነት ነው። ሀገርን በተመለከተ..ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ እንደ አባቱ እውነት ያለው ሰው አያውቅም። ከትላንት እስከዛሬ በተረማመደባቸው የዘመን ሀዲድ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን ከነነፍሱና ከነቀለሙ ያገኘው በአባቱ ልብ ውስጥ ነው። ያኔ ልጅ ሆኖ ኢትዮጵያ አባቱን ትመስለው ነበር። ያኔ ልጅ ሆኖ ሀገር ሲባል የአባቱ መልክና መልካም ስብዕና ነበር የሚታየው። በሕይወቱ የማይረሳውና ዛሬም ድረስ የሚያስቀው አንድ እውነት አለ..እኛ ቤት ኢትዮጵያ አለች ብሎ የክፍል ጓደኞቹን ሰብስቦ ወደ ቤት ይዞ በመሄድ ከአባቱ ጋር አስተዋውቋቸው ያውቃል፡፡
‹ንገረኛ..እየጠበኩህ እኮ ነው? የልጁ ተማጽኖ ከሀሳቡ መነጠቀው፡፡
‹በሕይወት ዘመንህ ሁሉ የሚከተልህን የአባቴን እውነት ልሰጥህ ትላንቴም በመበርበር ላይ ነበርኩ። አባቴ ለእኔ እንደሰጠኝ ሁሉ አንተም ለልጆችህ የምሰጠው እውነት ነው። ከዚህ እውነት ውስጥ አንድ ሳታጎድል አደራዬን ለልጅ ልጆችህ እንድታስተላልፍ እፈልጋለሁ። ሀገር እኔና አንተ እና ደግሞ ሌላው ሰው ነው። ሀገር የእኔና የአንተ ደግሞም የሌላው ሰው መልክ ናት። ሀገር ከዚህ ቤት ስትወጣ የምታየው እውነት፣ የምትሰማው ዜማ ነው። ሀገር የእኛና የጎረቤቶቻችን የፍቅር..የአንድነት ጠርዝ ነው። በትላንት በዛሬና በነገ መካከል የተሳለ የአብሮነት አሻራ፡፡
‹የሀገር ፍቅርስ? ትንሹ ልጅ ጠየቀ፡፡
‹የሀገር ፍቅር ሀገርን ከማወቅና ከመረዳት የሚጀምር እውቀት ነው። የሀገር ፍቅር በሀገር እውነት ውስጥ መኖር ነው..በአንተ በኔና በሌላው ነፍስ ውስጥ ሕያው ሆኖ መብቀል። በዚህ እውነት ዓለምህን ገንባ..በዚህ እውነት ቤትህን ሥራ..በዚህ እውነት ራስህን አሸንፍ፡፡
‹ለአስተማሪያችን ይሄን ከነገርኩት አስር ከአስር አገኛለሁ? ትንሹ ልጅ በመጓጓት ጠየቀ፡፡
‹ለአንድ ጊዜ ሳይሆን ለዘላለም የሚያኮራህን እውነት ነው የነገርኩህ ደግሞ የሁሉም ጥያቄ መልስ ሀገር ናት። ሀገርህን ስታውቅ ዓለምህን ታውቃለህ..የእውነት ስፍራው ይሄ ነው። በዚህ እውነት ውስጥ እንድትኖር እፈልጋለሁ። እውቀት ሁሉ፣ጥበብ ሁሉ፣ስልጣኔ ሁሉ ሀገርን ከማወቅ..ሀገርን ከመውደድ የሚጀምር ነው፡፡
ልጁ በአባቱ መልስ አስር ከአስር ሲያገኝ እያሰበ…በጓደኞቹ ፊት በኩራት ሲቆም..ሲጨበጨብለት እያሰበ ደስታ ወሰደው፡፡
‹የአባትን አደራ ለልጅ እንደመስጠት..የአባትን እውነት ለልጅ እንደመንገር..ሀገርን ለትውልድ እንደማውረስ ምን ትልቅ ስጦታ አለ? አባት እንዲህ እያሰበ ከጀንበሯ ጋር ወደ ቤቱ ገባ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም