ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በፕሬሱ ላይ ብዙ ችግሮች ነበሩ። ችግሮቹን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው በተለይ የግል ፕሬሱ ላይ ከልምድ ማነስ የሚመነጭ ሲሆን፤ ሁለተኛው የግድ ጋዜ ጣውን ወይም መጽሔቱን ለመሸጥ ሲባል መረጃዎች ሚዛናቸውን ሳይጠብቁ በተጋነነ መልኩ ለማሰራጨት ሙከራ ሲደርግ ነበር።
በዚህም የተነሳ የተወሰኑ ጋዜጠኞች መታሰር፤ መንገላታትና ፍርድ ቤት መቅረብ አጋጥሟቸው ነበር። በየትኛውም ዓለም ውስጥ ቢሆን ሆነ ተብሎ ስህተት ከተሠራ፣ ሕግ አታድርግ ያለውን ያደረገ ይቀጣል፤ የሚያከራክር ነገር የለውም። ነገር ግን በፕሬስ ነጻነት ስም የማይሆን ነገር ማድረግም በራሱ አግባብ አልነበረም። መንግሥትም ቢሆን እነዚህ የግል ፕሬሶች ተጠናክረው የተሻለ ሚዛናዊ አስተማሪና ቀስቃሽ ነገሮች እንዲያቀርቡ ድጋፍ አላደረግም።
መንግሥት በየጊዜው ሥልጠና እየሰጠ ራሳቸውን የሚያሻሽሉበትን መንገድ ቢፈጥር ጥሩ ነበር። ነገር ግን ያ አልተደረገም በተለይ እንደኛ ባለ አዳጊ አገር ውስጥ የግልና የመንግሥት በሚል ፈርጆ ማስቀመጥ ትክክል አይደለም። ምክንያቱም ሁለቱም የሚሠሩት ለህዝብ የተሻለ መረጃና እውቀት ለመስጠትናለማዝናናት ነው። ሁለቱ እርስ በርስ ሲሻኮቱ፤ ሲሰዳደቡና ሲተቻቹ ስናደምጥና ስናነብ ነበር።
አሁን እንደሚታየው አገሪቱ ስር ነቀል ለውጥ ላይ ባትሆንም የለውጥ ጎዳና እየተከተለች እንደሆነ የተለያዩ የፖለቲካ ልሂቃን ሲናገሩ እንሰማለን። አሁን ባለው ሁኔታ ሚዲያው በጭንቀት የሚሠራ አይመስለኝም። ጠቅላይ ሚስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሥልጣን ላይ በቆዩበት አንድ ዓመት ውስጥ ከሚዲያ ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ ጋዜጠኛ ታስሯል፤ ፍርድ ቤት ቀርቧል እንዲሁም ተከስሷል የሚል ነገር አልሰማሁም።
አሁን ያለው ሁኔታ ጥሩ ነው በትክክል እውነትን ይዞ ሚዛናዊነትን ጠብቆ ለህዝብ መሰራጨት ያለበት መሰረታዊ ጉዳይ ካለ አሁን ነው ጋዜጠኛው በደንብ መጠቀምና ደክሞ ታግሎ መሥራት ያለበት። አሁን ያሉት ሁኔታዎች አመቺ ጊዜ መሆኑን ያሳያሉ።
አሁን ጋዜጦችም የመንግሥት መጽሔቶችም ጥሩ ነገር ይዘው እየወጡ ነው። አንጋፋው ጋዜጣ አዲስ ዘመን ላይም ብዙ ለውጦች እያየሁበት ነው። ገዝተህ እንድታነብ ያደርግሃል፤ ነገር ግን ይበልጥ ደግሞ ሊጠናከር ይገባል። አሁን ነጻነቱ አለ። የግልም ሆነ የመንግሥት ሚዲያዎች ላይ ያለው ሙያተኛ ይህን ነጻነት በአግባቡ መጠቀም መቻል አለበት።
ነጻ ነው ተብሎ ያልተረጋገጠና በመረጃ ያልተደገፈ ነገር ይዞ መውጣት ህዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ ማድረግ ነው። በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ማናቸውንም ነገሮች ቢቻል ጋዜጠኛው ቦታው ድረስ ሄዶ እያየ ቢዘግብና ቢሠራ ብዙ ነገሮች ማስተካከል ይቻላል። መንግስት እንደድሮ ጋዜጠኛ አላስርም፤ አልገርፍም፤ ፍርድ ቤትም አላቀርብም የሚል አቋም ያለው ይመስላል።
አሁን ያለው መንግሥት ለሚዲያው የሚደረገውን ድጋፍ ሊያሻሽል ይገባል። ብዙ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎችና የግል ቴሌቪዥኖች እየተከፈቱ ነው። ይህ ማለት ግን ተመችቷቸው እየሠሩ ነው ማለት አይደለም። የሥራ ቦታ፤ ጽህፈት ቤት፣ ለሥራቸው የሚያስፈልጓቸው
ካሜራዎችና መቅረፀ ድምፆች ከቀረጥ ነጻ ሆነው መግባት አለባቸው። አለበለዚያ ሚዲያው ባለበት መንገድ ነው የሚቀጥለው። ጅምሩ ጥሩ ነው ነገር ግን ሙያተኛው ድጋፍና ሥልጠና ያስፈልገዋል።
የሚዲያ ካውንስል በአንዳንድ አገሮች ተጠሪነቱ ለፓርላማ ይሆናል። አንዳንድ አገር ላይ ደግሞ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ አካላት ይመሰርቱትና ራሱን ችሎ የሚዲያ ካውንስል ይቋቋማል።
በሚዲያ የሚለቀቅ ነገር ቅር የሚያሰኘው ግለሰብም ሆነ ተቋም «ስሜ ጠፍቷል አሊያም ያልተረጋገጠ ነገር ተጽፎብኝ ኪሳራ ላይ ወድቄያለሁ ልዳኝ» ብሎ ቅሬታውን ማቅረብ ያለበት ለሚዲያ ካውንስሉ ነው። ይህ ማለት መንግሥት ፖሊስ ጣቢያም ሆነ ፍርድ ቤት ሳይሄድ ጋዜጠኛውም ሳይንገላታ ሚዲያ ካውንስሉ የቀረበለትን አይቶ ጥፋት ሠርቷል የተባለውን ሚዲያ አስጠርቶ አነጋግሮ እንዲስተካከልና እርቅ እንዲፈጠር ያደርጋል። ስለዚህ የሚዲያ ካውንስል ያስፈልገናል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2011