የመነሻ ወግ፤
ከሁለት አሥርተ ዓመታት በፊት ይህ ጸሐፊ በአንድ የውጭ ሀገር በተገኘበት አጋጣሚ መረር ያለ ሞጋች የውስጥ ስሜት አጋጥሞት ነበር:: ያ ክስተት ያጠላው የሀዘን ድባብ ዛሬም ድረስ ደብዝዞ ሊጠፋ አልቻለም:: ሙግቱ አገርሽቶ በትዝታ ለመቆዘም ምክንያት በሆነው በዚያ ጉዳይ መነሻነት ወጋችንን መጀመሩ መልካም ሆኖ የታየኝ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ የኑሮ ዘይቤ ውስጥ ያ ስሜት የአብዛኛው ሕዝብ የዕለት ተዕለት መለያ መሆኑን በማስተዋሌ ነው:: እነሆ የገጠመኙ ትውስታ::
ጸሐፊው በተገኘበት በዚያ ሀገር ከተቀበሉት ወዳጆቹ መካከል አንደኛው ቤተሰብ ሀገር ቤት በነበሩ ጊዜ በጣሙን ይተዋወቁ ስለነበር ሲገናኙ የተፈጠረው የናፍቆት መግለጫ ስሜት የሚዘነጋ አይደለም:: የቤተሰቡ አባወራ በቀድሞ የእስታትስቲክ መ/ቤት ሠራተኛ የነበረ ሲሆን ባለቤቱም እንዲሁ የተሻለ በሚባል ኃላፊነት ላይ ነበረች:: የዕድል ጉዳይ እንዲሉ ከመጀመሪዎቹ ዙሮች በአንደኛው የዲቪ ሎተሪ እጣ ወጥቶላቸው ከሀገር የወጡት ጋብቻቸውን በፈጸሙ ሰሞን ነበር::
በፍልቅልቅነቷ ሀገር የሚያውቃት ያቺ እህታችን ልዩ መገለጫዋ በዜማ የታጀበ ሣቋና ኩርፊያ የሚባል ነገር ያለማወቋ ነበር:: በወቅቱ ለአንድም ቀን ፊቷ አዝኖና ዳምኖ አይተናል የሚል ሰው ማግኘት አዳጋች ነበር:: ከዚህች እህት ጋር በተገናኘንበት ወቅት ያ ቀድሞ የምትታወቅበት ሣቅና ጨዋታዋ ከእርሷ ዘንድ አልነበረም:: ጨዋታ አድማቂነቷም ፍጹም ሸሽቷት ዝምታ የሚያስቆዝማት ሆኖ መታየቷ በእጅጉ ግራ ያጋባ ነበር::
በዚህ ያልተለመደ ባሕርይዋ የተደነጋገረው ይህ ጸሐፊ “እህቴ ሆይ ምን ሆንሽ? ያ ሣቅሽና ፈገግታሽ ወዴት ሄደ? ምንስ የከፋ ነገር ቢገጥምሽ?” በማለት ደጋግሞ ሲጠይቃት እምባ እየተናነቃት የሰጠችው መልስ፡- “የዚህ ሀገር ኑሮና ሕይወት ሣቄን ዘርፎኝ ሆደ ባሻ ሆኛለሁ:: ፈገግታዬም ጨልሟል…” የንግግሯን ዐረፍተ ነገር ሳትጨርስ ባለቤቷ ፈጠን ብሎ “ሣቄን ተሰረቅሁ! ተዘረፍሁ! የሚሉት ፈሊጥ አላት:: እባክህ እርሷን ተዋትና ወደ ሀገር ቤት ጭውውታችን እንመለስ” ::
“እንደራሷ ሀገር ጣራው እስኪገነጠል ድረስ ካልሣቅሁና ካላሣቅኋችሁ ማለት እዚህ ሀገር አይሠራም:: ሣቅ ካማራትና መንከትከት ካስወደዳት እዚያው የናፈቃት ሀገሯ ትግባ! ወይንም ከባሕሉና ከሕዝቡ አኗኗር ጋር ራሷን አስማምታ ትኑር…” ባልም ግሳጼውንና ቁጣውን አንጠልጥሎ የተወው እንደ መበሳጨት እያለ ነበር::
“ሣቄን ዘረፉኝ! ሣቄን ሰረቁኝ!” ይህ ንግግር ዛሬም ድረስ በፍጹም በውስጤ ማቃጨሉን አላቆመም:: በቀንም በሌትም “ለካስ ሣቅም ይዘረፋል!?” የሚለው ጥያቄ ሕሊናዬን ሠንጎ እንደያዘኝ አስታውሳለሁ:: ይህን መሰሉን የሕመም ስሜት በወቅቱ ለማስታገስ የሞከርኩት የዚያችን ምስኪን እህቴን የንግግር ኃይለ ቃል ተውሼ በብዕሬ ጉልበት መተንፈስ ነበር:: እናም ውስጤ እየተተረማመሰም ቢሆን “ሣቄን መልሱልኝ!?” በሚል ርዕስ አንድ ግጥም ጽፌ አበርክቼላታለሁ::
ግጥሙን በርከት ብለው በተሰበሰቡ የጋራ ወዳጆቻችን ጉባዔ ላይ ቆሜ ባነበብኩበት አጋጣሚም አብዛኞቹ አድማጮቼ ዐይናቸው በእንባ ሲረጥብ አስተውያለሁ:: ዛሬም የተሠረቀው የእህቴ ሣቅ ይመለስላት አይመለስላት እርግጠኛ አይደለሁም:: ያ ፍልቅልቅ ተፈጥሮዋ ተመልሶላት ከሆነ እሰዬው::
ወጤቱን የማውቀው ይህንን ጽሑፍ ልኬላት መልስ ስትሰጠኝ ይሆናል:: እስከዚያው ድረስ ግን “የሣቅ መዘረፉ ክስተት” ኃዘንተኛ በሆነችው ሀገሬም የባሕል ያህል ሥር እየሰደደ ስለሆነ ብንወያይበት አይከፋም በሚል እምነት የሰነበተውን የትዝታዬን ወግ ለማጋራት መልካም መስሎ ታይቶኛል::
“ኃዘንተኛ እናቴ!”
ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ ከትከት ብላ እየሳቀች የኖረችባቸው ዓመታት የትኞቹ ዘመኖች ይሆኑ? ለዚህ ጥያቄ በቀላሉ መልስ ለመስጠት እንደሚያዳግት አይጠፋኝም:: በወቅት ወለድ ፈተናዎች ብቻም ሳይሆን ሀገሬ የታሪክ ኃዘንተኛ ሆና ለዘመናት እንደኖረችም ይገባኛል::
በየትኛው ዘመን ከትከት እያለች ስቃ እንደነበር የአንተን ምላሽ አስቀድመህ ግልጽ አድርግልን የሚባል ከሆነ ግን የእኔ የአምደኛው መልስ አይ+አዎ (አያዎ Paradox) ይሉት ብጤ ነው:: የአያዎ መልሴን ይበልጥ እንዲያብራራልኝም አንድ ነባር ሀገራዊ “ተረት” ማስታወሱን መርጫለሁ::
“ሰማዩን ካልጨበጥኩ፣ ምድርን ካልጠቀለልሁ በሚል አፍቃሬ ራስነት የሚታወቅ አንድ እብሪተኛ የአካባቢ ሹም አንድ እለት አገልጋዩን ጠርቶ የሚከተለውን ትዕዛዝ አዘዘው ይባላል:: ሩቅ ሀገር ወደምትገኘው እናቴ ዘንድ ሄደህ ጤንነቷን ጠይቀህልኝ ተመለስ:: እናቴ ሞታ ከሆነ መርዶውን በነገርከኝ ቅጽበት አንተም የእርሷ እድል ይገጥምሃል:: በጤንነት አግኝተሃት መልካም ዜና የምታመጣልኝ ከሆነ ግን እሾምሃለሁ፣ እሸልምሃለሁ:: ምርጫው የራስህ ነው::”
“ምስኪኑ አገልጋይ የጨካኙን አስተዳዳሪውን የአደራ መልዕክት ተቀብሎ ወደ ተላከበት የእናቱ ሀገር ገሠገሠ ይባላል:: ከተባለው ቀዬ ብቅ ሲልም የሹሙ እናት ሞተው የቀበሌው ሕዝብ እዬዬውን ሲያቀልጠው ይደርሳል:: በኃዘኑ ቤት እንደምንም እስከ ሰልሥቱ ከሰነባበተ በኋላ የጎፈሬውን ግማሽ ተላጭቶ፣ ግማሹን እንደነበረ አጎፍሮ ወደ ጌታው ቤት ተመለሰ:: ጌቶችም መምጣቱን እንደ ሰሙ ‹እናቴን ደህና አገኘሃት?› ብለው ሲጠይቁት ወደ ተላጨው ጎፈሬው አመለከታቸው::
‹ወዬው እምዬ ሞተች ማለት ነው?” ብለው እሪታቸውን ሲያቀልጡ ‹ቢሞቱ ኖሮ ጎፈሬዬን አጎፍራለሁ?› በማለት ያልተላጨውን የጎፈሬውን ግማሽ ከመከም በጣቶቹ ጠቆማቸው:: ሞታለች?
አልሞተችም? እያሉ መሟገታቸውን ለጊዜው አልገፋበትም:: የሚሻለው “አፌን በዳቦ አብሱ” በማለት መረርና ጠነን ወዳለው ሀገራዊ ጉዳያችን መመለሱ ይሻል ይመስለናል:: “ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ ስቃ ታውቃለች? ወይንስ አታውቅም?” ለሚለው ጉንጭ አልፋ መሟገቻ ይህ የተረት ትረካ መልሱን የሰጠ ይመስለናል::
“ሣቅ ብርቁ ሀገሬ!”
“ያ ትውልድ” እየተባሉ ከሚታወሱት የሀገራችን አፍቃሬ ለውጥና ሞገደኛ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኮሌጅ ተማሪዎች መካከል ገጣሚ ዮሐንስ አድማሱ አንዱ ነበር:: ይህ ትንታግ ብዕረኛ የነበረበትን ፊውዳላዊ ዘመን እንደምን በግጥሙ ያብጠለጥል እንደነበር በብዙዎች ዘንድ ይታወሳል:: በተለይም “ኃዘንተኛ እናቴ” በሚል ርዕስ ጽፎ ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው በተገኙበት የኮሌጅ ቀን ላይ በ1954 ዓ.ም ካነበው ረጅም ግጥሞቹ መካከል ጥቂት ስንኞችን ተውሰን እንደሚከተለው እናስታውሳለን::
“ኃዘንተኛ እናቴ ኃዘንሽ ቢበዛ፣
መልክሽ ጠቆረብኝ ሆነብኝ ቀዛዛ::
ምንም ቤትሽ ቢፈርስ ኑሮሽ በደረባ፣
እግርሽ ቢሰነከል ብትሆኚ ሰለባ፣
ዳግመኛ እንድትመጪ ይታየኛል እኔ፣
ለልቤ ደስታ ሐሴት ለዘመኔ::
ትካዜሽ ወጨፎ ሰቀቀን ጭፈና፣
ሸረጠጠው ልቤን አደረገው መና::
ኃዘንተኛ እናቴ የመጣውን ቀንበር እኔም ልሸከም፣
ልረስ ልቆፍረው በተለምሽው ትልም::
ፈንታዬን ተወጣሁ ፍጆታው ለሌላ፣
የትልሙን ማቃኛ ይፍጠር ሌላ መላ::”
ይህ ግጥም ከሺህ ቃላት በተሻለ ትናንትን ብቻ ሳይሆን ዛሬንም በአግባቡ የሚገልጽ ይመስለኛል:: ሀገሬ ሣቅ ርቋት፣ ኃዘን አጥልቶባት መኖርን የባሕል ያህል በአሜንታ ተቀብላ ስለመኖሯ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሀገር የሚያውቀው ነው:: “ሣቅ ብርቋ፣ ኃዘን ውርሷ” ሆኖ እስከ መቼ ትኖራለች የሚለውን ጥያቄ እንደ ሕዝብ መጠየቅ ጊዜው የሚፈቅድ ይመስለናል::
የተዳፈሯትን ወራሪዎች ድል በመታች ማግሥት የተሰዉባትን ልጆቿን እርም አውጥታ ሳትጨርስና የኃዘን ጨርቋን ከመለወጧ እስቀድሞ ሌላ መልክ ብዙ አበሳዎችን ስትጋፈጥ ስለመኖሯ በዝርዝር እንተርክ ብንል ሰማዩ ብራና፤ ዓባይ ወንዛችንም ቀለም ቢሆን ተጽፎ ስለመጠናቀቁ እርግጠኛ ለመሆን ያዳግታል::
“ደስተኛና ሣቂታ ብቻ ሳይሆኑ የተደላደለ ኑሮ ያላቸው ሀገራት” በሚል ርዕስ ከአንድ ዓመት በፊት በተጠና ዓለም አቀፍ ጥናት መሠረት የክብር ደረጃውን የተጎናጸፉት አብዛኞቹ ሀገራት ስካንዲኔቪያን በመባል የሚታወቁት እንደ ፊንላድ፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን ወዘተ. የመሳሰሉት ሀገራት ናቸው:: የእኛይቱ “ኃዘንተኛ አደይ” የተሽቀነጠረችው ወደ 130ኛ ደረጃ ነበር:: ዛሬ ቢሆን ምናልባትም ወደ ኋላ አፈግፍጋ ከመጨረሻዎቹ የዓለም ሀገራት ዋነኛዋ ሳትሆን አትቀርም::
የኢትዮጵያ የመከራ ሱናሚ መቼ እንደሚሰክን ለመተንበይ የሚቻል አይመስልም:: ፈውስ አልባ የሆነው በሽተኛው ፖለቲካችን የሀገራችንን ሣቅ ነጥቆ “ኃዘንተኛ” ካደረጋት ዓመታት ነጉደዋል:: ይህም ያነሳት ይመስል በየጊዜው መልኩን እየለዋወጠ ፈገግታ አልባ የሚያደርጋት መከራ መቼ ከፍጻሜ እንደሚደርስም ለማወቅም ሆነ ለመተንበይ እንዳዳገተን እነሆ ዘመን ጠብቶ ዘመን እየመሸ ነው::
ጸሎታችንና ጾማችን፣ እርቅና መሸማገላችን፣ ይቅር መባባላችንና መወቃቀሳችን ስለምን ፍሬ አፍርቶ ከመከራ እንደማያሳርፈን እንደእንቆቅልሽ ከመሆንም አልፎ የባሕል ያሕል ተጣብቶን የኑሯችን አንዱ ክፍል እስከ መሆን ደርሷል::
ፖለቲካውን ስናስታምም ኢኮኖሚው ጤና አጥቶ አልጋ ላይ ይውላል:: ማኅበራዊ መስተጋብራችንን ያጠበቅን ሲመስለን የጎጠኝነትና የብሔር ልክፍት በየጊዜው እያገረሸ ያጥወለውለናል:: ወደየቤተ እምነቶቻችን ፈጥነን እየሮጥን ፈጣሪን የሙጥኝ እንዳንል የመሰናክሎቻችን አበዛዝ የትየለሌ ሆኖ ግራ ተጋብተናል::
ሕጉን በሕግ አምላክ ብንለው አልሰማ ብሎናል:: ጉልበተኞችንም በጉልበት አምላክ እያልን ብንማጸናቸው እብሪታቸውን አጠናከሩ እንጂ ተማጽኗችን ሊያራራቸው አልቻለም:: በወንጌል/በቁርአን አምላክ እያልን ሰባት ጊዜ ሰባ ሱባዔ ብንገባም ሰሚ አምላክም ሆነ አሰሚ አማላጅ አለሁ ሊለን አልቻለም:: ስለዚህ ኢትዮጵያ ሣቋ ተነጥቆ ፈገግታዋ ጨልሞ “የኃዘን ከል እንደለበሰች” ብትኖር መች ይፈረድባታል?
አንጀታችንን በአንጀታችን ቋጥረን ረሃብን መቋቋም ባሕላችንም ወጋችንም ነው – አላማረርንም:: በጦርነት ተጋድለንና ተቋስለን “በሆድ ይፍጀው” ብሂል የደም ሸማችንን ጠቅልለን ማስቀመጡንም በሚገባ እናውቅበታልን – ‹ግደል ተጋደል› ተለምዷዊ መፈክራችንም አይደል:: ፖለቲካና ዘመን አመጣሽ አይዲዮሎጂ ሲያመሳቅለንም በጎሪጥ እርስ በእርስ እየተጎሸማመጥን መተላለፍን ተክነንበታል – ደም ተቃብተንም ቢሆን አብረን መኖርንም በሚገባ እናውቅበታለን!
ይሄ ሁሉ ሀገራዊ ወፈፍታ አልበቃ ብሎን እነሆ ሌላ አሳርና መከራ ዝናብ እንዳረገዘ ደመና እያንጃበበ ለስቅቅ ዳርጎ አሸማቆናል:: ይህ ከቤተ እምነቶቻችን ጎራ አፈትልኮ የሚወጣው መብረቃዊ ሞገድ በጊዜ ታክሞ ካልዳነ በስተቀር ምን ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ለመገመት እንኳን የሚያዳግት ሆኖብናል:: “ለእኔ እናት ምን በጃት፣ ያም አፈር ያም ድንጋይ ያም ኮረት ጫነባት” ያለችው አልቃሽ እውነት ብላለች::
ቀደም ሲል የጠቀስነው ባለቅኔ ዮሐንስ አድማሱ “እስኪ ተጠየቁ” በሚል ርዕስ በ1954 ዓ.ም ከጻፈው የኮሌጅ ቀን ሌላው ግጥሙ ውስጥ በሚከተሉት ጥቂት ስንኞች ሃሳባችንን እናሳርጋለን::
“ይዘልቃል ወይ ከቶ በንዲህ ዓይነት ስልት፣
ወጋግራውን ሁሉ ምሶሶውን ሁሉ ቁንቁን ጨርሶት::
እንዲህ እንደሆነ ቤቱ በውነት፤ ባለም መቃብር፣
ማገሩ ሁሉ አልቆ ቤቱ ሆኖ አፈር፤
ግድግዳ ብቻዋን ቤት አትሆንም ሰልታ፣
በግድ የለሽ ሥራ አለማገር ቀርታ::
ወደፊትም ደግሞ ታስቡ እንደሆነ ትልቅ የቤት ሥራ፣
ግድግዳና ጣሪያው እንዲያምር በተራ፣
አለማገር ሆኖ እንዳይፈርስ አደራ::”
ነብየ እግዚአብሔር ኤርሚያስ ቢቸግረውና ግራ ቢገባው የሚከተለውን ጸሎት ወደ ፀባኦት ያደረሰው እንደሚከተለው በመቃተት ነበር:: “አቤቱ! የሆነብንን አስብ፤ተመልከት፣ ስድባችንንም እይ::…የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም:: …የልባችን ደስታ ቀርቷል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጧል:: አክሊል ከራሳችን ወድቋል:: ስለዚህ ልባችን ታሟል:: ስለዚህም ነገር ዓይናችን ፈዝዟል:: ስለ ምን ለዘላለም ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረጂም ዘመን ትተወናለህ? ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን” (ሰቆቃወ ኤርምያስ ምዕ. 5):: አሜን! የኢትዮጵያ ሣቅ ከተዘረፈበት አድራሻ እንደ ሀገራዊ ቅርሶቻችን ተመልሶ ለማየት ፈጣሪ ይርዳን::
ሰላም ለሀገሬ! በጎ ፈቃድም ለዜጎች::
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2015