
አዲስ አበባ፦ ከደንበል ሃይቅ 102 ሄክታር የሸፈነውን የእንቦጭ አረም በዘንድሮው ዓመት ጥቅም ላይ ለማዋልና ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት እየተሰራ እንደሆነ የባቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ ገለጹ።
የባቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የእንቦጭ አረም የደንበል ሃይቅን 102 ሄክታር ሸፍኗል። የእንቦጭ አረም በባህሪው አስቸጋሪ ከሚባሉ አረሞች ውስጥ አንዱ ስለሆነ ለማጥፋት የሕዝብ ተሳትፎ፣ ድጋፍ እና ቴክኖሎጂ የሚፈልግ ነው።
እንደ ባቱ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮ ዓመት 102 ሄክታር እንቦጭ ለማጽዳት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ ከተማ አስተዳደሩ የእንቦጭ አረምን ለማጥፋት በሁለት መንገዶች እየሰራ ነው። አንደኛው አረሙን ከሃይቁ ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አረሙን ጥቅም ላይ ማዋል ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ገዛኸኝ ገለፃ፤ በባቱ ከተማ እየተደረገ ባለው እንቦጭን የማጥፋት ዘመቻ ከ102 ሄክታር ውስጥ 18 ሄክታሩን እንቦጭ ማንሳት ተችሏል። በዚህ ዘመቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ አረሙ ሙሉ ለሙሉ ተነቅሎ የቃጠሎ ሥራ ይጀመራል። ይህ በዋናነት የሕዝብ ተሳትፎ ይፈልጋል።
የባቱ ከተማ ነዋሪ የእንቦጭ አረምን ለማጥፋት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ነው ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ የእንቦጭ አረምን ወደ ከሰል፣ ጌጣጌጥና ጫማ መቀየር የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርጾ የከተማ አስተዳደሩ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።
በዚህም የእንቦጭ አረምን ወደ ከሰል፣ ጌጣጌጥና ጫማ መቀየር እንደሚቻል የከተማ ወጣቶችን እያሰለጠነ እንደሆነ ከንቲባው ተናግረው፤ በዚህም በርካታ የከተማዋ ወጣቶች የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል ብለዋል። እንቦጭ ወደ ጥቅም የሚቀየር ከሆነ ከከሰል ምርት ጋር ተያይዞ እጅግ በጣም ተፈላጊ ነው። ይህም ውጤቱና የቅድመ ሙከራ ሂደቱ ታይቷል ብለዋል።
እንደ ከንቲባው ገለፃ፤ በዘመቻው የሚሰሩት ሁለቱ ሥራዎች ሲደመሩ የእንቦጭ አረም ስጋት ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ምንጭ የሚሆንበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህም እንቦጭን ከደንበል ሃይቁ ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ያስችላል። ይህ የሚሆነው ግን የሕዝብ ተሳትፎ ሲኖር ነው።
እንቦጭን በዚህ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት እንችላለን። ነገር ግን እንቦጭ በባህሪው ክረምት ሲመጣ መልሶ ስለሚበቅል ተደጋጋሚ የሆነ ሥራ ይፈልጋል ያሉት ከንቲባው፤ በዚህ ዙሪያ ማሽን መግዛት ከከተማ አስተዳደሩ አቅም በላይ ስለሆነ ችግሩን መፍታት ለሚችሉ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉለት በጽሁፍ ጥያቄ አቅርቧል ብለዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም