በስልጤ ዞን የምትገኘው ደጋማዋ ምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ለፍራፍሬ ልማት እጅግ ምቹ ነች።በተለይም ፖም ለማልማት እጅግ ምቹ እንደሆነች ይነገርላታል።ይሁን እንጂ ለረጅም ዘመናት የወረዳዋ አርሶ አደሮች ምቹ አየር ሁኔታ ተጠቅመው ፍራፍሬ በማምረት ተጠቃሚ አልነበሩም።ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ ግን የወረዳዋ አብዛኞቹ አርሶ አደሮች ፖምን በስፋት በማልማት ላይ ናቸው።አርሶ አደሮቹ በፖም ምርት ከራሳቸው ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በወረዳዋ በምዕራብ ሙጎ ቀበሌ የሙኖሮ መንደር ነዋሪው አቶ ፈድሉ አህመድ እንደሚናገሩት፤ የዛሬ 10 ዓመት ገደማ በግብርና ባለሙያዎች የተሰጣቸውን ስልጠና በመጠቀም የፖም ችግኝ ከጨንቻ አምጥተው ማልማት ጀመሩ።በአሁኑ ወቅት 40 የፖም እንጨት አላቸው፤ ከእነዚህ ውስጥ 20 እንጨቶች በማፍራት ላይ ናቸው። ከዓመት ወደ ዓመት ፖሞቹ የሚሰጡት ምርት እየጨመረ መጥቷል።ቤተሰብ በየወቅቱ ከጓሮ እየቀነጠሰ የሚመገበውን ሳይጨምር ከአንድ እንጨት እስከ 50 ኪሎ ይሰበስባሉ።
በግምት አንድ ኪሎ ፖም በሰፈራቸው ለሚገኙ ነጋዴዎች በ10 ብር በመሸጥ ሌሎች ለቤት አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ፍላጎቶችን እንደሚያሟሉ የሚናገሩት አቶ ፈድሉ፤ የወረዳዋ መዲና ወደ ሆነችው ሌራ ወስደው ቢሸጡ በኪሎ 30 ብር ያገኛሉ።ሆኖም ከቀበሌያቸው ወደ ወረዳቸው መዲና ለመሄድ የትራንስፖርት ችግር በመኖሩና ፖም በአፋጣኝ ለገበያ ካልቀረበ ስለሚበላሽ በሰፈራቸው ለሚገኙ ነጋዴዎች በርካሽ ዋጋ እየሸጡ መሆናቸውን ይናገራሉ።
እንደ አቶ ፈድሉ ማብራሪያ የገበያ ትስስር አለመፈጠር፤ የመንገድ ችግርና የውሃ ችግር ባለመቀረፉ ምክንያት ከፖም ልማት ማግኘት ያለባቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።የተለያዩ የውሃ አማራጮችን የሚጠቀሙበት ሁኔታዎች ቢመቻቹና በትላልቅ ከተሞች ከሚገኙ የፖም ፈላጊዎች ጋር የገበያ ትስስር ቢፈጠር የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ በድሉ ሽኩራላ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ፖም በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ያነሳሉ።20 የፖም እንጨት ያላቸው ሲሆን፣ ሃያውም በማፍራት ላይ ናቸው።አቶ በድሉ ከአንድ እንጨት በአንድ ጊዜ ከ30 ኪሎ በላይ እያመረቱ ሲሆን፣ በአካባቢያቸው በሚገኙ አነስተኛ ገበያዎች ውስጥ በመውሰድ ለነጋዴዎች እየሸጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።
እንደ አቶ በድሉ ማብራሪያ ፖምን ማምረት ሌሎች ሰብሎችን ከማምረት እጅግ የተሻለ ትርፍ እያስገኘላቸው ነው።ከዚህ በፊት እንሰት ብቻ ያለሙ ነበር፤ አሁን ደግሞ ከእንሰት ጎን ለጎን ፖም እያመረቱ ነው።ከእንሰት ከሚያገኙት የተሻለ ጥቅም ከፖም እያገኙ ናቸው።አንድ እንሰት ለምርት የሚበቃው በሰባት ዓመት ሲሆን፣ ፖም ከሰባት ዓመት ቀድሞ ይደርሳል።የፖም ምርትና የእንሰት ምርት በገበያ ካላቸው ተፈላጊነት አኳያም ሰፊ ልዩነት አለ ባይ ናቸው።
የውሃ እጥረትና ገበያ ትስስር አለመፈጠሩ ለፖም ልማት ችግር ሆኗል የሚለውን የአቶ ፈድሉን ሀሳብ የሚያጠናክሩት አቶ በድሉ፤ ከአምና ጀምሮ አልፎ አልፎ የፖም ቅጠል እየደረቀ መሆኑን ይናገራሉ።ቅጠላቸው የደረቁ ፖሞች ምርታማነት የመቀነስ ሁኔታ መታየቱን በመግለጽ ችግሩን ለባለሙያዎችና ለአመራሮች ቢያሳውቁም እስካሁን መፍትሄ እንዳልተገኘለት ጠቁመዋል።
በምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የሆርቲካልቸር ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ኸይረዲን መሃመድ እንደሚናገሩት የወረዳዋ አርሶ አደሮች ስለ ፖም ጥቅም እየተረዱ በመምጣታቸው በስፋት ማምረት ጀምረዋል።ከወረዳዋ ነዋሪ 90 በመቶ
የሚሆነው ፖም በማምረት ተጠቃሚ እየሆነ ነው።ከወረዳዋ መሬት 480 ሄክታር የሚሆን መሬት በፖም ተሸፍኗል፤ ከዚህ ውስጥ 54 ሄክታሩ በአሁኑ ወቅት ምርት እየሰጠ ነው።በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ በሄክታር እስከ 750 ኪሎ ግራም እየተመረተ ነው።በአማካይ ደግሞ በሄክታር 300 ኪሎ ግራም እየተሰበሰበ ነው።በዓመት በአማካይ እስከ 16 ሺ 200 ኪሎ ግራም እየተመረተ ነው።
አርሶ አደሮቹ በአቅራቢያቸው ባሉ ገበያዎች የፖም ምርትን ለነጋዴዎች እየሸጡ ተጠቃሚ እየሆኑ ሲሆን፤ ነጋዴዎች ከአርሶ አደሮች የሰበሰቡትን ወደ አዲስ አበባ መጫን ጀምረዋል።አንዳንድ አርሶ አደሮች ራሳቸውም በካርቶን በማሸግ አዲስ አበባ ወስደው አንድ ኪሎ እስከ 70 ብር እየሸጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ኸይረዲን ማብራሪያ፤ ከዚህ ቀደም የፖም ችግኝ በአብዛኛው ከጨንቻ በማምጣት በማባዛት ለአርሶ አደሮች የማከፋፈል ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወረዳዋ አዲስ የፖም የችግኝ ማፊያ ጣቢያ ተቋቁሞ ማፍላት ተጀምሯል።ተጨማሪ ሁለተኛ የፖም ችግኝ ጣቢያ በመቋቋም ላይ ሲሆን፣ በእነዚህ ጣቢያዎች የሚፈሉ ችግኞችን ለአርሶ አደሮች በስፋት ለማቅረብ ታቅዷል።
የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ክፍተት መኖሩን የሚያነሱት አቶ ኸይረዲን እስካሁን ድረስ አርሶ አደሮች በራሳቸው ወስደው ገበያ እየሸጡ እንጂ በመንግሥት በኩል ሁኔታው አልተመቻቸላቸውም።በቀጣይ ተቋማዊ በሆነ መልኩ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከህብረት ሥራ ኤጀንሲዎች ጋር በመቀናጀት አዲስ አበባ የሚሸጥበት ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ኸይረዲን እንደሚሉት፤ ፖም ከፍተኛ ውሃ የሚፈልግ ሲሆን ይህን ካላገኘ ደግሞ ምርታማነቱ ላይ የራሱ የሆነ ጫና ይፈጥራል።በተለይም በበጋ ወቅት ብዙ ውሃ ማጠጣትን ይፈልጋል። ይህን ችግር ለመቅረፍ አርሶ አደሮች የተለያዩ የውሃ አማራጮችን ተጠቅመው ውሃ እንዲሰበስቡና እንዲያጠጡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ነው።
በወረዳው በፖም ልማት ላይ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮች የወረዳው አስተ ዳደር ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ኸይረዲን መንግሥትም በወረዳው የፖም ልማት ላይ በስፋት የመሳተፍ ውጥን እንዳለው አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2011
በመላኩ ኤሮሴ