የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተጀመረው የፈረንጆች በጀት ዓመት የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማከናወን ሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በመመደብ ወደ ሥራ መግባቷን ገለፀች።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማህበራዊና ልማት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሞገስ ትናንት በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ቤተክርስቲያኗ በተያዘው በጀት ዓመት አራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር መድባ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን አስታውቀዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የልማት ኮሚሽኑ በሁሉም ቅርንጫፍና ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቶች 199 ፕሮጀክቶችን እንደሚተገብር የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በጥሬ ገንዘብ እና በአይነት በድምሩ ሁለት ቢሊዮን 381 ሚሊዮን 792 ሺ 670 ብር መመደቡን ገልፀዋል።
የተመደበው ብር ለጤና አገልግሎት፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለሴቶችና ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለተፈናቃዮችና ለጉዳት ተጋላ ጮች፣ ለትምህርት፣ ለመጠጥ ውኃ ግንባታና ንጽህና፣ ለአየር ንብረት ጥበቃ፣ ለስደተኛና ከስደት ተመላሾች ወዘተ… ድጋፍ ለመስጠት ጥቅም ላይ እንደሚውል ዋና ዳይሬክተሩ አብ ራርተዋል።
ቤተክርስቲያኗ ባለፈው በጀት ዓመት አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለአምስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ልዩ ልዩ የልማት ድጋፎችን ማበርከቷን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰው፤ ከዚህም ውስጥ በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በደቡብ ክልል ለተፈናቀሉ ሰዎች የተደረገው ድጋፍ ከፍ ያለውን ቁጥር እንደሚወስድ፣ ከተያዘው በጀትም 32 በመቶ ለዚህ ተግባር መዋሉን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የተቋቋመው የማህበራዊና ልማት ኮሚሽን ቤተክርስቲያኒቱ ካቋቋመቻቸው የበጎ አድራጎት ተቋማት አንዱ ሲሆን፤ በመላ ሀገሪቱ 13 ቅር ንጫፍና 58 ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም ከአራት ሺ በላይ ሰራተኞች እንዳሉት ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2011
በ ኢያሱ መሰለ