• ኤጀንሲው 4 ሚሊዮን ብር ከምዝበራ ታድጓል
አዲስ አበባ፡ የፌዴራል የተቀናጀ መሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ እየወሰዳቸው ያሉ ርምጃዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የኤጀንሲው የ9 ወር አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ እንዳሉት፤ ኤጀንሲው ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ የሄደበት ርቀት አበረታች ነው። ሆኖም ኤጀንሲው በሚያስተባብራቸው ተቋማት መካከል ያለው ቅንጅት በላቀ ደረጃ ቢጠናከር ከፍተኛ ወጪ ማዳን ይችላል።
በመሆኑም ሰፊ የዳሰሳ ጥናቶችን በማድረግ እና አሰራሮቹን በተገቢው በመፈተሽ ለብክነት የሚዳርጉ አሰራሮች ለይቶ የማስወገድ ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት ሰብሳቢው፤ በቅንጅትና በአንድ አቅዶ የመስራት ልምዶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አልማው መንግስቴ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት፤ ከኤጀንሲው የቢሮ ሕንጻ ኪራይ ጋር ተያይዞ ብልሹ አሰራሮች ነበሩበት። ለአምስት ዓመት ውል ተዋውሎ 9 ሚሊዮን ብር በዓመት ሲከፈልበት የነበረው የቢሮ ሕንጻ መንግስትን ለአላስፈላጊ ወጪ ከመዳረጉም ባለፈ ለግለሰቦች መበልጸጊያ ሆኖ ቆይቷል።
ሥለዚህ ውል የተገባው ለአምስት ዓመት ቢሆንም እንዲቋረጥ ተደርጎ ኤጀንሲው በዓመት 5 ሚሊዮን ብር ሌላ የቢሮ ሕንጻ በመከራየት ሲመዘበር የነበረውን 4 ሚሊዮን የመንግስት ገንዘብ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።
የመንግስትን ሀብትና ንብረት ለብልሽት ሲዳርጉ የነበሩ የአሰራር ጉድለቶች በኤጀንሲው እንደነበሩ
በውል ለይተን በመረዳታችን አቅደንና ተቀናጅተን መስራት እንድንችል አድርጎናል ያሉት አቶ አልማው በክትትልና ድጋፍ ወቅት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ያገኛቸውን ክፍተቶች እና የሠጠውን አስተያየት መሰረት በማድረግ የተቋሙን አሰራሮች በጥልቀት የመፈተሽ ስራ መሰራቱን አስታውሰዋል።
የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰይዳ ከድር እንዳብራሩት፤ከንብረት አያያዝና ግዥ ሥርዓት ጋር ተያይዞ ለምዝበራ የተጋለጡ አሰራሮችን ማስተካከል ተችሏል። ለትራንስፎርመር ግዢና ለኔትወርክ ዝርጋታ በሚል ያለአግባብ ወደ ግለሰቦች (ቢሮ አከራዮች) ኪስ ሲገባ የነበረ 750 ሺህ ብር ለመንግስት ተመላሽ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።
በሌላ በኩል ከሰራተኛ ቅጥር ጋር ተያይዞ የፌዴራል የተቀናጀ መሠረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ሰፊ ክፍተቶች ያሉበትና ያልተቀረፉ መሆ ናቸውን ጠቅሰው የመዋቅር ማሻሻያዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ምላሽ እንደሚያገኝ ገልጸዋል።
በኤጀንሲው ከሰው ኃይል ቅጥርና ከሌሎች ብልሹ አሰራሮች ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የነበሩ አመራሮች ለእስር ተዳርገው እንደነበር ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2011
በ መሃመድ ሁሴን