ዘመን በተቀያየረ ቁጥር የሴቶች ፀጉር አሰራር ፋሽንም አብሮ ይቀየራል። ትናንት የነበረው ፋሽን ዛሬ የለም። ዛሬ ያለው ፋሽን ነገ አይኖርም። ነገር ግን ከብዙ ግዜ በኋላ አንዳንድ የፀጉር አሰራር ፋሽኖች ተመልሰው ሊመጡ ይችላሉ። የሴቶች የፀጉር አሰራር ፋሽን ሲባል ታዲያ ዘመናዊውንና ባህላዊውን ያጠቃልላል። ምክንያቱም በአለም አቀፍ ደረጃ አብዛኛዎቹ እንስቶች የሚከተሏቸው የፀጉር አሰራር ፋሽኖች ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆኑ ነው።
ከዚህ ውጪ ግን ሴቶቹ እንደየሀገራቸው ሁኔታ የሚከተሏቸው ባህላዊ የፀጉር አሰራር ፋሽኖች ይኖራሉ። ለአብነትም በኢትዮጵያ ሽሩባ አንዱ ባህላዊ የሴቶች ፀጉር አሰራር ፋሽን ነው። ሹሩባ በኢትዮጵያ የገጠርም ሆነ የከተማ ሴቶች ወቅት ጠብቀው፣ በአል ተከትለው አልያም በፈለጉት ቀን መርጠው የሚሰሩት የፀጉር ፋሽን ሲሆን፤ አሁን አሁን በዘመናዊ የሴቶች የውበት ሳሎንም ጭምር በተለያየ ዲዛይን ሴቶች ይሰሩታል።
አሁን አሁን በሴቶች ዘንድ ዘመናዊን ከባህላዊ ያጣመረ የፀጉር አሰራር ፋሽን የመሰራት ፍላጎት እየጨመረ የመጣ ይመስላል። ከዚህ አንፃር ዘመናዊውን የሴቶች ፀጉር አሰራር ከባህላዊ ጋር በማደባለቅ ሁሉም አይነት የፀጉር አሰራር ፋሽኖች እኔ ዘንድ አለ የሚለው አራት ኪሎ ድንቅ ስራ ህንፃ ሶስተኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው ሃብትሽ የሴቶች የውበት ሳሎን ነው። ከፀጉር ስራ ፋሽኑ በዘለለ የእጅና የእግር ጥፍር ስራዬም የተዋጣ ነው ይላል።
ወንደሰን በቀለ የሀብትሽ የውበት ሳሎን ባለቤት ነው። በእርሱ የውበት ሳሎን በአሁኑ ጊዜ በብዙ ሴቶች ዘንድ የሚዘወተረው የፀጉር ፋሽን ‹‹ዌቭ›› ይሰኛል። ይህ የፀጉር አሰራር በሌሎች የውበት ሳሎኖችም ውስጥ ሴቶች የሚመርጡት የፀጉር ፋሽን ነው። ‹‹ዌቭ›› የሚባለው ስትሬት፣ ፐብሊሽና ስፌት ሲሆን ስፌቱ ‹‹ዌቭ›› ይሰኛል።
የ‹‹ዌቭ›› ፀጉር ስራ መጠቅለል ወይም ፀጉሩ ፍሪዝ እንዲሆን ማድረግ ሲሆን በቅድሚያ ሴቷ ፀጉሯን ታጥባና ተጠቅልላ ካስክ ውስጥ እንድትገባ ይደረጋል። ፀጉሯ ደርቆ ከካስክ ከወጣች በኋላ ፀጉሯ በፔስትራ ለስልሶ በካውያ ይጠቀለላል። ከዛ ፀጉሯ ሲዘረጋ ራሱ ከርል ይሆናል። ስፌት ደግሞ በፀጉሯ ላይ ሂዩማን ሄር መስፋት ሲሆን የተሰፋውን ሂዩማን ሄር በካውያ አማካኝነት ወደ ‹‹ዌቭ›› መቀየር ወይም በተለያየ መልክ ፀጉሩን መስራት ነው። ነገር ግን የአብዛኛዎቹ እንስቶች ምርጫ ዌቭ ነው።
ቀለም ሲሆን ደግሞ ገና እንዲይዝ እንደመጣች የቆሸሸው ፀጉር ላይ ከተቀባች በኋላ ትታጠብና ካስከ ትገባለች። ከካስክ ከወጣች በኋላ የምትፈልገውን የፀጉር አሰራር ትሰራለች። ነገር ግን ቀለም ከተቀባች ፀጉሯን ሁልጊዜም በተለያዩ ቅባቶችና እንደ ካስትር ኦይልና አልመንድ በመሳሰሉት ቅባቶች መንከባከብ የግድ ይላታል። ይህም ፀጉሯ እንዲፋፋና እንዲጠነክር ያደርገዋል።
ከ ‹‹ዌቭ›› የፀጉር ስራ በመቀጠል ሴቶች በሚፈልጉት የተለያየ ቀለሞች የፀጉር ቁርጥ ፋሽኖችን ይሰራሉ። በብዛት ሴቶቹ ለፀጉር ቁርጥ ምርጫው የሚያደርጉት ቀለም ሃይላይት ወይም ሁለት አይነት ቀለም ያለውን ነው። ከዘመናዊው የ‹‹ዌቭ›› ፀጉር ስራ በተጨማሪ በባህላዊ መንንገድ የሚሰራው አልባሶ የተሰኘው የፀጉር አሰራር በእንስቶች ዘንድ ተመራጭ የፀጉር ፋሽን ነው። በአብዛኛውም ጥምቀትን በመሰሉና በሌሎች በአላትና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ወቅት ሴቶች ይሰሩታል።
አልባሶ የሚሰራው ሹሩባው ከተሰራ በኋላ ከበስተኋላ ፍሪዝ ዊግ /የመቀሌ ዊግ/ በመስፋት ነው። ከዛም ጉብ ጉብ ብሎ በተጎነገጎነው ፀጉር ውስጥ የብረት ዱላ ይገባል። ከበስተኋላው ፍሪዝ ይሆናል። ከአልባሶ በተጨማሪ ሴቶቹ የተለያዩ ሹሩባዎችን በዊግና ያለዊግ ይሰራሉ። ቴዎድሮስና አምፖሎም ከሹሩባ ፋሽኖች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። እነዚህም ታዲያ ወቅት ያላቸው ሲሆን ሴቶች በብዛት ክረምት ላይ ይሰሯቸዋል። ነገር ግን አሁን አሁን በበጋም ጭምር ወቅት ሳይገድበው ሴቶች የሚሰሩት ፋሽን እየሆነ መጥቷል።
ከፀጉር ስራው በተጨማሪ ሴቶች በአብዛኛው የጥፍር ሙሌት /ጄል/ ‹‹በሺላክ›› ይጠቀማሉ። ሴቶቹ እንደጣት መጠናቸው በቁጥር ጥፍር ተለጥፎላቸው ፓውደር ጄል የእግርም ሆነ የእጅ ጥፍር ላይ እንዲሞላ ይደረጋል። አንድ ጊዜ የተሰራው ጥፍር ስራም እስከ አንድ ወር ድረስ ያገለግላል። ልክ እንደ ‹‹ዌቭ›› ሁሉ የጥፍር ሙሌትም በአብዛኛዎቹ የከተማ እንስቶች ዘንድ የሚዘወተር ፋሽን ሆኗል።
ስፌት የሚሰራው በትክክለኛው ሂዩማን ሔር ከሆነ ዋጋው ከፍ ይላል። ነገር ግን በአርተፊሻል ከሆነ ይቀንሳል። አብዛኛዎቹ እንስቶች ትክክለኛውን ሂዩማን ሄር ከሌላ ቦታ ገዝተው ይዘው በመምጣት የሚሰሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ አርተፊሻሉን ከ500 እስከ 700 ብር ከዛው ከፀጉር ቤቱ ገዝተው ይሰራሉ።
ሀብትሽ የውበት ሳሎን በውበት ኢንዱስትሪው ሰባት አመታትን የቆየ ሲሆን፤ ደንበኞች ወደ ሳሎኑ የሚመጡት በአብዛኛው በሰው ሰው ነው። ከዚህ በተጨማሪም በኢንስታግራምና ቴሌግራም ገፅ አማካኝነት የፀጉር ስራዎችን ተመልክተው ለመስራት የሚመጡም በርካቶች ናቸው። የገበያው ሁኔታም ጥሩ የሚባል ሲሆን አምስት ሰራተኞችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2015