ለሀገር ሰላምና ልማት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሰው ናቸው የዛሬው የዘመን እንግዳችን ፡፡ ትውልዳቸውም ሆነ እድገታቸው በቀድሞ አጠራር ኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት ሴሪናገባ አውራጃ አልጌ ሳቺ ወረዳ ሲሞቦና ገልጂ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አልጌ እና ጎሬ በሚገኘው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤቶች ተምረዋል፡፡ በደብረብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ገብተውም በመምህርነት የትምህርት መስክ ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በዳይሬክተርነትና ሱፐርቪዥን ትምህርት ተጨማሪ ዲፕሎማ፣ በትምህርት አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡
እንግዳችን በቀድሞው አጠራር ጋሞ ጎፋ ክፍለሃገር ተመድበው ቁጫ ቦላ በተባለ ትምህርት ቤት ለሁለት ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ ወደ ኢሉባቦር ተመልሰውም በተማሩበት አልጌ ትምህርት ቤት ከመምህርነት እስከ ዳይሬክተርነት ሰርተዋል፡፡ የስርዓት ለውጥ ሲመጣ መቱ ከተማ የጎልማሶች ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው በአካባቢው ላልተማረው ማህበረሰብ ከፍተኛ መሰረት መጣላቸው ይነገራል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኤስ.ኦ.ኤስ ችልድረንስ ቪሌጅ በተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ከተማሪዎች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊነት ጀምሮ ሐረር በሚገኘው የድርጅቱ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ጀነራል ማናጀር ሆነው ለትምህርት መስፋፋት ከፍተኛ ሥራ አከናውነዋል፡፡ በድርጅቱ አማካኝነት አስመራ በተመደቡበት ወቅትም ያስገነቧቸው 16 ህንፃዎች ዛሬም ድረስ ለከተማዋ ድምቀት እንደሆኑ ነው የሚጠቀሰው፡፡
ሰዎች ለሰዎች በሚባለው ድርጅትም ተቀጥረው በተወለዱበት ኢሉባቦር አካባቢ በርካታ ትምህርት ቤቶች፤ ህፃናት ማሳደጊያዎች፤ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ያከናወኑት እንግዳችን በተለይም የህብረተሰቡ የዘመናት ጥያቄ የነበሩ የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱ መንግስትና የልማት አጋሮችን በማስተባበር ያደረጉት አስተዋፅኦ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ «የልማት አርበኛ» የሚል ማዕረግ ጭምር አሰጥቷቸዋል፡፡
በዚህም አላበቁ «ኦነሲሞስነስብ» የተባለ ፋውንዴሽን በማቋቋም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የትምህርት ቤት፤ የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማቶች እንዲገነቡ አድርገዋል፡፡ መቱና አዲስ አበባ ላይ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ገንብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመቱ ዩኒቨርሲቲ አማካሪ የሆኑት እንግዳችን ደሃውን ህብረተሰብ የልማት ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በህብረተሰብ መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት ሽማግሌ በመሆን የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቋቁሞ በነበረና የኢትዮጵያ የሰላምና የዲሞክራሲ ማህበር ውስጥ በመሳተፍ የሰላምና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ለመንግስት ምክረ ሃሳብ ጭምር በመስጠት የላቀ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣም አቶ አረጋ ጌላን የዛሬው እንግዳ አድርጎ እንደሚከተለው ይዞላችሁ ቀርቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ታስረው እንደነበር ሰምቻለሁ። በእዚያ እድሜዎ ታስረው የነበሩበት አጋጣሚ ምን እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ አረጋ፡- በአካባቢያችን ዘመናዊ ትምህርት ባለመኖሩ አባቴ የቄስ ትምህርት ቤት ከወንድሞቼ ጋር ውዬ እንድመጣ ይልከኝ ነበር። ይሁንና እድሜዬ ገና ትንሽ ስለነበረ ከትምህርት ይልቅ ጨዋታ ላይ ነበር የማተኩረው። አብዛኛውን ጊዜ እንዳውም ከመምህሩ ባለቤት ጋር ቤት ቁጭ ነበር የምለው። በዚህ መካከል መንግስት በወረዳው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ይከፍትና እኔም አንደኛ ክፍል ገባሁ። ይሁንና መምህሩ ተማሪዎችን እየደበደቡ ስላስቸገሩ ተማሪዎቹ ሁሉ አድመው ከትምህርት ቤት ይቀራሉ፤ ትምህርት ቤቱ ይዘጋል። እኔም ገና ፊደል ሳለይ ትምህርት አቋረጥኩኝ።
አንድ ቀን የእኔን ፍየል ለመሸጥና አባቴ ልብስ ሊገዛልኝ ገበያ አብሬው ሄድኩኝ። ገበያ ውስጥ ልብሱን ለመግዛት እየተዟዟርን ሳለ በመካከል ግርግር ይፈጠራል፤ ከግራ ከቀኝ ‹‹ያዘው!›› ‹‹ያዘው!›› የሚል ነገር ሰማሁኝ። ግን እኔን ስላልመሰለኝ መንገዴን ልቀጥል ስል ያዙኝ። ከዚያ አባቴን አነጋግረው በግዳጅ ታፍኜ ትምህርት ቤት እንድገባ ተደረገ። አባቴ መጀመሪያ ላይ ቢያንገራግርም በኋላ ተስማማ። እናም እኔን ጨምሮ ከዚያ ትምህርት አፈንግጠው የወጡ ተማሪዎች ሁሉ ተለቅመው አልጌ ትምህርት ቤት ውስጥ ለሶስት ቀን ታሰርን። በየቀኑ አንዳንድ ራስ በቆሎ እየተቆላ እየበላን ነው ያሳለፍነው። በሶስተኛው ቀን የከተማ ልጆችን አምጥተው እያሳዩን እንደእነሱ ጎበዝ እንድንሆን መክረውን ወላጆች ፈርመው ወደየቤታችን ተመለስን። እናም በዚያ መንገድ ነው ትምህርት የጀመርኩት።
አዲስ ዘመን፡- በኋላም ትምህርት ለመማር ብዙ ዋጋ እንደከፈሉም ሰምቻለሁ፤ እስቲ ስለዚህ ሁኔታ በጥቂቱ ያጫውቱን?
አቶ አረጋ፡– ልክ ነሽ! በልጅ እድሜ የማይቻል የሚባል ዋጋ ከፍያለሁ። ይሁንና ትምህርት ቤቱ እስከ አምስተኛ ክፍል ብቻ ስለነበርና በአካባቢያችን ሌላ ትምህርት ቤት ስለሌለ አብዛኛው ተማሪ አምስተኛ ክፍልን ደጋግሞ ለመማር ይገደዳል። እኔም ሶስት ዓመት አምስተኛ ክፍል ላይ ቆይቻለሁ። በኋላ አባቷ ዳኛ የሆኑ አንድ ጓደኛዬ ወደ ጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ ጎሬ ሊዛወሩ እንደሆነ ሰማሁ። እባካችሁ ይዛችሁኝ ሂዱ የፈለጋችሁትን ስራ እሰራላችኋለሁ አልኳት። በነገራችን ላይ በእኛ ጊዜ ተማሪ ሰው ቤት ሲቀመጥ ውሃ ይቀዳል፤ ልብስ ያጥባል፤ እንጨት ይለቅማል። ጓደኛዬ ለአባቷ ስትነግራቸው በሃሳቡ ተስማምተው ይዘውኝ ሄዱ። ወላጆቼ ልጃችን የከተማ ዱሪዬ ሆነ አሉ። ግን እኔ የጓደኛዬ አባት ቤት ሆኜ በስራ አግዛቸው ነበር፤ ውሃ ወንዝ ወርጄ እቀዳለሁ፤ እንጨት እፈልጣለሁ፤ እላላካለሁ፤ ግን ደግሞ እንደተባለሁ አባትየው እኔንም ሆነ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት አላስገቡንም። አንድ ቀን ታላቅ ወንድማቸው ለእንግድነት በመጡበት ጊዜ ቤት ተቀምጠን ሲያዩ ተቆጥተው በማግስቱ ትምህርት ቤት እንድንመዘገብ አደረጉን። በወቅቱ ታዲያ በጣም ዘግይተን ስለነበር ሁለተኛ ሴሚስተር ላይ ነው መግባት የቻልነው።
በነገራችን ላይ ጎሬ የጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ ብትሆንም ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት ነበረባት። በከተማ በነበረችው ትንሽ ምንጭ ላይ ነዋሪው በየእለቱ ሲጋደል ነው የሚውለው። እኔም ከትምህርት ቤት ስመጣ ውሃ ለመቅዳት ረጅም ሰልፍ ነበር የምጠብቀው። አንዳንድ ጊዜ እንዳውም ተራው ሳይደርሰኝ እዛ ነው የማመሸው። አንድ ቀን ወረፋ ስጠብቅ ድንገት እንቅልፍ ይዞኝ ይሄድና ውሃ የምቀዳበትን ጣሳ ሰው ይዞብኝ ሄደ። በዚህ ምክንያት ውሃ ሳልቀዳ ወደ ቤት ባዶ እጄን ስመለስ ዳኛው በጣም ተቆጡና በዚያው ከቤታቸው አባረሩኝ።
ተስፋ ቆርጬ ወደሀገሬ እየተመለስኩ ሳለ በአጋጣሚ እዛው ከተማ የሚኖር የባላባት ልጅ የሆነ ጓደኛዬን አገኘሁትና ያለሁበትን ሁኔታ ስነግረው የሚኖርባቸውን ሴት አናግሮልኝ እሱ ጋር እንድቀመጥ ጠየቀኝ። እንዳለውም ሴትየዋ በደስታ ተቀበሉን። ምክንያቱም ደግሞ እንደነገርኩሽ እሱ የባለአባት ልጅ በመሆኑ ማር፤ ቂቤና እህል ይላክላቸው ስለነበር ስለቀለብ የሚያሳስብ ነገር ስለሌለ ነው። በተጨማሪም ደግሞ እየለመድኩኝ ስመጣ ስራ አግዛቸው ስለነበር ይበልጥ ወደዱኝ። የሚገርምሽ ግን ዳኛው ሰውዬ ትምህርት ቤት ድረስ ሄደው ‹‹እቃ ሰርቆኛልና ከዚህ በኋላ ዋስ አልሆነውም›› ብለው ከሰሱኝና ከትምህርት ቤት እንድባረር ጥረት አድርገው ነበር። በወቅቱ የነበሩት ኃላፊ መጀመሪያ ላይ እውነት መስሏቸው አባረውኝ የነበረ ቢሆንም ለቅሶዬን አይተው ስለነበር ብዙም ሳርቅ አስጠርተውኝ ሁኔታውን ጠየቁኝ። ጣሳው ሰው ወስዶብኝ እንጂ ሰርቄ እንዳልሆነ፤ እሱንም ቢሆን ለባለቤቱ መክፌሌን፤ የድሃ ልጅ መሆኔንና በከተማው ውስጥ ምንም ዘመድ እንደሌለኝ ነገርኳቸው። ይህንን ሲረዱ በጣም አዝነው ራሳቸው ዋስ ሆነውኝ ትምህርቴን እንድቀጥል አደረጉ።
ሴሚስተሩ ሲያልቅ ወደ ቤተሰቦቼ ሄድኩኝ፤ ለወንድሞቼ መማር እንደምፈልግና እንዲያግዙኝ ጠየኳቸው።
ቤተሰቦቼ ይህንን ፅኑ ፍላጎቴን ሲሰሙ የከፋ ተወላጅ ከሆኑ ባልና ሚስት ጓደኞቻቸው ጋር ሆኜ እንድማር አደረጉኝ። እነዚህ ሰዎች ልጅ ስላልነበራቸው በጣም ይወዱኝና እንደልጃቸው ያዩኝ ስለነበር አብሪያቸው እየበላሁ ስራ እያገዝኳቸው እነሱ ጋር ተቀምጬ ተማርኩኝ። ግን ከአንድ ቤት ሌላ ቤት በስቃይ ስለተማርኩኝ ስድስተኛ ክፍል ማለፍ አልቻልኩም። ይህም ቢሆን ግን ምንም አልተሰማኝም ነበር፤ ምክንያቱም እኔ መማሬ እንጂ ከክፍል ክፍል መዛወሬ ብዙም አያሳስበኝም ነበር እና ነው። ክረምት ላይ በደንብ ተዘጋጅቼ አጠናሁና በሚቀጥለው ዓመት ጥሩ ውጤት አምጥቼ አለፍኩኝ። ከዚያማ በቃ ትምህርቴን ይበልጥ እየወደድኩት መጥቼ በየዓመቱ ከፍተኛ ውጤት እያመጣሁኝ ነበር የማልፈው።
ዘጠኛ ክፍል ስደርስ የተለያዩ የትምህርት መስኮችን መምረጥ ቢቻልም በአጋጣሚ ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ በሄድኩበት አጋጣሚ እድሉ ያመልጠኝና እዛው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት እስከ 10ኛ ክፍል ቀጠልኩኝ። ከዚያ ግን የመምረጥ እድሉ ገጠመኝና ደብረብርሃን የመምህራን ማሰልጠኛ ተወዳድሬ ገባሁኝ። በወቅቱ የውጭ መምህራን ተመደብኩኝ። ግን ደግሞ የምሄድበት ገንዘብ አጥቼ ተቸገርኩኝ። የአካባቢው ማህበረሰብ ገንዘብ አዋጥቶልኝ ከጎሬ ጅማ በ19 ብር ከፍለው በአውሮፕላን ላኩኝ። ጅማ ስደርስ ደግሞ በአጋጣሚ የማውቀው ሰው አገኘሁና አዲስ አበባ ይዞኝ መጣ፤ እሱም ደብረብርሃን ላከኝ። ደብረብርሃን ከጠበኩት በላይ ጥሩ ኑሮ ነው የኖርኩት። ምክንያቱም ገጠር ስኖር በቀን አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ነው የምንበላው የነበረው፤ ደብረብርሃን ግን ጥሩ ጥሩ ምግብ እየቀረበልን በቀን ሶስት ጊዜ እንመገብ ነበር። አልጋውና መጣጠቢያውም እንደእኔ ላለ የገጠር ልጅ ብርቅ ነበር። በዚያ ሁኔታ ትምህርቴን አጠናቅቄ ዲፕሎማዬን አገኘሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስራ ከያዙ በኋላ የተወለዱበት ሥፍራ ተመልሰው በርካታ የልማት ስራ አከናውነዋል፤ ጥቂት የማይባለው በኢኮኖሚ ደህና ደረጃ ላይ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ለአካባቢ ልማት ጥረት ሲያደርግ አይታይም። ምክንያቱ ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ አረጋ፡– ለእኔ መማር ማለት ከማህበረሰባችን ትንሽ ላቅ ያለ አስተሳሰብ ሲኖረን ነው። ይህም ሲሆን ደግሞ ሳይማር ላስተማረው ወገኑ የተሻለ ህይወት ለማምጣት ብዙ ዋጋ ለመክፈል ቁርጠኛ ይሆናል። ለራሳችን ብቻ የምንኖር ከሆነ የተማርነው ትምህርት ዋጋ የለውም፤ ትርጉም ያጣል። ዋጋ ከፍሎ እዚህ ላደረሰን ማህበረሰብ መልሰን የምንከፍለው ነገር መኖር አለበት። አንቺም እንዳልሽው ብዙዎቹ ትልቅ ደረጃ ቢደርሱም የወጡበት ቀዬ ተመልሰው ለመሄድና የሕብረተሰቡን ችግር ለመረዳት አይፈልጉም። ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰው የተማሩበትን ትምህርት በቤትም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ዞር ብለው ያላዩ ብዙዎችን አውቃለሁ።
ወደገጠር በሄድኩኝ ቁጥር መፅሐፍት እለግሳ ለሁ፤ አቅሜ የሚችላቸውን የተለያዩ ድጋፎችንም አደርጋለሁ። ይህንን ደግሞ የማደርገው እኔ ለተወለዱበት አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ነው። የህብረተሰባችንን ኑሮ መቀየር እና ችግሩን ማቃለል ካልቻልን የተሻለ ኑሮ ላይ መሆናችን ትርጉም የለውም። ይህ ደሃ ህዝብ እኛን እኮ ያስተማረን እንጨት ቆርጦ፤ ድንጋይ ተሸክሞና ጭቃ አብኩቶ በገነባው ትምህርት ቤት ነው። ያ ማህበረሰብ በጉልበቱም ሆነ በገንዘቡ ዋጋ ከፍሏል። ይሄ እዳ መከፈል ይኖርበታል።
በተለይ የተማረ ሰው ብዙ ኃላፊነት አለበት፤ ይህንን የማያደርጉ ሰዎች በእውነቱ ተምረዋል ለማለት ያስቸግራል። እኛ ከፊት ምሳሌ መሆን ካልቻልን ሀገር ልታድግ አትችልም። እኔ ተቀጥሬ በምሰራበትም ጊዜ ሆነ አሁን በአካባቢዬ በሄድኩኝ ቁጥር የማህበረሰቡን ዋነኛ ችግር ምንእንደሆነ የራሴን ጥናት አደርግ እና ሌሎችን በማስተባበር ድጋፍ እንዲያገኙ አደርጋለሁ። ሌላው ቢቀር መፅሐፍትን ለምኖ አቅም ለሌላቸው የትምህርት ተቋማት ማድረስ ይቻላል። እኛ ሰው ቤት ተቀምጠን ነው የተማርነው፤ ስለዚህ እድሉን ላላገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻል አለብን።
እኔ የምችለውን ሁሉ ለአካባቢው ህብረተ ሰብ በማድረጌ ከፍተኛ ፍቅርና ከበሬታን አግኝቼበታለሁ። በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ጥያቄያቸው እንዲመለስ ስለምጥር ‹‹አምባሳደራችን›› እስከማለት ድረስ ያላቸውን ከበሬታና የሰጡኝን ኃላፊነት ይገልፁልኛል። አሁንም ድረስ ከሰዎች ለሰዎች ድርጅት ጋር በቅርበት ስለምንሰራ የጎደሉ ሥራዎችን እያየሁ እንዲደግፏቸውና የልማት ስራዎችን እንዲያከናውኗቸው ስለማደርግ ከህብረተሰቡ ከፍዬ የማልጨርሰው ፍቅር ነው ያገኘሁት። ህዝቡ በድግሱም ሆነ በሃዘኑ ይጠራኛል። ባልሄድም እንኳን ‹‹አረጋ ይስማ›› ይሉና ይጠሩኛል። ስሜ እዛ ተተክሎ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የሰላምና የዲሞክራሲ ማህበር ውስጥ በነበሩበት ወቅትም በሀገር ሰላምና አንድነት ዙሪያ ብዙ ስራ ማከናወኖት ይጠቀሳል፤ እስቲ ስለዚህ ስራዎ በጥቂቱ ያብራሩልን?
አቶ አረጋ፡- እንዳልሽው በልማትና በዲሞክራሲ ዙሪያ የሚሰራ ማህበር (ቲንክ ታንክ ግሩፕ) ውስጥ ነበርኩኝ። እኔ ብቻ ሳልሆን በርካታ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች ነበሩበት። በዚህ ግሩፕ ውስጥ እያለን በተለይ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ብዙ ጥረት አድርገናል። በወቅቱ ለነበረው መንግስትም ይሆናል የምንለውን ምክረ-ሃሳብ እናቀርብ ነበር። ከዚህም ባሻገር ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንም እንዲፈቱ የሀገራቱ መሪዎች ድረስ በማነጋገር የበኩላችንን ጥረት አድርገናል። ቢቀጥልና ቢጠነክር ኖሮ አሁን ላይ እንደሀገር ያጋጠሙን ችግሮች በሙሉ በተፈቱ ነበር። ምክንያቱም እንዳልኩሽ ከፍተኛ እውቀትና ተሞክሮ ያላቸው ሰዎች በመሆናቸው አለመግባባቶች የከፋ ችግር ከመፍጠራቸው በፊት እንዲፈቱ የማድረግ ብቃቱ ያላቸው በመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ በተወለዱበት አካባቢ የፀጥታ ችግር ስጋት ከሆነባቸው አካባቢዎች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ አኳያስ እንደሀገር ሽማግሌ ሰላም ለማምጣት ሚናዬን ተወጥቻለሁ ብለው ያምናሉ?
አቶ አረጋ፡- በመሰረቱ ማንኛውም ሰው ቢሆን በሰላም ወጥቶ መግባትን አይጠላም። እያንዳንዱ ሰው ቢጠየቅ በሰላምና በፍቅር መኖርን ነው ቀዳሚ ምርጫው የሚያደርገው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ‹‹የኤስ. ኦ. ኤስ መስራች ሄርማን ጊ ማይነር ›› ግለሰብ ሁልጊዜ ለሰላም የምንከፍለው ዋጋ ለጦርነት ከምንከፍለው በጣም በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ ሁሉም ለሰላም መስራት እንዳለበት ይናገሩ ነበር። እኔም በዚህ መርህ ስለኖርኩበትና ስለማምንበት ሁልጊዜም ቢሆን ለሰላም ቅድሚያ እሰጣለሁ። ደግሞም እንደተባለው ለሰላም በጣም ዝቅተኛ ዋጋ ነው የምንከፍለው። ለዚህም ነው በዚህም ሆነ በተወለዱኩበት አካባቢ ግለሰቦች እንኳን ሲጋጩ ቁጭ ብለው በመነጋገር እንዲፈቱት ግፊት የማደርገው። ምክንያቱም ቁጭ ብሎ በመነጋገር የምናጣው ነገር የለም።
እኔ ብዙም ፖለቲካ ውስጥ መግባት ባልፈልግም አሁን ላይ የሚያጋጩንን ርዕሰ ጉዳዮች በየአካባቢያችን ቁጭ ብለን ብንነጋገር ይፈታሉ የሚል እምነት አለኝ። ሰፈራችንን ሰላም ካደረግን ሀገራችንም ሰላም ትሆናለች። በመሆኑ ሁላችንም በየአካባቢያችን ለሰላም መሰረት መጣል እንችላለን። የማስተምረውም ይህንኑ ነው። ህዝቡ ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖር እያንዳንዳችን ኃላፊነታችንን ብንወጣ ብዙ ነገሮችን መለወጥ እንችላለን። ነገር ግን ምን ያገባናል ካልን የትም አንደርስም። ከዚህ አኳያ እንዳው በስፋት ሰርቼበታለሁ ባልልም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለሰላም እሰብካለሁ፤ እመክራለሁ፤ የተጣሉትን አስታርቃለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ የህብረተሰቡ አብሮ የመኖር እሴት መሸርሸሩ አሁን ለተፈጠረው አለመግባባትና ግጭት ምክንያት እንደሆነ ይነሳል። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ አረጋ፡– እንዳልሽው አብሮ የመኖር እሴቶቻችን መሸርሸር ለግጭት አንድ መንስኤ ሊሆን ይችላል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ያለፈ ታሪካችን ያጣላንና ለግጭት ምክንያት ሲሆን ይታያል። በመሆኑም የሚጣላን ያለፈ ታሪካችን ከሆነ ያለፈው አለፈ ብሎ ስለወደፊቱ መነጋገሩ ነው የሚበጀን። ለምሳሌ በሀገሪቱ የፊውዳል ስርዓት እንደነበር እየታወቀ አልነበረም፤ በደል አልተፈፀመም ብሎ ከመሟገት ይልቅ ለተፈጠረው ነገር ይቅርታ ተጠያይቆ ወደፊት መቀጠል ነው ለሁላችንም የሚጠቅመው። አለበለዚያ ግን ሁላችንም የየራሳችን ጥግ ይዘን ከቀጠልን ሀገርን ማዳን አንችልም።
እንዳነሳሽው የቀድሞው አብሮ የመኖር እሴቶቻችን መሸርሸር ለእኔም ስጋት ነው። ለትምህርትና ለስራ የተለያዩ አካባቢዎች ስሄድ ባዶ እጄን ነበር የምሄደው። በየሄዱከበት አካባቢ ያለውን ህዝብ ወገኔ አድርጌ ነው የኖርኩት። እነሱም ከሌላ አካባቢ ነው የመጣኸው ብለው አላገለሉኝም። አሁን ግን ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ያለመሳሪያ መንቀሳቀስ ስጋት የተፈጠረበት ሁኔታ ነው ያለው። እያንዳንዱ ሰው በስጋትና በጥርጣሬ የሚኖር ከሆነ እንደሀገር ለመቀጠል አስቸጋሪ ነው። እኛ ደብረብርሃን ስንማር አንድ የመንግስት መርሆ ነበር፤ ይህም ማንኛውም ተማሪ እጣ ወደ ደረሰበት ሀገር እንዲሄድ ይደረግ ነበር። ተማሪው የተወለድኩበት አካባቢ ብቻ ነው የምማረው ማለት አይችልም። ይህ የመንግስት ስርዓት ህዝብ ለህዝብ አስተሳሰረን እንጂ አልጎዳንም። ይቅርታ አድርጊልኝና በትምህርትም ሆነ በስራ ወደአንድ አካባቢ መሰባሰብ መልካም አይመስለኝም።
አዲስ ዘመን፡- ይህ አብሮ የመኖር እሴት በተሸረሸረበት ሁኔታ ወላጆች ልጆቻቸውን ልከው ለማስተማር ስጋት አይሆንባቸውም?
አቶ አረጋ፡- መቼም እንግዲህ ለዚህ ሁኔታ መፈጠር ሁላችንም ቢሆን ከተጠያቂነት አናመልጥም ብዬ ነው የማስበው።አሁንም ቢሆን ሁላችንም ብንጠየቅ የምናነሳው ችግር ተመሳሳይ ነው። ምኞታችንም ያን ያህል የተራራቀ ነው ብዬ አላምንም። እንደእኔ እምነት ሁሉም ተማሪ በየትኛው የሀገሪቱ ጥግ ሄዶ ያለስጋት መማር አለበት። ለዚህ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎቹ ባሉበት አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ከሌላ አካባቢ የሚመጣውን ተማሪ እንደራሱ ልጅ መንከባከብ አለበት፤ ተማሪውም ልክ እንደወላጆቹ የዚያን አካባቢ ማህበረሰብ ማክበር አለበት። ይህ ሲሆን ነው አሁን አንቺ ያልሽው ስጋት የሚጠፋው።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን የማድረግ ኃላፊነት የማን ነው?
አቶ አረጋ፡- ለእኔ እገሌ እገሌ ማለቱ ሊያስቸግረኝ ይችላል። ግን ለራሴ የማልፈልገውን ነገር ለሌላው ላለማድረግ መጠንቀቅ ይገባል። ሁላችንም በጎውና ክፉውን መለየት የቻልን ሰዎች እስከሆንን ድረስ ራሳችንን ከዚህ ተግባር ማቀብ ይገባናል። እርግጥ ነው፤ አንድ ሰው በጎ በማሰብ ብቻ ለውጥ ላያመጣ ይችላል፤ ግን በየአካባቢው ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ቢሞክር ሀገርን ማዳን ይቻላል። ስለዚህ በጥፋት መንገድ ያሉትን የመመለሱ ኃላፊነት የጥቂት ሰዎች ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነው።
በተለይ የሀገር ሽማግሌዎች መደመጥ መቻል አለባቸው። በፊት ሀገርን የሚመሩት የሀገር ሽማግሌዎች ናቸው፤ ህዝቡም የሚፈፅመው እነሱ ያሉትን ነበር። አሁን ግን ያ እሴት ጠፍቷል፤ የሀገር ሽማግሌዎች የሚሰማቸው አጥተዋል። ስለዚህ አሁን ያለውን ችግር መፍታት ከተፈለገ በተለይ ወጣቱ ሽምግሌዎችን ማክበርና ማዳመጥ መቻል አለበት። በእኛ ባህል የሀገር ሽማግሌ የማህበረሰቡ የበላይ ነው። ሲሄዱ እንኳን መንገድ ይለቀቅላቸዋል። ለግድያ የሚፈላለጉ ወገኖችን ሳይቀር ያስታርቃሉ። በሀገር ህልውና ላይ ሁነኛ አስተዋፅኦ ያላቸውን ሽማግሌዎች ዋጋ ካሳጣናቸው አደጋው የከፋ ነው የሚሆነው።
ለዚህ ደግሞ መንግስትን ብቻ መጠበቅ የለብንም። ለሽማግሌዎች ቦታና ክብር እንስጣቸው። መምህራንም በትውልድ ቀረፃ ላይ ኃፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። ማህበረሰቡም የአንዱ ሰፈር ሲቃጠል ለምን ማለት አለበት። በምንአገባኝነት አይደለም ሀገርን ራሳችንንም ማኖር አንችልም። የትልልቅ ሰዎች ቦታ ማጣት ይህችን ሀገር ገደል ይዞ ነው የሚገባው። በአጠቃላይ ለሀገር ዋጋ የከፈሉ ትልልቅ ሰዎችን አክብረን ከተወያያን የዚህን ሀገር ችግር መፍታት የማንችልበት ምክንያት አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡- እርሶም እንዳነሱት መንግስት አለመግባባቶችና ጥያቄዎችን መፍታት ያስችል ዘንድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁሟል። እርሶ ከዚህ የምክክር ኮሚሽን ምን ይጠብቃሉ?
አቶ አረጋ፡– ሰላም ለማምጣት ከንግግር እንጂ ከጦርነት አይጀመርም። በአፋችን መልካም ነገር ከተናገርን ሰላም ይመጣል። በመሰረቱ ይህንን የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙ ባለፈ ሌላ ምርጫም የለም። ለዚህች ሀገር ተስፋ የሚሰጠውም ይሄ ብቻ ይመስለኛል። በተለይ ሁሉም ህብረተሰብ እስከታች ድረስ የሚወያይ ከሆነ፤ ህዝቡ ከተደመጠና መግባባት ላይ ከተደረሰ አብዛኛው ችግር ይፈታል ብዬ አምናለሁ። ደግሞም ኮሚሽኑ ውስጥ የተመደቡት ሰዎች በእድሜም ሆነ በእውቀት የበሰሉ በመሆናቸው መፍትሔ ለማምጣት እንደሚሰሩ አልጠራጠርም።
እኔ ለዚህ ኮሚሽን ማሳሰብ የምፈልገው ነገር ቶሎ ውጤት ላይ መድረስ እንዲችል ነው። ምክንያቱም በዘገየ ቁጥር ችግሩ እየሰፋና መልክ እያጣ ይመጣል የሚል ስጋት ስላለኝ። ሳይዘገይ እስከታች በመውረድ ካወያየ ለውጥ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ። ምርጫችንም ይሄው ብቻ ነው። እርግጥ ነው በአንድ ጀምበር ችግር አይፈታም ግን ደግሞ በዘገየ ቁጥር የሚፈጠረውን ተጨማሪ ስጋት እንዳይኖር እና ችግራችንን እንዳያራዝመው መጠንቀቅ ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባ ቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ አረጋ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም