ጥር የአዲስ ተስፋ፤ የአዲስ ህይወት መጀመሪያ ነው፡፡ ከምርት ጀምሮ መልካሙን ሁሉ የምንካ ፈልበት፤ የተዘራው እህል አፍርቶና ተወቅቶ ወደ ጎተራ የሚገባበት ነው። ከዚህም ባሻገር የአደባባይ በዓላት የሚበዙበት ፤ ሕይወትን በአዲስ መልክ የሚጀምሩ ጥንዶችን የምናይበት የሰርግ ወርም ነው።
አዲስ ዝምድና መፍጠሪያ ወር ስለሆነ ወሩ የመሰባሰብ ወርም ይባላል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ‹‹የሙሽሮች ወር› ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ተሰባስቦ መደሰት ያለበት፤ ያለውን አብሮ መካፈል የሰፈነበት፣ እርቅና ሰላም የሚወርድበት፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአዲሶቹ ጥንዶች አዲስ ቤተሰብ ለመመስረት ተስፋ የሚሰንቁበትና አደራ የሚረከቡበት ወር ነው፡፡ እንደውም ከጋብቻ በኋላ ስላለው ነገር ሲነገር እንዲህ እየተባለ ይዘፈናል፡፡
« የዛሬ ዓመት አሃሃ
የዛሬ ዓመት
የሚጡ እናት፣
የዛሬ ዓመት አሃሃ
የዛሬ ዓመት
የማሙሽ አባት ፤
ይህ ሲታሰብ ደግሞ መውለድ መክበድ አለና ኑሮን ለማሻሻል ማቀድም ግድ ነው፡፡ የዛሬው አስተሳሰብ እንደ ትናንቱ አይደለም፡፡ ልጅ በእድሉ ይኖራል አይባልም ፤ ከእድል በላይ መስራትና ቅሪት ማስቀመጥ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን፡፡ እናም እናት አባት ለመሆን የተዘጋጁት ሙሽሮች ለነገው ልጆቻቸው ምን መስራት እንዳለባቸው ያስባሉ። የሠርጉን ቀን ከማቀድ ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያለውን ፕሮግራም ያካተተው ስርዓት ይነድፋሉ፤ ይህ ደግሞ እንደ የአካባቢው ባህል የተለያየ ነው።
ወቅቱ ምንም እንኳን ጎተራው የሚሞላበት ቢሆንም የሰርግ ግብዣዎች በአግባቡ ካልታቀዱ ለሰርገኞች ሆነ ለቤተሰቦቻቸው የችግር ምንጭ መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡ በከተማ ከአዳራሽ መረጣን ጀምሮ የቪዲዮ እና የፎቶግራፍ፤ የኬክ እና የመኪናዎች ወዘተ፤ በገጠርም የአካባቢው ማህበረሰብ የሚጠብቀውን ከዛም ያለፈ ድግስ ለማዘጋጀት የሚደረግ ጥረት ከፍያለ የችግር ምንጭ ይሆናል።
‹‹ሰርግና ሞት አንድ ነው›› በሚል የሚደረገው የሰርግ ግብዣ የሙሽሮችን ሆነ የቤተሰቦቻቸውን ቀጣይ ጊዜያት በችግር የተሞሉ ከማድረግ ባለፈ፤ የተጋቢዎችን የእለት ተእለት ሕይወት ፈታኝ ሲያደ ርጉት ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት ለመፍረስ አደጋ የሚጋለጡ ጋብቻዎች ጥቂት አይደሉም ፡፡
እንደ ሀገር በሰርግ ወቅት የሚፈጠር አላስፈላጊ ወጪን፤ ድካምን ለመቀነስ ገና ብዙ መስራት የሚጠይቅ ነው። ሙሽሮችና ቤተሰቦቻቸው አቅማቸውን ተረድተው እራሳቸውንና ህይወታቸውን የሚመስል ግብዣ ማዘጋጀት መልመድ ይጠበቅባ ቸዋል። የሰርግ ግብዣዎች በየትኛውም ሁኔታና ደረጃ ቢዘጋጁ ስህተት በማነፍነፍ እና ይህንኑ በማጎላት በሚታወቁ ግለሰቦች የአንደበት ቃል ሰለባ መሆናቸው የማይቀር ነው።
የሆነ አቃቂር ወጥቶላቸው ከሰርጉ እለት ጀምሮ አጀንዳ የመሆናቸው እውነታ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። በሁለንተናዊ መንገድ ለአሉባልታ ሰለባ ያልሆነ የሰርግ ግብዣ አለ ብሎ አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚያስችል ተሞክሮ አለ ለማለት የሚከብድ ነው።
ከዛ ይልቅ በሀገራችን የተከሰተው የኮሮና በሽታ በአስገዳጅ ሁኔታ ይዞት የመጣውን ተሞክሮ ማንሳት ይሻላል። በሽታው እንኳን መጣ ባይባልም ይዞት መጥቶ የነበረውን በጎ በጎ ተሞክሮዎች ማሰብ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተሻለ እድሎችን መፍጠር ያስችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በበሽታው መሰባሰብ ባለመፍቀዱ ብዙ ድግሶች አልታዩም፡፡ እንደውም አንዳንዱ በማህበራዊ ሚዲያዎች ማግባቱን ነግሮን ያለፈበት ጊዜም ነበር። ይህ ደግሞ ሁለት ነገሮችን ያቀለለልን መስሎ ይሰማኛል፡፡ የመጀመሪያው በርካታ ሰዎች በበሽታው እንዳይያዙ ያደረገ ሲሆን፤ ሁለተኛው በርካቶችን ካላስፈላጊ ወጪ የታደገ መሆኑ ነው፡፡ ሙሽሮቹ ለቀጣይ ወጪያቸው ቅሪትን ትተው እንዲያልፉ መልካም አጋጣሚን ፈጥሮላቸዋል፡፡
ከዚህ አለፍ ሲልም ሁሉም የተስማማበትና የተቀበለው ድግስ፤ እንኳን ደስ ያለህ(ሽ) የተባለበት ጋብቻም ሆኖ እንዲያልፍ አግዟቸዋል፡፡ ለምን አልተጠራሁምን ስላስቀረ በድግስ ጥሪ ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን መቀያየምም አስቀርቷል። እንዲህ ይሁን ባይባልም የሰርግ ድግሶች አቅምን ታሳቢ ባደረገ መንገድ በዘላቂነት ተግባራዊ የሚሆኑበት ስርአት ቢበጅ መልካም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የገጠሩን የሰርግ ድግስ እንደ አንድ ተሞክሮ ብንወስደው ይጠቅመናል፡፡
በገጠር የሚደረጉ የሰርግ ድግሶች ገና ከጅማሮው የአካባቢው ነዋሪ ተሰብስቦ የሚመካከርበት ነው። ማን ምን ያድርግ የሚባልበትና የሥራ ክፍፍል ጭምር የሚከናወንበት ነው፡፡ በመሰባሰብ ውስጥ መተባበር ግድ የሆነበት የሰርግ ድግስ አይነት ነው፡፡ ደጋሽ ሰው ብቻውን ሁሉንም የማይወጣበት፡፡ ሰው ያለውን የሚያዋጣበት፣ ጉልበቱንም፣ አቅሙንም የማይሰስትበት ነው፡፡
ጎረቤት የሙሸሮቹን “ሸብ ረብ አለች ምድር” እያለ ሽሙንሙን አድርጎ የሚድርበት ነው፡፡ በዚያ አጋጣሚም ሌሎች መልካም ነገሮች በተደራቢነት ይከናወናሉ፡፡ መቃቃር ይወገዳል፤ ፍቅር ይሰፍናል፡፡ የተጣላ እንኳን ተበድሎ ቢሆንም ይቅርታ ይጠይቃል። ምክንያቱም ያለ ጎረቤቱ ማንም የለውም፡፡
ይህንን የማያደርግ ሰው ካለ ደግሞ ተከሳሽና ተወቃሽ ነው፡፡ ሰርጉን ብቻውን በላው ይባላል፡፡ ይህ ደግሞ ክፉ ስድብ ነው። ይህ እንዳይሆን የሙሽሮች ወላጆች ሰርጉን ገና ከጅምሩ ለጎረቤት በማሳወቅ ጎረቤቱን የዝግጅቱ ዋነኛ ተሳታፊ ያደርጋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ያልተጠበቀ መጥፎ ነገር እንኳን ቢከሰት ኃላፊነቱ የጋራ ይሆናል፡፡ ይህ የሚያኮራ ባህላችን ዛሬም ሕያው በመሆኑ ወደዚህ ባህላችን ለመመለስ አልረፈደብንም፡፡ በዚህም የጥቅምት ወር መልካም ትሩፋቶቻችንን ከስጋት በማራቅ ወሩ ከፍ ያሉ የጥር በረከቶችን መሰብሰቢያ ማድረግ እንችላለንና እንጠቀምበት፡፡ በዚህ አይነት ከፍ ያለ ድምቀት ፈክቶ እንዲያልፍም እናድርገው፡፡
ክብረ ነገስት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም