የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ ነው። የሬክታንግል ቅርጽ አለው። ስሪቱ ከብረት ነክ ነገሮች ነው። አፍ ላይ ከወዲያ ወዲህ በማንቀሳቀስ ድምጽ እንዲያወጣ ይደረጋል። በዚህ መሳሪያ ጨዋታ ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ከንፈርና ምላስ ናቸው። አጨዋወቱም አየር በማስገባትና በማስወጣት ነው። ይህ የሙዚቃ መሳሪያ ‹‹ሀርሞኒካ›› ይባላል። ‹‹ሀርፕ›› ከሚለው የፈረንሳይኛ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም የአፍ ክፍል እንደማለት ነው። መሳሪያውም በአፍ ብቻ የሚጫወቱት ነው።
ሀርሞኒካ በተለያዩ የዓለም አገራት የታወቀ ቢሆንም መነሻው አውሮፓና አሜሪካ ውስጥ ነው። ዓለም አቀፍ ተወዳጅነት ባላቸው የብሉስ፣ ፎክ ሙዚክ፣ ክላሲክ ሙዚክ፣ ጃዝ እና ሮክ ሙዚቃዎች ይጠቀሙታል። ሀርሞኒካ መነሻው ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያ ነው፡፡
ይህን ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያ ከኢትዮጵያዊው አገር በቀል ዋሽንት ጋር እናነጻጽረው። ዋሽንት የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ ነው። የሚሰራው ከሸንበቆ ተክል ሲሆን አሁን አሁን ከብረትና ከፕላስቲክ መሥራት ተጀምሯል። ዋሽንት አራት ወይም አምስት ቀዳዳዎች ያሉት ሲሆን፤ ዋሽንት ተጫዋቾች እንደሚሉት የተለያየ ዜማ መፍጠር የሚቻለው ቀዳዳው ላይ የሚያርፉ ጣቶችን ምት በመቀያየር ነው። አጨዋወቱም ሙሉ በሙሉ በትንፋሽ ነው። ተጫዋቾች የቀዳዳዎችን ምት በመቀያየር በፈለጉት ቅኝት ይጫወቱታል።
ሀርሞኒካን ከዋሽንት ጋር ያነፃፀርነው ዛሬ ጥምቀት ስለሆነ እና በጥምቀት በዓል ላይ ሀርሞኒካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለመደ ስለሆነ ነው። ጥር 10 ቀን በዋዜማው (ከተራ) እና ጥር 11 ቀን የጥምቅ ዕለት ጃንሜዳ ከጫፍ እስከ ጫፍ ይደምቃል። በተለይም በከተራው ዕለት ወጣቶች እዚህም እዚያም ክብ ሰርተው ይጫወታሉ።
በዚህ የጥምቀት ጨዋታ ታዲያ እየገነነና በጣም ታዋቂ እየሆነ የመጣው የሀርሞኒካ ጨዋታ ነው። እዚህ ቦታ ላይ እንደ አታሞ እና ዋሽንት የመሳሰሉ አገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያዎች አይታዩም። የሚገርመው ግን የእነዚያ ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች አጀማመርም ሆነ ዕድገት ከራሳችን የሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ነው።
ኩረጃ ልማዳችን ነውና እነሆ ሀርሞኒካ የጥምቀት መለያ ሆኗል። የሬዲዮም ሆነ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የጥምቀት ሰሞን የሚያሰሙንና የሚያሳዩን የሀርሞኒካ ጨዋታ ነው። በእርግጥ ሜዳው ላይ ያለው እሱው ስለሆነ የሚቀረጸውም ይሄው ነው፤ ግን መጀመሪያውኑም ከአገር በቀል መሳሪያዎች በላይ ስላስተዋወቁት ነው፡፡
እርግጥ ነው መጠቀሙ ምንም ችግር የለውም፤ ለአጨዋወትም ቅልጥፍና ያለው ቀላል መሳሪያ ነው። ዳሩ ግን የአባቶች ጥበብ የታየበት የአገራችን የሙዚቃ መሳሪያዎችን ሙሉ በሙሉ እየዋጣቸው ነው። የሀርሞኒካ የጥምቀት ጨዋታ መሳሪያው ብቻ አይደለም አገር በቀል ያልሆነው፤ ራሱ የሚጫወቱት ጨዋታም ከአገሪቱ ወግና ባህል ወጣ ያለ ነው። እርግጥ ነው እነዚህን ጨዋታዎች ራሱ ሀርሞኒካው አላመጣቸውም፤ ግን ሀርሞኒካውን ሲጠቀሙ የመዘመንና የመሰልጠን ምልክት ስለመሰላቸው ጨዋታውም ተቀይሯል። አለባበሳቸውና ለጨዋታ የሚጠቀሟቸው ቃላት በኢትዮጵያ ወግና ባህል ውስጥ ያልተለመዱ ናቸው።
‹‹ወደ ዘመናዊነት ሽግግር እና ባይተዋርነት በጃንሜዳ ሀርሞኒካ ቃል ግጥሞች ክዋኔ›› በሚል ርዕስ ሕሊና ሰብስበው የተባሉ አጥኚ በዚሁ ጉዳይ ላይ የሰሩት ጥናት አለ። አጥኚዋ አዲስ አበባ ውስጥ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶች የሚጫቱትን ጨዋታ በማስተዋልና በማነጋገር የሰሩት ነው።
በጥናቱ ላይ የተጠቀሱት የቃል ግጥሞች እንደሚያሳዩት፤ አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት የነበሩ የስነ ቃል ግጥሞችን ለዘመኑ በሚሆን መልኩ የተቀየሩ ናቸው። ይሄ ማለት አሁን ላይ የሚታየውን ነባራዊ ሁኔታ እንዲገልጹ ተብሎ ማለት ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ በታዋቂ ዘፋኞች የሚታወቁ የዘፈን ግጥሞችን አንደኛውን ስንኝ በመቀየር የሚጫወቷቸው ናቸው። እንግዲህ በዚህ ቦታ ላይ ያሉት ወጣቶች ስለሆኑ፤ በዚያ ላይ የጥምቀት ጨዋታ ስለሆነ፤ ዋና ዓላማው መዝናናት እንጂ ማስተማር አይደለም። ለምሳሌ የአብርሃም በላይነህ ‹‹ውበቷ ውበቷ የዚች ልጅ ውበቷ›› የሚለውን ዘፈን ‹‹ውሸቷ ውሸቷ የዚች ልጅ ውሸቷ›› እያሉ ይዘፍናሉ። አንዳንዴ ለማሳቅ ተብሎም ነውር የሆኑ የወሲብ ቃላት ይገቡበታል። በእርግጥ እነዚህ የወሲብ ቃላት መተኪያ የሚሆን የአራዳ ቃላት ስለተፈጠረላቸው በአራድኛው ነው የሚጠቀሙት።
እነዚህ ወጣቶች ጨዋታና ዋዛ ፈዛዛ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችንም ያነሳሉ። ቀደም ባለው ጊዜ የነበሩ የስነ ቃል ግጥሞችን በዚህኛው ዘመን አውድ ይቀይሯቸዋል። ለምሳሌ
አሥር ሳንቲም ያለው አይባልም ድሃ
አምስቷን ለዳቦ አምስቷን ለውሃ
ይባል ነበር። ይሄ ግጥም የተፈጠረው በአምስት ሳንቲም ዳቦ መብላት ይቻል በነበረበት ዘመን ነው። አሥር ሳንቲም ያለው የተሻለ ስለሆነ ድሃ አይባልም ነበር ማለት ነው። አሁን ላይ በዚህ ግጥም መዝፈን የድሮውን ለማስታወስ ካልሆነ በስተቀር የዚህን ዘመን ሰው ብሶት ሊገልጽ አይችልም። እናም በዚህ ጥናት ላይ እንዲህ ተብሎ እናገኘዋለን፡፡
አምስት ሳንቲም ያለው አይባልም ድሃ
በጀሪካን ሙሉ ይጠጣል ውሃ
አጥኝዋ የድሮውን አልጠቀሱትም፤ የጠቀሱት የአሁኑን ብቻ ነው። ይህ የድሮውን ቀየር ተደርጎ የተዘፈነው ዘፈን አምስት ሳንቲም ምንም ጥቅም እንደሌለው የሚገልጽ ነው። ውሃ ከመጠጣት ውጭ ሌላ ነገር ሊገዛ አይችልም። አጥኝዋ ከባድ ድህነትን የሚገልጽ ነው ብለውታል።
ራሳቸው ወጣቶች እየፈጠሩ (ከዘፈኖች እያገጣጠሙ) አስተዳደራዊ ሥርዓቶችንና የተቋማትን የአሰራር ውጣ ውረድም ይገልጻሉ። ለምሳሌ
ባናገርኩሽ ቁጥር አትበይ ባሌ ባሌ
አታካብጅ ነገሩን ልክ እንደ ቀበሌ
በጥምቀት በዓል ላይ ስልክሽን ስጭኝ ወይም እንጫወት ብሏት ‹‹ባል አለኝ›› ብላ እምቢ ላለች ሴት የተዘፈነ ነው። ባል ባይኖራትም ለመግደርደር ‹‹ባል አለኝ›› ልትል ትችላለች። በትክክል ያገባች ብትሆንም ደግሞ የወጣትነት ነገር ነውና ‹‹ታዲያ ብታገቢስ ምን ችግር አለው?›› በሚል ስሜት ነው ‹‹ምን ታካብጃለሽ!›› የተባለችው። እንግዲህ በዚህ ጨዋታ ውስጥ ነው ከቀበሌ አሰራር ጋር ያነፃፀራት። ቀበሌ የሚለው ለግጥሙ ቤት መምታት ቢመረጥም ሁሉንም ተቋማት ይወክላል፤ ሲቀጥል ደግሞ ቀበሌ ውስጥ ጉዳይ ስለሚበዛ የባለጉዳዮች መጉላላት ይበዛል፤ ግልጹን እንናገር ከተባለ ደግሞ የቀበሌዎች አሰራር የዘመነ አይደለም፤ ለትንሽ ትልቁ ቀጠሮ ይበዛበታል።
አጥኝዋ በጥምቀት ላይ ያስተዋሉት ነገር ባህላዊም ዘመናዊም እንዳልሆነ ይገልጻሉ። ተጫዋቾች ከፊልምና ከተለያዩ ነገሮች ያጠረቃቀሙትን ነው ጉራማይሌ አድርገው የሚታዩት። ይሄው የሚጠቀሙት ግጥም እንኳን ጉራማይሌ ነው። ድሮ የነበረውን የመጨረሻ ስንኙን በመቀየር ነው። አለባበሳቸው፤ የሂፕሆፕና ራፕ ዘፋኞች፣ የሆሊውድ ፊልሞች ላይ ከባባድ ወንጀል የሚፈጽሙና የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ነው። የሀርሞኒካ ከዋኞች እነዚህን አካላት ስለሚያደንቋቸው ብቻ እንጂ መልዕክቱ ገብቷቸው አይደለም። ማፈንገጣቸውም በውጫዊ ተፅዕኖ ምክንያት እንጂ በእውቀትና በይሁንታ አይደለም።
በሀርሞኒካ ጨዋታ ነውር የሆኑ ነገሮችን እያነሱ ይጫወታሉ። ነውር ሲባል ቃላቱ ሳይሆን ድርጊታቸው ነው። አጥኝዋም ‹‹ነውር›› ሲሉ ነው የሚገልጹት፤ በነገራችን ላይ እነዚህ ነውር የሆኑ ድርጊቶችን የተጠቀሙት ለማሞካሸት ወይም ለማበረታታት ላይሆን ይችላል። እንዲያውም እየሰከሩና እያጨሱ ከሚተወንበት ፊልም እነዚህ ይሻላሉ። ግጥሙን የሚሰማ ታዳሚ እየተዝናና ነውርነቱንም ማሰብ ይችላል። ለምሳሌ እንዲህ ይባላል፡፡
ያሙናል ያሙናል
ይመለከቱናል
ጫት ቤት ይውላሉ ይሉናል
አዎ ያሙናል
እኛ ተሻሽለን ሽሻ ጀምረናል፡፡
በዚህ ግጥም ውስጥ ምፀት ይታያል። እርግጥ ነው ድርጊቱ ነውር መሆኑን የሀርሞኒካ ተጫዋቾችም አምነዋል። አምነውም ነው ‹‹ያሙናል›› ያሉት። ‹‹እኛ ተሻሽለን ሺሻ ጀምረናል›› ሲሉ በምፀት ሽሻ ከጫት በላይ ነውር መሆኑን እየተናገሩ ነው። እዚህ ላይ እንግዲህ እንደ አረዳዳችን ነው። ብዙ ጊዜ ግጥም በቀጥተኛ መልዕክት አይገለጽም። ምናልባት ግን ይሄኛው የዘፈን ግጥም ስለሆነ ያን ያህል ይራቀቁበታል ብሎ ለማሰብ አያስኬድ ይሆናል። የሆነው ሆኖ ግን ከጫት ወደ ሽሻ መሄድ ከሱስ መላቀቅ ነው ብሎ የሚያስብ አይኖርም።
ከዚህ ይልቅ ነውር የሚሆኑት በዕድሜ የገፉ ሰዎችን የሚሳደቡ የግጥም ዘፈኖች አሉ (ግጥሞችን እዚህ አልጠቀማቸውም)፤ በአካላዊ ሰውነታቸው ማሸብሸብና እንደ ወጣት ሴቶች ማራኪ ባለመሆናቸው የሚሰነዘሩ ቃላት ነውር ናቸው። በሌላ በኩል አዛውንቶችን በአራዳ ቃላት ማናገርም ሌላው ነውር ነገር ነው። ‹‹ላሽ ይበሉ፤ ዱቅ ይበሉ›› የሚሉ ቃላት ስድብ ይሁኑ አድናቆት አዛውንቶች ሊያወቁ አይችሉም።
ለአገር ፍቅር የተዘፈኑ ዘፈኖችንም በሌላ ይተኩታል። አንዳንዱ ከወጣት የማይጠበቅና ተስፋ አስቆራጭ ነው። ‹‹መማር ያስከብራል፤ ሀገርን ያኮራል›› የሚለውን ተወዳጅ ዜማ እንኳን ‹‹መማር ይደብራል፤ ሀገር ምን ያደርጋል›› በሚል ቀይረው ይጫወታሉ። በእርግጥ ይሄ የሰነፍ ተማሪ ስለሆነ ጎበዝ ተማሪ አይሰማቸውም፤ እንዲህ አይነት ወጣት በኩረጃ ያለፈ ወይም ትምህርት አልሳካለት ብሎ ያቋረጠ መሆን አለበት።
አንዳንዶቹ ግን ለማሳቅ ተብሎ የሚቀየሩ ናቸው። ለምሳሌ ‹‹ሃይሌ ሃይሌ ገብረሥላሴ›› የሚለውን የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ዘፈን ‹‹ሃይሌ ሃይሌ ገብረሥላሴ፤ ያለህን ግጨኝ ለሱሴ›› እያሉ ይጫወታሉ። ‹‹ለሱሴ›› የሚለው ነውር ቢሆንም ሀሳቡ ግን አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ሀብታም መሆኑንም የሚገልጽ ነው።
ሌላው የሀርሞኒካ ጨዋታ ደግሞ በሰፈር መወዳደስ ነው። በነገራችን ላይ በሰፈር መወዳደስ በገጠር አካባቢም የተለመደ ነው። የመጡበትን አካባቢ በመጥቀስ በጀግንነት ወይም በሥራ ሙያ ወይም በእንግዳ ተቀባይነት ይወዳደሳሉ፤ በወጣቶች ግን ብዙ ጊዜ የሚዘወተረው ጀግንነትን መሰረት ያደረጉ ዘፈኖች ናቸው። የአዲስ አበባውም ለዚህ የቀረበ ነው።
ተወልደን ተወልደን ተወልደን አራዳ
አምልጠን የለም ወይ ቦምብ ሲፈነዳ
ተወልደን ተወልደን ተወልደን ጉለሌ
መልሰን የለም ወይ የእርዳታውን ስንዴ
ተወልደን ተወልደን ተወልደን ማርገጃ
እምቢ ያልን እንደሆን ማምለጫውን እንጃ
እምቢ እንጃ እምቢ እንጃ!
እያሉ ይጫወታሉ። አጥኝዋ ስለሀርሞኒካ ጨዋታዎች ፋይዳ እንደጠቀሱት፤ ለከዋኞች ስነ ልቦናዊ እርካታና ማህበራዊ ትስስርን ይፈጥራል። የውድድር መንፈስን ያጠነክራል፤ ፈጠራን ያበረታታል። ፋይዳው ለከዋኞች ብቻ ሳይሆን ለአስተዳዳር አካላትም እንደሆነ ነው አጥኝዋ የሚጠቁሙት፤ ይሄውም የዘመናዊነትን ምንነት ለመተግባር የወጣቱን ማህበራዊ ስነ ልቦና ያሳያል። ለሚወጡ ፖሊሲዎች ያግዛል ማለት ነው። ራሱ የሀርሞኒካው ጨዋታም የቱሪዝም መስህብ ይሆናል።
የአጥኝዋ ጥቆማ ተግባር ላይ ቢውል ጥሩ ግብዓት ነው። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር (አሁን ባህልና ስፖርት የተባለው) በየጊዜው ‹‹መጤ ባህሎች›› እያለ ጥናትና ውይይት ያካሂዳል። ዳሩ ግን አዳራሽ ውስጥ ከሚደረግ ውይይት ባለፈ እንዲህ አይነት ሁነቶችን መከታተል ላይ እምብዛም ነው። ትክክለኛው የወጣቶች ስሜት የሚታወቀው ደግሞ በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ እንጂ ከየቀበሌው ለስብሰባ ከተጠራ ወጣት አይደለም። ለጥናት የሚሰማሩ አካላትም እንዲህ አይነት ቦታ ላይ ሄደው ሲሆን ትክክለኛውን ክዋኔ ያገኙታል። መጠይቅ አዘጋጅቶ በማሰራጨት ትክክለኛውን ክዋኔ ማግኘት አይቻልም።
በሌላ በኩል ደግሞ አገር በቀል የሆነውን ወግና ባህል ማስተዋወቅ የሚቻለውም በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ነው። ዓመታዊ የባህል ፌስቲቫል ከማዘጋጀት ይልቅ እንዲህ አይነቱ የህዝብ በዓል ላይ ማስተዋወቅ የበለጠ ተደራሽ ያደርገዋል። ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃንና የአስተዳደር አካላት ሊሰሩበት ይገባል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 11 /2015