በአሁኑ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ከገቡ ፅንሰ ሃሳቦች መካከል የፖለቲካ ገበያ (ፖለቲካል ማርኬት ፕሌስ) አንዱ ነው። የዚህ ጽንሰ ሀሳብ ትርጉም ምንድን ነው? ምንጩና መገለጫው እንዲሁም የዓለም አገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል? አሁን ላይ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ለምን መጣ ተባለ? ጉዳቱ ምን ያህል ነው ? የፖለቲካ ገበያ በኢትዮጵያ አለ ከተባለ ምን እርምጃ ተወሰደ ? ስንል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌን አነጋግረን እንዲህ አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- የፖለቲካ ገበያ ማለት ምን ማለት ነው? የሚመሠረተውስ በምን ላይ ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- የፖለቲካ ገበያ ግላዊ የፖለቲካ ግብይት ላይ የተመሠረተ ነው። የፖለቲካ ታማኝነት እንደሸቀጥ የሚቀርብበት ሲሆን፤ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ተሳታፊዎቹ ሊሆኑ ይችላሉ። ከላይ ሲታይ ፖለቲከኞች ሃሳብ ይዘው ለሕዝቡ ይቀርባሉ። ሃሳቡን ለገበያ አቅርበው ይወዳደሩበታል። ይህ ሲባል ዴሞክራሲን የሚያበረታታ ቢመስልም ዴሞክራሲን ያጠፋል።
ዴሞክራሲ እንደሚታወቀው በሃሳብ የበላይነት ላይ የሚያምን ሥርዓት አልያም በሃሳብ ዙሪያ ላይ ተከራክሮ አብዛኞቹ የሚስማሙበት ሃሳብ ተግባራዊ የሚሆንበት ነው። ይህንን ሂደት የፖለቲካ ገበያው ያጠፋዋል። ስለዚህ ይህ ሁኔታ በዓለም ላይ ባላደጉ አገሮችም ሆነ ባደጉ አገሮች በሁለቱም ላይ ልምዱ አለ። ባደጉ አገራት ላይ ተቋም ስለላ የፖለቲካ ገበያው አገር እንዳያፈርስ ጉዳዩን ተቋማት ይከታተላሉ። ተቋማት ተገንብተዋል። ነገር ግን ባላደጉ አገራት ላይ ተቋማት ስላልተገነቡ አገር እስከማፍረስ የመሄድ አቅም ያለው አደገኛ አዝማሚያ ነው። በማለት የፖለቲካ ገበያውን በአጭሩ መግለጽ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህ ፅንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መነገር የጀመረው አሁን ነው? አሁን ለምን ተነገረ? ለኢትዮጵያስ አሳሳቢ ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካ ገበያ ወይም ፖለቲካ ማርኬት ፕሌስ ብለን የምንጠራው እሳቤ፤ ሃሳቡም ተግባሩም ዓለምአቀፋዊና በሌሎች የዓለም አገራት ላይ ልምድ ነው። በኢትዮጵያ ብቻ ያለ አይደለም። ይህ እሳቤ ጎልቶ የወጣው በ20ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነው። ከዚያ እያደገ መጣ። በቅድሚያ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት ነው ተብሎ የመጣው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ነበር። ይህ እየተገነባ ከቀጠለ በኋላ፤ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ደግሞ የፖለቲካ ገበያ እንደ አንድ ልምድ በሁሉም አገራት ብቅ ብቅ ማለት ጀምሯል። ይህ የፖለቲካ ገበያ የአደጉ አገራትም ሆነ ያላደጉ አገራት ችግር ነው፡፡
ለአብነትም አፍሪካን ብንወስድ የፖለቲካ ገበያ ችግር ሰለባ የሆኑ አገሮች አሉ። አሁን ሁኔታውን ለመቀየር ከፍተኛ ጥረት ላይ የምትገኘው ሱማሌን ማንሳት ይቻላል። ሱማሌ በፖለቲካ ገበያ ችግር ምክንያት፤ ማዕከላዊ መንግሥት አጥታ አገር ወደ መበተን ደረጃ ላይ እንደተደረሰ የተለያዩ መረጃዎችና የተማራማሪዎች ጥናቶች ያሳያሉ። ስለዚህ አንደኛ በተጨባጭ በሌሎች አገሮች ላይ የታየ ችግር ነው። ሁለተኛ በየመን፣ በሊቢያና በሶሪያ ያሉ ግጭቶችና ችግሮችም ከፖለቲካ ገበያ ጋር እንደሚያያዝ የተለያዩ ጥናቶች አረጋግጠዋል። ስለዚህ የፖለቲካ ገበያ ችግር በባህሪው ዓለምአቀፋዊና በሌሎች አገራትም ከፍተኛ ጉዳትን እያስከተለ ያለ ነው። በተለይም ታዳጊ በሆኑ አገራት ላይ ግን የከፋ ችግር ያስከትላል። ከፍተኛ ችግር የሚያስከትልበት ምክንያትም ተቋም የገነቡ ባለመሆናቸውና በሌሎችም ችግሮች ምክንያት ነው።
ወደ ኢትዮጵያም ስንመጣ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ የፖለቲካ ገበያን በተመለከተ ኅብረተሰቡ እንዲያውቅና እንዲረዳ፤ መንግሥትም በተገኘው አጋጣሚ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው እየሠራና ሚዲያዎችም የጉዳዩን ምንነት ለማሳወቅና እየሠሩ ያሉበት ዋናው ምክንያት በአሁኑ ወቅት አዝማሚያው በከፍተኛ ሁኔታ ጎልቶ በመውጣቱ ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ገበያ አዝማሚያ በእጅጉ ጎልቶ የወጣበት ጊዜ ላይ ስለደረስን፤ ይህንን ጎልቶ የወጣውን የፖለቲካ ገበያ አዝማሚያ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው መክተው መልክ ካልስያዙት ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ገበያ በዚህ ደረጃ አጀንዳ ሆኖ ወጥቷል።
የፖለቲካ ገበያ በኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ ተዋንያን አላቸው። አሁን ስለ ኢትዮጵያ እየተመለከትን በመሆኑ ለአብነትም ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ገበያ ተዋናዮች እነማናቸው ብለን ብንወስድ ፖለቲከኞች፣ የሚዲያ ሰዎች፣ አክቲቪስቶች፣ የታጠቁ ቡድኖች፣ በዚህ ሂደት እናተርፋለን የሚሉ ባለሀብቶች የሚሳተፉበት ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ገበያ ላይ እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ የውጭ ኃይሎችም ይሳተፉበታል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ የተረጋጋ ከሆነ፤ የተሻለ ከሆነና ኢትዮጵያ ታድጋለች፤ ትበለጽጋለች፤ ስለዚህ ለእኛ ስጋት ትሆናለች ብለው በተሳሳተ መንገድ የሚያምኑ የውጭ ኃይሎች፤ ሁሌም ቢሆን የኢትዮጵያን ዕድገት፣ ብልጽግናና ከፍታን የማይፈልጉ ኃይሎች አሉ። እነዚህ አካላት ጭምር የሚሳተፉበት ነው።
የፖለቲካ ገበያው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ በአገር ውስጥ ያሉ አካላት ብቻ የታጠረ ሳይሆን ከአገር ውጪ ዓለም አቀፋዊ በሆኑ ኃይሎች የሚደገፍ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህን ነገሮች ለማባባስ እንደመግቢያ በር የሚጠቀሙ ማቀጣጠያዎችም አሉ።
እንደሚታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያን በብዘኃነታችን እንታወቃልን። ኢትዮጵያውያን የተለያየ ማንነት ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ወግ እና ባህል አለን። የተለያየ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥም አለን። አንድ ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅ ኃያል አገር እንገነባለን ብለን እየሄድን ነው። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ሆና የተፈጠረችው በተፈጥሮ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦችን ይዛ ነው። አንዱ የፖለቲካ ገበያተኞች ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱት፤ ይህንን በተፈጥሮ ያለውን ብዘኃነትና በዚህ ብዘኃነት አስተዳደር ውስጥ ባለፉት ዘመናት በመጣንበት መንገድ የተፈጠሩ የቅሬታ የቁርሾ መነሻ ናቸው የሚባሉ ጉዳዮችን በከፍተኛ ሁኔታ በማቀጣጠል ነው።
በሌላ አባባል ማክረርን እንደማሳያ መግለፅ ይቻላል። የብሔር አክራሪነት፣ በሃይማኖት ውስጥ ሽፋን አድርገው ሃይማኖትን መነሻ ያደርጋሉ። የትኛውም ሃይማኖት በራሱ አክራሪ አይደለም፤ ብሔርም በራሱ አክራሪ አይደለም። አክራሪዎች ግን ብሔር ውስጥ ያለውን ጉዳይ በማክረር ሃይማኖት ውስጥ ያለውን ጉዳይ በማክረር፤ ግጭት ለመቀስቀስና የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ነጋዴዎች አሉ።
በሦስተኛ ደረጃ ኋላቀርነትና ድህነት አለ። በዚህ ምክንያት ያሉ ብሶቶችና ችግሮች ላይ ቤንዚል በመጨመር ለማቀጣጠል ይፈልጋሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ዘመኑ ማህበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነበት ጊዜ ስለሆነ የሀሰት ትርክቶችና የሀሰት ወሬዎችን በከፍተኛ ደረጃ በማሰራጨት ሕዝብ ውስጥ ግራ መጋባት በመፍጠር የፖለቲካ ነጋዴዎች ይጠቀማሉ። ስለዚህ በእኛ አገርም በሌሎች አገርም ከላይ የተጠቀሱ ማባባሻ መንገዶችን ተጠቅመው፤ አንደኛ ግጭት እንዳይቆምና እንዲቀሰቀስ ይሠራሉ። ሙስናና ዝርፊያ እንዳይቆም፣ መረጋጋት እንዳይኖር አድርገው ይሠራሉ። በዚህ ሂደትም ይጠቀማሉ።
እነዚህ ነገሮች በአገራችን በተለያየ መንገድ ይገለጣሉ። ለምሳሌ የሆነ ቦታ ላይ ንጹሐን ላይ ከኢትዮጵያ ባህል ወጣ ባለ መንገድ ጥቃት እንዲፈጸም ያደርጉና ቅድም እንደጠቀስኩት የታጠቁ ቡድኖችና ሚዲያዎች አንዱ የፖለቲካ ገበያ አካል በመሆናቸው በታጠቁ ኃይሎች ይሄ ሲሆን ደግሞ ሚዲያዎቻቸው ይህንን የብሔር ቅርፅ ያስይዛሉ። ይህንን የሃይማኖት ቅርጽ ያስይዙታል። መንግሥት ላይ ኅብረተሰብ እንዲነሳሳ ያደርጋሉ። ይህንን መሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ በሃሰት ስም ለማጥፋት ይጠቀሙበታል። ስለዚህ በአጭሩ መንግሥትና ሕዝብ እንዳይተማመን፤ መንግሥትና ሕዝብ አብሮ እንዳይቆም፤ መንግሥትና ሕዝብ አብሮ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ እንዳይችሉ ይሠራሉ። በዚያ መሀከል ለማትረፍ ይሠራሉ ማለት ነው። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ መሠራት ያለባቸው የተለያዩ ሥራዎች አሉ።
ለዚህ ወሳኝ ነው የሚባለው የዴሞክራሲ ባህልን መገንባት እና የአስተሳሰብ ባህላችን መቀየር አንዱ ነው። ፖለቲካችን ከኔትወርኪንግ እና ከኢ- መደበኛ አደረጃጀት ወጥቶ፤ ተቋማዊ መሆን አለበት። ፖለቲካችን በመርህ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። ፖለቲካችን ማንኛውም ፖለቲካዊ ጉዳይ በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግረን መፍታት እንችላለን ወደሚል መምጣት አለበት። ከመጠፋፋት እሳቤ መውጣት አለበት።
የተለያየ ሃሳብ የያዙ አካላት ለአንድ አገር እንደሚሠሩ አምነው፤ እነዚህ አካላት የተሻለ ተከታይ ማፍራት የሚችሉት የተሻለ ሃሳብ በማምጣት ነው እንጂ፤ ፖለቲካን በመግዛት፣ በማጭበርበር፣ የሃሰት ወሬ እና ትርክትን በመገንባት ወይም በአፈ ሙዝ የበላይነት ነው ብሎ የሚታመንበት ሁኔታ መቀየር አለበት።
ስለዚህ የዴሞክራሲ ባህል መገንባት እና ዴሞክራሲያዊነት ማጎልበት፤ ምክንያታዊ እሳቤዎችን ማጎልበት፤ ከስሜት፤ ከጊዜአዊ ፍላጎት እና ጥቅም እንዲሁም አገር እና ሕዝብ የራሱ ጉዳይ ብሎ ከመንቀሳቀስ መቆጠብ አለበት ማለት ነው።
ሌላው ልማትን ማፋጠን ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው። ይሄ ማለት የሥራ አጥነትን ችግር መፍታት፣ በድህነት እና በኋላ ቀርነት ምክንያት የሚፈጠሩ ብሶትንና ኋላቀርነትን ማስወገድ ያስፈልጋል። ስለዚህ ለሁላችንም የተመቸች አገር እንገነባለን ብለን ያስቀመጥነውን ግብ ኢትዮጵያውያን ለማሳካት በጋራ መቆም አለብን። ስለዚህ እያንዳንዱ አካል በተሰማራበት ውጤታማ መሆን አለበት።
አራተኛው ሌብነት እና ብልሹ አሠራርን ማስተካከል ነው። ሌብነት ካለ እና ብልሹ አሠራር ካለ ብሶት ይኖራል አለመረጋጋት ይኖራል። ይሄን ደግሞ የፖለቲካ ነጋዴዎች ይፈልጉታል። ይህ ደግሞ በማያቋርጥ እሽክርክሪት ውስጥ የሚያስገባን ነው።
ስለዚህ ከዚህ መውጣት፤ ለአገር ለሕዝብ ለነገው ትውልድ የሚሆን ተቋም መገንባት ያስፈልጋል። ድህነትን እና ብልሹ አሠራርን በጋራ መታገል ያስፈልጋል። አሁን ላይ መንግሥት በሙስና እና በሌብነት ዙሪያ ላይ የጀመረውን አገራዊ ንቅናቄ ማገዝ፤ የፖለቲካ ነጋዴዎች ረጅም ርቀት እንዳሄዱ ያደርጋቸዋል።
የመጨረሻው ደግሞ ለአገር የሚሆን ተቋም መገንባት፤ ለኢትዮጵያ የሚሆን ተቋም መገንባት ወሳኝ ናቸው። እነዚህን መሰል ነገሮችን በማድረግ ፖለቲካ ገበያውን መግታት ካልተቻለ በጣም አደገኛ ውጤት ሊያስከትል ስለሚችል አሁን ላይ ጉዳዩ አጀንዳ ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡- የፖለቲካው ገበያ ለኢትዮጵያ ፈተና ነው?
አቶ ተስፋዬ፡– የፖለቲካ ገበያ በኢትዮጵያ ደረጃ በጣም አደገኛ እና ከባድ አዝማሚያ ይዞ የመጣ ነው። በጋራ ሆነን ግን ይህንን የማሸነፍ ብቃት አለን። ምክንያቱም ብዙ ችግሮችን ኢትዮጵያውያን በጋራ አልፈን እናውቃለን። ስለዚህ የፖለቲካ ገበያው አደጋ አለው፤ አይናቅም። በጋራ ሆነን ማሸነፍ እንችላለን።
በጋራ መሆን ካልቻልን ግን በተለያየ መንገድ፤ የፖለቲካ ገበያተኞች በሚፈልጉት መንገድ አስቀድሜ እንዳልኩት ፖለቲካ ገበያ ውስጥ የውጭ ጠላቶችም ያሉበት በመሆኑ ጉዳዩ የሚናቅ አይደለም። የውጭ ጠላቶች ደግሞ ሁሌም ኢትዮጵያ እርስ በርስ እንድትባላ፤ እርስ በእርስ የተከፋፈለች፤ ደካማ ሆና እንድትቆይ የሚፈልጉ አካላት ያሉበት ነው ።
ኢትዮጵያ ከዛሬ መቶ አመታት በፊት፣ ያኔ በጨለማው ዘመን ለውጭ አካላት እጅ ያልሰጡ ኢትዮጵያውያን ያሉባት እና የኖሩባት ምድር ናት። ስለዚህ ትናንት አባቶቻችን በደም መሰዋዕትነት፤ በሕይወት መሰዋዕትነት አገራችንን አቆይተው ለዚህኛው ትውልድ አስተላልፈዋል። እኛ ደግሞ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመቆም፤ ልማትን በማረጋገጥ፣ ኋላቀርነትን በመቅረፍ፤ በጦርነት እሽክርክሪት ውስጥ እንድንቆይ ያደረገውን የፖለቲካ ባህላችንን በመቀየር ፤ የፖለቲካ ገበያተኞች አገርን እንዳይበትኑ ማድረግ እንችላለን አቅሙም አለን። በጋራ መቆም ከቻልን ለሌሎችም ምሳሌ መሆን እንችላለን።
አዲስ ዘመን ፡- ይሄን ያህል ችግር መሆኑ ከታወቀ ምን እርምጃ ተወሰደ?
አቶ ተስፋዬ፡– መላው ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ ገበያ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። የጋራ ግንዛቤ እንዲፈጠር መንግሥት እየሠራ ነው። ሚዲያውም ይህንኑ በመሥራት ሕዝቡ አደጋው ስለመኖሩ እንዲያውቅ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። ፖለቲከኞች አደጋው መኖሩን፣ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ ዜጎች ጭምር ይሄ ችግር መኖሩን ማወቅና በጉዳዩ ላይ መነጋገርና መወያየት እንዲሁም ከዚህ ችግር መውጣት የሚቻለው እንዴት ነው ብለው ማሰብ እንዲችሉ ማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።
ከዚያ በመቀጠል አሁን በአገር ደረጃ ለአብነትም በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል የተከሰተውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው ያለው። ስለዚህ ሰላም ለመገንባት የተጀመሩ ሥራዎችን እንዳይቀለበሱ ማድረግ፤ ሰላም በየትኛውም ሁኔታ የሁሉም ነገር ቅድመ ሁኔታ መሆን አለበት። ከሰላም አኳያ ዜጎች በአንድነት መቆም አለብን። ሰላም ሲጠፋ የተወሰነ የመንግሥት አካላት፣ የተወሰነ የፓርቲ አባላትና አመራሮችን ብቻ ሳይሆን የሚያሳጣን አገርንም ጭምር ነው። ስለዚህ በሰላም ግንባታ ዙሪያ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አሉ። በዚህ ዙሪያ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በማገዝ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማድረግ ነው።
በሦስተኛ ደረጃ ሙስና፣ ሌብነት እና ብልሹ አሠራሮችን በተመለከተ እንደሚታወቀው አገራዊ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው። መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። ምክንያቱም የፖለቲካ ገበያተኞች አንዱ የሚያተርፉት ሙስና ብልሹ አሠራር እና ዝርፊያ ሲኖር ነው። ይህን ለመመከት መንግሥት እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች አሉ። ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። በየጊዜው በሚዲያ የሚገለጹ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በሕዝብ ተወካዮች ቀርበው በጉዳዩ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብን እና የመንግሥት አቋም ከገለጹ በኋላ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አሉ። ከዚህ አኳያ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ላይ ሕዝቡ ሁሉ ተረባርቦ መንግሥትን ማገዝ፤ መሪዎችን ማገዝ፤ ይህ እቅድ እንዲሳካ ማድረግ ፤ የተጀመረው ሥራ ዳር እንዲደርስ ማድረግ ፤ የተጀመረውን ሥራ ማጠናከር እና የፖለቲካ ገበያ ለመቀልበስ የሚያግዝ ነው የሚሆነው።
አራተኛው ሃሳብ ደግሞ መንግሥት ተቋማትን ለመገንባት የጀመራቸው ሥራዎች አሉ። ተቋማት ነፃ፣ ገለልተኛ ፣ የአንድ ጠባብ ፖለቲካ ፓርቲ መሆን የለባቸውም። ለምሳሌ አሁን አገር እየመራ ያለው ብልጽግና ፓርቲ ነው። በዚህ አገር ላይ ብልጽግና ፓርቲ ለዘላለም ይኖራል ማለት አይደለም። ነገ ደግሞ ሌላ ፓርቲ ሊመጣ ይችላል። ይመጣልም ! ጥርጥር የለውም። ነገር ግን አሁን ብልጽግና ፓርቲ ለውጡን የመምራት እና መንግሥትንም የመምራት ዕድል ሕዝቡ ስለሰጠው መንግሥት እየሠራ ያለው ለአገር የሚሆን፤ ለሁሉም ዜጎች የሚሆኑ ተቋማት መገንባት አለባቸው ተብሎ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። ለምሰሌ፡- በምንም መንገድ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ እሳቤ ማዕከል መደረግ የሌለባቸው ተቋማት አሉ። እነዚህ ተቋማት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚሆን መንገድ መኖር አለባቸው። ለምሳሌ ምርጫ ቦርድ፣ ሰብዓዊ መብት፣ የጸጥታ ተቋማት የመሳሰሉትን ለመገንባት የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። የእነዚህ የተቋማት ግንባታ ሥራ ማጠናከር አንዱ ነው ።
ስለዚህ እዚህ ላይ አንዱ የፖለቲካ ገበያ ጎልቶ የሚወጣው ወይም አደጋ የሚያስከትለው ተቋም ሳይገነባ ሲቀር በመሆኑ፤ ችግር እንዳይፈጠር ተቋም በመገንባት ሥራ ላይ መንግሥት የጀመራቸው ሥራዎች አሉ። በዚህ ዙሪያ ላይ የተቋማት ግንባታ የተጀመረውን ሥራ የሚመለከታቸው አካላት በሚገባ አጠናክረው ይዘው መቀጠል አለባቸው፤ ዜጎችም እዚህ ላይ ማገዝ አለባቸው።
በአጠቃላይ በአገር ደረጃ የተጀመረው ለውጥ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን ከገባችበት ችግር መውጣት በሚያስችል መንገድ ነው። ለውጡ (ሪፎርሙ) ከተሳካ የፖለቲካ ነጋዴዎች ገበያ ስለሚጠፋ ለውጡን ለማደናቀፍ ከተቻለም ለመቀልበስ የሚደረግ ርብርብ አለ። ይህ የኢትዮጵያውያን ለውጥ የኢትዮጵያውያን ጥያቄ መነሻ አድርጎ የተጀመረ እንቅስቃሴ እንዳይሳካ መሥራት አለባቸው ማለት ነው። ለምሳሌ አሁን በአገር ደረጃ ብንመለከት ማንኛውም ጉዳይ ላይ ልዩነት እየሰፋ፤ ማንኛውም ጉዳይ ላይ አጀንዳ እንዳይጠፋ በማድረግ ጥርጣሬና አለመተማመን በመንግሥት እና በሕዝቡ መካከል እየሰፋ እንዲሄድ ከፍተኛ ዘመቻ የሚካሄድበት ወቅት ነው። ይሄ አገርን፤ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመገንባት አያግዝም። ከዚህ አኳያ ምሁራኑ፣ የሚዲያ፣ የፖለቲካ ሰዎችም ፣ የሃይማኖት መሪዎችም፣ አርቲስቶችም ፣ የሃሳብ መሪዎች የሚባሉት በሙሉ አገርን በማስቀደም በጋራ መሥራት ይገባናል።
በእኛ አገር ላይ ሁለት ሦስት ነገሮች ይደበላለቃሉ። ለምሳሌ አገረ መንግሥት ማለትም ኢትዮጵያ የምትባል አገር የሁላችንም ናት። ፖለቲካ ፓርቲ ደግሞ የውስን አካላት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አገርን እና የፖለቲካ ፓርቲን ማቀላቀል፤ አገርን እና አስተዳደርን የማቀላቀል ሁኔታዎች ይታያሉ።
አገር የሁላችንም ናት። ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነገር ላይ በጋራ መቆም አለብን። የሚታረሙ የሚስተካከሉ ነገሮች ላይ ደግሞ በአጠቃላይ በታላቋ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ የፖለቲካ ሃሳቦችን ማራመድ ስለሚቻል ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ከገባች የፖለቲካ ፓርቲ ወዘተ ትርጉም የለውም ማለት ነው።
ስለዚህ መጀመሪያ አገራችን የተረጋጋች፣ አገራችን ሰላማዊ እንድትሆን፣ ሰላም ከሁሉም በላይ የመጀመሪያ መንገድ መሆኑን በሁሉም አካላት መገንዘብ ከተቻለ ኢትዮጵያውያን ከዚህ አኳያ አገራቸውን የሚወዱ በዓለም ደረጃም የምንታወቅበት አኩሪ ታሪኮች ያሉን ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን በጋራ የምንቆም ከሆነ አሁን በፖለቲካ ገበያው ምክንያት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ማለፍ እንችላለን ማለት ነው ፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ተስፋዬ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥር 11 /2015