አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ ከስደት ተመላሽ ዜጎቿን በሀገራቸው መልሶ ለማቋቋምና ለማዋሀድ የሚያስችል የ15 ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ከአውሮፓ ህብረት ጋር መፈራረሟ ተገለፀ።
አቶ እዮብ አወቀ፤ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር ትናንት በኢሊሌ ሆቴል በተደረገው ሀገራዊ ከስደት ተመላሾችን መልሶ የማቋቋምና የማዋሀድ የምክክር መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ ከተለያዩ ሀገራት ለሚመለሱ በርካታ ኢትዮጵያውያን፤ በተለይም ከአውሮፓ የሚመጡ የስደት ተመላሾችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋምና ለማዋሀድ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የ15 ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ተፈራርማለች።
ፕሮጀክቱ፤ በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከአውሮፓ ለሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ከስደት ተመላሾችን በዘላቂነት በሀገራቸው ላይ እንዲቋቋሙ የሚያስችል ነው።
በአሁን ወቅት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ በአዲስ መልክ በሰላም ሚኒስቴር ስር ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ኤጀንሲው ከስደት ተመላሾችን ጉዳይ ከሚመለከታቸው የክልል፣ የፌዴራል፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋር በመሆን ተመሳሳይና ወጥ የሆነ አሰራር በመዘርጋት በሀገራቸው ላይ መቋቋም እንዲችሉ በዘላቂነት ይሰራልም ብለዋል።
አቶ ዘውዱ በዳዳ፤ የስደት ተመላሾች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የፕሮጀክት ኃላፊ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ከስደት ተመላሾችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋምና ለማዋሀድ የተዘጋጀው የምክክር መድረክ ዋና ዓላማው በተበጣጠሰ መልኩ ሲሰሩ የነበሩ ስራዎችን ወደ አንድ በማምጣት መልክ ማስያዝ ነው። ይህም ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረጉ ጥረቶችን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ የሚያስችልና የመንግስትን አቅም የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።
ኤጀንሲው፤ ስራውን ከጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል ያሉት ኃላፊው፤ በዋናነት የሚሰራውም ከስደት ተመላሽ ለሆኑ ዜጎች ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ድጋፍ በማድረግ በዘላቂነት ራሳቸውን በገቢ የሚደግፉበትን ስርዓት መፍጠርና በቀላሉ ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀል እንዲችሉ ማድረግም ነው ብለዋል።
መድረኩ የተዘጋጀው በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ሲሆን፤ የአውሮፓ ህብረት ተወካይና አባል ሀገራት፤
ኤምባሲዎች፣ ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተሳትፈዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011
በፍሬህይወት አወቀ