አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ለአዲስ አበባ ፈጣን አውቶብስ መንገድና ለአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አምስት የልቀት ማዕከላት ግንባታ የሚውል የ300 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበና በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሚስተር ሊም ሙንሚን ትናንትና በገንዘብ ሚኒስቴር አዳራሽ የብድር ማዕቀፍ ስምምነት በተፈረመበት ወቅት አቶ አድማሱ እንደገለጹት፤ የደቡብ ኮሪያ መንግስት ለኢትዮጵያ የምትሰጠው የ300 ሚሊዮን ዶላር ቀላል የብድር አይነት ሲሆን ዘንድሮና በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት የሚተገበር ነው፡፡
የብድር ስምምነቱ ተግባራዊ የሚሆነውም ሁለቱ መንግስታት ቅድሚያ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ብለው በመረጧቸው የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አምስት የልህቀት ማዕከላት ለማቋቋምና የአዲስ አበባ ፈጣን የአውቶብስ መንገድ ግንባታን ለማከናወን መሆኑን ገልጸው፤ የደቡብ ኮሪያ መንግስት ለኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴዎች ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥልም አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሚስተር ሊም ሙንሚን በበኩላቸው፤ ደቡብ ኮሪያ ለታሪካዊ ወዳጇ ኢትዮጵያ የ300 ሚሊዮን ዶላር ቀላል ብድር ለመስጠት መወሰኗ የሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ደቡብ ኮሪያ እኤእ ከ2016 እስከ 2018 በኢትዮጵያ ለተከናወኑ የሀይል ማሰራጫ፣ ለመንገድና ለጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ 500 ሚሊዮን ዶላር ቀላል ብድር ማበደሯ ተገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011
በጌትነት ምህረቴ