አዲስአበባ፤– የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ጎብኝዎችን ቁጥር 37 ሚሊዮን 171 ሺህ 869 ለማድረስ አቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 23 ሚሊዮን 415 ሺህ 53 መድረሱን አስታወቀ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸሙን ባቀረበበት ወቅት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳሁን እንዳስታወቁት፤ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ማደግ ዘርፉ እንዲያድግ፣ አገልግሎቱ እንዲዘምንና የውጭ ቱሪዝም እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረክታል። ቱሪዝምን ዘላቂ የሚያደርገው የአገር ውስጥ ቱሪዝም በመሆኑ መንግስት ስልት ነድፎ እየሰራ ነው። ከፍተኛ መሻሻልም እየታየ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ እንደገለጹት፤ በዘጠኝ ወራት 505 ሺህ 769 የውጭ አገር ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። ከጎበኙት ቱሪስቶች አገሪቱ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች።
ቀደም ሲል የውጭ አገር ቱሪስቶችን የተመለከተ የመረጃ አሰባሰብ ስርዓት ውስንነት ነበረው። አሁን ላይ የአሰባሰብ ስርዓቱን ዘመናዊ በማድረግ መረጃው ተሰብስቧል። ቀደም ሲል መረጃ የተሰበሰበበት ስርዓት ችግር መሆኑን በማንሳት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የቱሪስት ቁጥር ከለፉት ጊዜ በተሻለ እየጨመረ መምጣቱን አመላክተዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት የካፒታል በጀትአፈፃፀም ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ምን እንደሆነ ማብራሪያ ጠይቀዋል። የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ በተያዘው እቅድ ያለመከናወኑና የመዳረሻ ቦታዎች ያለመልማታቸው ተነስቷል። የስፖርት ፌዴሬሽኖች በጀት አጠቃቀም፤ ተግባራቸውን መፈጸማቸውን ያለመከታተል ችግር፣ የኦዲት ጉድለቶች ማስተካካያ እና ሌሎች ጥያቄዎችን ማብራሪያ ጠይቀዋል።
ዶክተር ሂሩት፤ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ቅርሶች ከደረሰባቸው ጉዳት አንፃር የአክሱም ሀውልት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የአባ ጅፋር ቤተመንግስት ቅርሶችን ለመጠገን የተለያዩ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ቅርሶችን በማስጠገን ሂደት ገንዘብ የሚለግሱ፣ በዓለም የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅትየተመዘገቡ፣ የቅርስ ባለቤቶችን ይሁንታ ስለሚፈልጉና ጥገናውን ከሚያከናውኑ ድርጅቶች የጋራ መግባባት ለመድረስ ውስብስብ ሂደት ስለሚያልፍ በፍጥነት ስራውን ለማከናወን አልተቻለም። ሌሎች በርካታ ቅርሶች የሚጠገኑ ቢኖርም በመንግስት አቅም ውስንነት ሁሉንም ማከናወን አልተቻለም። ሰለሆነም ቅርሶች የሁሉም በመሆኑ ክልሎችና ዜጎች ቅርሶችን ለመጠገን መስራት አለባቸው ብለዋል።
ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዘጠኝ ወራት ለብሄራዊ ስታዲየም ግንባታ፣ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ፣ ለቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ግንባታ እና ለታዳጊ ወጣቶች ስፓርት ፕሮጀክት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የካፒታል በጀት የተያዘ ሲሆን ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የዕቅዱ 30 በመቶ ተፈጽሟል። አፈፃፀሙ ዝቅተኛ የሆነውም ፕሮጀክቶቹ በጨረታ ሂደት በመሆናቸው ነው። በቀጣይ ወራት ወደስራ ስለሚገባ አፈጻጸሙ እንደሚሻሻልም አመላክተዋል።
የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለማልማት ስልት ተነድፎ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የስፖርት ፌዴሬሽኖች አፈጻጸም ችግር መሆኑን አምነው ለማስተካከል ይሰራል ብለዋል። የኦዲት ማስተካከያ እየተሰራ ነው፤ ሆኖም አንዳንድ ሰዎች በህይወት የሌሉ በመሆኑ ለውሳኔው የምክር ቤቱ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011
በአጎናፍር ገዛኸኝ