አጣዬ፤ በአጣዬ ከተማ በአንጻራዊነት ሰላም በመስፈኑ ከጥቃቱ በኋላ ተዘግተው የነበሩ ባንክ እና የተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ትናንትና ተከፍተዋል። አጎራባች የሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳ ህዝብ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተገልጿል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደምሰው መሸሻ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ከጥቃቱ በኋላ ባንክን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማትን አገልግሎቶችን የሚፈልገው ህዝብ እስከ አሁን አገልግሎቱን ማግኘት አልቻለም። አሁን ግን የመከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ከአማራ ክልል ልዩ ሃይል ጋር በሚያደርጉት ጥበቃ አንጻራዊ ሰላም እየታየ ነው።
ከአካባቢው ሽማግሌዎች፣ ባለሃ ብቶች እና የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር ውይይት መደረጉን የገለጹት አቶ ደምሰው፣ንግድ ባንክን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማት ተከፍተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
በወረዳው በደረሰው ጥቃት 9 ሺ ሰዎች ለአስቸኳይ እርዳታ ተጋልጠዋል። ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚሆን እርዳታ እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል። ከዚህ ውስጥ ቤት የፈረሰባቸው፣ የተዘረፉ እና የተፈናቀሉ ዜጎች በመኖራቸው ለማቋቋም የሚያስችል ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለእለት ደራሽ ምግብ በተጨማሪ የመጠጥ ውሃ እና የተለያዩ ድጋፎች ለህብረተሰቡ መድረስ እንዳለበት ጥሪ ያቀረቡት አቶ ደምሰው፤እስከአሁን ድረስ አጎራባች የሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳ ህዝብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ የጣርማ በር እና ሸዋሮቢት ወረዳ ህዝብ ለተጎጂዎች 240 ሺ ብር በላይ እንዲሁም በአይነት ደግሞ ግምቱ 100 ሺ ብር የሆነ ንብረት ድጋፍ አድርገዋል።
የደብረብርሃን ከተማ ባለሃብቶች እና ነዋሪዎች ደግሞ የእለት ደራሽ ብስኩቶች እና 12 ሺ ሊትር የታሸገ ውሃ አቅርበዋል። የአንኮበር እና ሞረትና ጅሩ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም የህብረተሰቡ ድጋፍ ብቻ በቂ ባለመሆኑ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአጣዬ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰለሞን ጋሻው እንደገለጹት፤ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ፈጥነው የደረሱት የአካባቢው ሚሊሻዎች ናቸው። ይሁንና ችግሩ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ደርሷል።
ከመጋቢት 27ቱ ጥቃት ሁለት እና ሶስት ቀናት በኋላ መከላከያ ሰራዊት በመግባቱ ከቀን ወደቀን አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ ይገኛል። በመሆኑም የጸጥታ ጥበቃው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011
ጌትነትተሰፋማርያም