አዲስ አበባ፦ ለተሽከርካሪና ለትራንስፖርት ድርጅቶች ከነዳጅ ቀጥሎ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቀው ጎማን በማደስ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይቻላል ተባለ።
አቶ አየለ አስፋወሰን የእጥፍ ጎማ ቁጠባ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጥቶባቸው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ጎማዎች የወጣባቸውን ወጪ ያህል ሳያገለግሉ እየወደቁ ይገኛሉ።
ለዚህም ዋናው ምክንያት ህብረተሰቡ ጎማን መልሶ የመጠቀም ቴክኖሎጂን ባለማወቁና ግንዛቤ ባለመፈጠሩ ነው ይላሉ።
አንድ ጎማ በ13 ሺህ ብር እንደሚገዛ የገለፁት ስራ አስኪያጁ፤ ጎማው ተሽከርካሪው
ላይ ተገጥሞ ከ45 ሺህ እስከ 50 ሺህ ኪሎሜትር የሚያገለግል ሲሆን፤ ተሳቢ ላይ በመግጠም ደግሞ 20 ሺህ ኪሎሜትር በድምሩ 70 ሺህ ኪሎሜትር ብቻ አገልግሎ ጎማው ይጣላል። ነገር ግን ጎማው ከመውደቁ በፊት በእጥፍ ጎማ ቁጠባ ቢጠገን ብዙ ሺህ ኪሎሜትሮችን መልሶ እንዲያገለግል ማድረግ ይችላል። በዚህም ለጎማ የሚወጣውን ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል።
አንድ አዲስ ጎማ መኪናው ላይ ቢበዛ 45 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን አገልግሎ ተሳቢ ላይ ያገለግል የነበረውን 20 ሺህ ኪሎሜትር በመተው በአራት ሺህ ብር ቢጠገን ከጥገና በኋላ በአምስት ጊዜ እጥፍ ተሳቢው ላይ 100 ሺህ ኪሎሜትሮችን ማገልገል ይችላል።
በተጨማሪም አንድን ጎማ ሶስት ጊዜ ማደስ እንደሚቻል የተናገሩት ስራ አስኪያጁ፤ 45 ሺህ ኪሎሜትሮችን ያገለገለው ጎማ ሶስት ጊዜ በማሳደስ በ12 ሺህ ብር 300‚000 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ማገልገል እንደሚቻልም አብራርተዋል።
እጥፍ ጎማ ቁጠባ በአሁን ወቅት ለ25 የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል በመፍጠር በቀን እስከ 160 ጎማዎችን በማደስ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል እያደረገ የሚገኝ አምራች ኢንዱስትሪ ሲሆን፤ ማህበረሰቡ ቴክኖሎጂውን ቢያውቅና ግንዛቤውን ተፈጥሮለት ጎማዎችን እስከ 45 ሺህ ኪሎሜትሮች ተጠቅሞ ቢያቀርብ ከመቶ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ይቻላል።
ከዚህም በላይ የውጭ ምንዛሪን በማዳን በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፍ ይቻላል ያሉት አቶ አየለ፤ በዚሁ በመልሶ ማደስ ቴክኖሎጂ የመኪና ብቻ ሳይሆን የአውሮፕላንም ጎማ ተጠግኖ ማገልገል እንደሚቻል ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2011
በፍሬህይወት አወቀ